“እጅግ በጣም አዛኝ ሩኅሩህ በኾነው.. “
ወደ ርዕሰጉዳያችን ከመግባታችን በፊት እጅግ ለማከብራቸውና ለምወዳቸው ሙስሊም አንባብያን ከፍ ባለ ትህትና ልላቸው የምፈልገው ነገር ይኖረኛል። ይህ ጽሑፍ ሙስሊሞች እውነትን ያውቁ ዘንድ እንጂ እነርሱን የማበሳጨት ዓላማ የለውም። ከዚህ በታች የምጠቀማቸው ምንጮች በሙሉ “የአላህ ቃል” ተብሎ በሙስሊሞች ከሚታመነው ከቁርአን የተወሰዱ ናቸው። በመኾኑም ቁርአንን ቃል በቃል ስለምጠቅስ ከእኔ ጋር ሳይሆን ከመጽሐፋቸው ጋር እንዲዋቀሱ ለመጠቆም እወዳለሁ። መልካም ንባብ!
እስላማዊ የኅዘኔታ ትርጉም በመዝገበ ቃላት ከሚታወቀው የተለየ ካልሆነ በስተቀር ከእስላማዊ ምንጮች የምናውቃቸው አላህም ሆነ ሙሐመድ ከቶውኑ የማዘን አዝማሚያ አይታይባቸውም። አላህ በቁርኣን ለ «100» ያህል ጊዜያት “አዛኝ ነው” ተብሎ ተወድሷል። በሀገራችን ብሂል “መልከ-ጥፉን በስም ይደግፉ” በሚለው አረዳድ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ መባሉ ቃላትን አላስፈላጊ ስፍራ በማዋል ከማባከን የዘለለ አንዳች የሚፈይደው ነገር የለም። አላህ «እጅግ በጣም አዛኝ፣ ሩኅሩህ» ተብሎ በተደጋጋሚ ቢጠቀስም ግብሩ በተቃራኒው እንደሆነ በቀላሉ እዚያው ቁርአን ውስጥ እንመለከታለን።
“እጅግ በጣም አዛኝ” ማለት ወዳጆቹን ብቻ ነጥሎ የሚወድ ወዳጆቼ አይደሉም ላላቸው ደግሞ እጅግ በጣም ጨካኝ የሚሆን ማለት አይደለም። ይህ የተለመደ ዓይነት ባሕርይ እንጂ አዛኝ የሚባል ተቀፅላ አያስፈልገውም። አዛኝነት በዚህ የሚለካ ከሆነማ እናት ጅብም ለልጆቿ ታዝናለች። የአንድ አካል አዛኝነት የሚመዘነው ጠላቶቼ ወይንም አላውቃቸውም ለሚላቸው ወገኖች በሚያሳየው ምህረትና ርህራሄ ልክ ነው።
ሰዎች በኾነ ወቅት አለመግባባት፣በሐሳብ መለያየት፣ ግጭት ሊገጥማቸው ይችላል፤ ይህም ወደ ጥላቻ ሊያመራ ይችላል። ነገር ግን ጥላቻን እንዲሽር የሚያደርገው «ፍቅር፣ኅዘን ርህራሄ» ነው። ለወዳጆቹ ብቻ የሚያዝን፣ ያለ በቂ ምክንያት ጠላት ብሎ በፈረጃቸው አካላት ላይ ደግሞ የአረመኔ ጥግ የሚሆን አካል «እጅግ በጣም አዛኝ» ሊሆን ቀርቶ «አዛኝ ነው» ሊባል አይገባውም። እዚህ ላይ ለአብነት ሂትለርን ላንሳ። ኢቫ ብራውን የተሰኘች እንስት ለእርሷ ትኩረት በመንፈጉ እራሷን ልታጠፋ ሞከረች። ታድያ በታሪክ ውስጥ ምድር ካስተናገደቻቸው ሰዎች ውስጥ በብዙዎች ዘንድ «እጅግ አረመኔ» የሚባለው ሰው እጅግ አዝኖላት ትኩረቱን ወደእርሷ ማድረግ ጀመረ። [ Speer, Albert (1971) [1969]. Inside the Third Reich . New York: Avon. ISBN 978-0-380-00071-5, p. 130] ይህም ብቻ ሳይሆን ሂትለር እጅግ የሚወዳቸውና የሚያዝንላቸው የቅርብ ሰዎችም ነበሩት። ታድያ ይህንን ብቻ ይዞ «ሂትለር እጅግ በጣም አዛኝ ርህሩህ ነው» ቢባል ስላቅ አይሆንምን?
ይህ በንዲህ እንዳለ አላህ እንኳንስ ክደውኛል ላላቸው አካላት ይቅርና ለመስሊሞችም እንኳን አዛኝነቱን አላሳየም። እውነት አላህ ለሙስሊሞች የሚያዝንላቸው ቢሆን ኖሮ በገሀነም እያስፈራራ፣ “ከሞት ወድያ ጥሩ ጥሩ ምግብ ትበላላችሁ፣ ከቆንጆ ሴቶች ጋር ወሲብ ትፈጽማላችሁ” እያለ እየደለለ ወደ ጦር ሜዳ ባልላካቸው ነበር።የሙሐመድ ተከታዮች አብዛኞቹ ድሀ የነበሩ እንደነበር ላነበበ ሰው « ከሞት በኋላ ምግብ ትበላላችሁ» የሚል ድለላ እጅግ ስሜት ይረብሻል።
“በጦርነት ላይ) መሞትንም ሳታገኙት በፊት በርግጥ የምትመኙት ነበራችሁ፡፡እናንተም የምትመለከቱ ስትኾኑ በርግጥ አያችሁት (ታዲያ ለምን ሸሻችሁ)።” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:153)
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ፡፡እናንተም የምትሰሙ ስትኾኑ ከርሱ አትሽሹ፡፡” የጦርዘረፋዎች ምዕራፍ (8:20)
“በዕውር ላይ (ከዘመቻ በመረቅቱ) ኃጢአት የለበትም፡፡ በአንካሳም ላይ ኃጢአት የለበትም፡፡ በበሽተኛም ላይ ኃጢአት የለበትም፡፡ አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዝ ሰው ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያገባዋል፡፡ የሚሸሸውንም ሰው አሳማሚውን ቅጣት ይቀጣዋል፡፡” አገር የመክፈት ምዕራፍ (48:17)
“ከአዕራቦች ወደ ኋላ ለቀሩት በላቸው፡- «የብርቱ ጭካኔ ባለቤት ወደኾኑ ሕዝቦች (ውጊያ) ወደፊት ትጠራላችሁ፡፡ ትጋደሏቸዋላችሁ፤ ወይም ይሰልማሉ፡፡ ብትታዘዙም አላህ መልካም ምንዳን ይሰጣችኋል፡፡ ከአሁን በፊት እንደሸሻችሁ ብትሸሹም አሳማሚን ቅጣት ይቀጣችኋል፡፡»” አገር የመክፈት ምዕራፍ ( 48:17)
“እነዚያን በአላህ መንገድ የተገደሉትን ሙታን አድርገህ አትገምታቸው፡፡ በእርግጥ እነርሱ እጌታቸው ዘንድ ሕያዋን ናቸው፤ ይመገባሉ፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:169)
“እነዚያ (ከትግል) የቀሩ ሲኾኑ ለወንድሞቻቸው ፡- «በታዘዙን ኖሮ ባልተገደሉ ነበር» ያሉ ናቸው፡፡ «እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ከነፍሶቻችሁ ላይ ሞትን ገፍትሩ»በላቸው፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:168)
“አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ፡፡ ብትሸሹም አላህ ከሓዲዎችን አይወድም» በላቸው፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:32)
“ከሞት ወይም ከመገደል ብትሸሹ መሸሻችሁ ፈጽሞ አይጠቅማችሁም፡፡ ያንጊዜም ጥቂትን እንጂ የምትጣቀሙ አትደረጉም በላቸው፡፡” የአሕዛብ ምዕራፍ (33:16)
“አላህ እነዚያን እነርሱ ልክ እንደ ተናሰ ግንብ የተሰለፉ ኾነው በመንገዱ (በሃይማኖቱ) የሚጋደሉትን ይወዳል፡፡” የሰልፍ ምዕራፍ (61:4)
“በአላህ እመኑ፡፡ ከመልክተኛውም ጋር ኾናችሁ ታገሉ፤ በማለት ምዕራፍ በተወረደች ጊዜ ከነሱ የሰፊ ሀብት ባለቤቶች የኾኑት (ለመቅረት) ፈቃድ ይጠይቁሃል፡፡ «ከተቀማጮቹ ጋርም እንኹን ተወን» ይሉሃል፡፡ በቤት ከሚቀሩት ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ በልቦቻቸውም ላይ (ዝገት) ታተመባቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ አያውቁም፡፡” የንስሐ ምዕራፍ ( 9:86-87)
እግዚአብሔር አምላክ በአዲስ ኪዳን አንድያ ልጁን ለኃጥያት ስርየት ይሆነን ዘንዳ ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። በዘመነ ብሉይ ሕይወታቸው ላለፉ ሰዎች ኹሉ እግዚአብሔር ለኃጢአታቸው ስርየትን ሰጥቷል። የክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ባሉበት ተሰብኮላቸዋል፦
“ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው።” 1ጴጥሮስ 3:18-19
በብሉይ ኪዳን እስራኤል የእግዚአብሔር መንግሥት ምልክት ትሆን ዘንድ በምድር ምሳሌ ነበረች። በክርስቶስ ኢየሱስ ያመንን፣ የዘላለም ሕይወት ቃል የተገባልን በእርሱም እርግጠኛ የሆንን ሰዎች በእምነት የማይመስሉንን ሰዎች በምድር ላይ ሕይወታቸውን በግፍ እንዲጠፋ አድርገን ይባስ ብሎም በእርሱም ሳንረካ ለዘላለም እንዲቀጡ አንሻም። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰበከውን ወንጌል አምነን የተቀበልን ሰዎች ሁሉን ማድረግ የሚችለው ፈጣሪ ሰዎችን ከሞት ወዲያ ባለ ምቾትና ልቅ ወሲብ እያባበለ ሌሎችን ወደ ማሠቃየትና መግደል ይመራል የሚል እምነት ፈፅሞ የለንም። አንድያ ልጁን ከሰጠን በኋላ “ነቢይ” በመላክ “አበረታታ፣አደፋፍር” እያለ ለጦርነትና ለእልቂት ሕዝብን ይጋብዛል የሚል ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። በዓለማዊ ሊቃውንት ትንታኔ መሰረት «ጤነኛ ግብረ ገብ» እያደገ፣ እየተሻሻለ ይመጣል እንጂ ወደኋላ ከቶ ሊመለስ አይችልም። ይህ ሐሳዊው ነቢይ ሙሐመድ ተከታዮቹ እየፈሩ አልዋጋ ሲሉት የተጠቀመበት ማታለያ ዘዴ መኾኑ ልቦና ካለው ሰው ሁሉ ሊሰወር የሚችል አይደለም።
ከዚህም ባሻገር በቁርአን የተጠቀሰው ለጂሀዳውያንና የኢስላም ገነት ለሚገቡ ሰዎች ሙሐመድ ቃል የገባው የምግብና የመጠጥ ዓይነት ለአሁን ዘመን ሰው ብዙም አጓጊ አይደለም። ሙዝ፣ ከተስኒም የተበረዘ ጠጅ፣ አጎበር ያለው አልጋ፣ የሚንቧቧ ውሀ፣ ቁርቁራን የመሳሰሉ የተለያዩ ዓይነት ፍራፍሬዎች፣ ከፍ የተደረገ ምንጣፍ፣ ጡተ-ጎቻማ ሴቶች፣ የተሞላ ብርጭቆ፣ አትክልት እና ወይን፣ ሰፋፊ የወርቅ ሳህን እና ኩባያዎች፣ ፈሳሽ ምንጭ፣ ወራጅ ወንዝ፣ የተደረደሩ መከዳዎች ወዘተ…
በኢስላም መንገድ የንፁኅንን ሕይወት የሚያጠፉና የእራሳቸውን የሚገብሩ አካላት ይህንን ቃል ተስፋ በማድረግ በሞታቸው ሰዓት እንኳ ፈገግታ እንደሚነበብባቸው ይነገራል። ይህንን ጉዳይ “ኢስላም ሰላም ነውን?” በሚል ርዕስ በሰፊው እንዳስሰዋለን። ሙስሊም ወገኖቻችንን እንዲሁም የኢስላም ሰባክያንን “ አትዘን፣ ጨክን፣ ለጦርነት አደፋፍር፣ ጫንቃዎቻቸውን በኀይል ምቱ፣ በጦርነት ወቅት ፈርታችሁ ከሸሻችሁ ገሃነም እከታችኋለሁ፣ አሰቃዩዋቸው፣ ወዘተ.” የሚልን አካል በምን ዓይነት መመዘኛ አዛኝ እንደሚሉ መጠየቅ እፈልጋለሁ።
“አንተ መልክተኛ ሆይ! እነዚያ በክሕደት የሚቻኮሉት ከእነዚያ ልቦቻቸው ያላመኑ ሲኾኑ በአፎቻቸው «አመንን» ካሉትና ከእነዚያም አይሁድ ከኾኑት ሲኾኑ አያሳዝኑህ…” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:176)
“… እነዚያም የተሰደዱ ከአገሮቻቸውም የተባረሩ በመንገዴም የተጠቁ የተጋደሉም የተገደሉም ክፉ ሥራዎቻቸውን ከእነርሱ በእርግጥ አብሳለሁ፡፡ በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በእርግጥ አገባቸዋለሁ፡፡ ከአላህ ዘንድ የኾነን ምንዳ (ይመነዳሉ)…” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:198)
“እነዚያም በክህደት የሚቻኮሉት አያሳዝኑህ፡፡ ከነርሱ ፈጽሞ አላህን በምንም አይጎዱምና፡፡ አላህ በመጨረሻይቱ ዓለም ለእነሱ ዕድልን ላያደርግ ይሻል፡፡ ለእነርሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:176)
“በአላህም መንገድ ተጋደል፡፡ ራስህን እንጅ ሌላን አትገደድም፡፡ ምእምናንንም (በመጋደል ላይ) አደፋፍር፡፡ አላህ የእነዚያን የካዱትን ኀይል ሊከለክል ይከጀላል፡፡ አላህም በኀይል በመያዙ የበረታ ቅጣቱም የጠነከረ ነው፡፡” (የሴቶቹ ምዕራፍ 4:84)
“አንተ ነቢዩ ሆይ! ምእምናንን በመዋጋት ላይ አደፋፍራቸው፡፡ ከእናንተ ውስጥ ሃያ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ፡፡ከእናንተም መቶ ቢኖሩ ከእነዚያ ከካዱት እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች ስለኾኑ ሺህን ያሸንፋሉ።” የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ ( 8:65 )
“አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡” የንስሐ ምዕራፍ (9:73)
“ተጋደሉዋቸው፡፡ አላህ በእጆቻችሁ ያሰቃያቸዋል፡፡ያዋርዳቸዋልም፡፡ በእነሱም ላይ ይረዳችኋል፡፡የምእምናን ሕዝቦችንም ልቦች ያሽራል፡፡ “ የንስሐ ምዕራፍ ( 9:14)
“እነዚያንም ከእናንተ ውስጥ (ዝሙትን) የሚሠሩዋትን አሰቃዩዋቸው…” የሴቶቹ ምዕራፍ (4:16)
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ታገሱ ተበራቱም፡፡ (በጦር ኬላ ላይ) ተሰለፉም፡፡ትድኑም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:200)
“ከዚያም «ከራሱ በላይ ከፈላ ውሃ ስቃይ አንቧቡበት፡፡»…” የጭስ ምዕራፍ (44:48)
“ሁከት እስከማይገኝና ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሉዋቸው፡፡ ቢከለክሉም ወሰንን ማለፍ፤ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም (ወሰን አትለፉባቸው)፡፡” የላሚቷ ምዕራፍ (2:193)
“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው ፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና ፡፡” የንስሐ ምዕራፍ (9:5 )
“መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው ፡፡” የንስሐ ምዕራፍ (9:29)
“አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፡፡ ክርስቲያኖችም አል-መሲሕህ ልጅ ነው አሉ፡፡ ይህ በአፎቻቸው (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፡፡የእነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፡፡ አላህ ያጥፋቸው፡፡(ከእውነት) እንዴት ይመለሳሉ!” የንስሐ ምዕራፍ (9:30)
“ከዚያም አላህ እርጋታውን በመልክተኛውና በምእምናኖቹ ላይ አወረደ፡፡ ያላያችኋቸውንም ሰራዊት አወረደ፡፡ እነዚያን የካዱትንም በመገደልና በመማረክ አሰቃየ፡፡ ይህም የከሓዲያን ፍዳ ነው፡፡” የንስሐ ምዕራፍ (9:26)
“እናንተም አሸናፊዎቹ ስትኾኑ አላህ ከእናንተ ጋር ሲሆን አትድከሙ፡፡ ወደ ዕርቅም አትጥሩ፡፡ ሥራዎቻችሁንም ፈጽሞ አያጎድልባችሁም፡፡” የሙሐመድ ምዕራፍ (47:35)
እስልምናን ያልተቀበሉ ምን አጠፉ?
ሙሐመድ ባደረበት ፀረ-ማሕበረሰብ የስብዕና እክል ካልሆነ በስተቀር እስልምናን ያልተቀበሉ ሰዎች ምንም ጥፋት የለባቸውም። እንደ ሙሐመድ አስተምህሮ አላህ አስቀድሞ እንዳያምኑ አድርጓቸዋል፦
“እነዚያ የካዱት (ሰዎች) ብታስፈራራቸውም ባታስፈራራቸውም በነርሱ ላይ እኩል ነው፤ አያምኑም፡፡ አላህ በልቦቻቸው ላይ በመስሚያቸውም ላይ አትሞባቸዋል፤ በዓይኖቻቸውም ላይ መሸፈኛ አልለ፤ ለነሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡” የላሚቷ ምዕራፍ (2:6-7)
እዚህ ጋር ሙስሊም ወገኖቻችን ከጭፍን ጥላቻ ተቆጥበው እንዲያስተውሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ። በእስልምና ላይ ስለማተኩር ንፅፅራዊ ይዘት ያላቸውንም ኾነ የሌላቸው በርካታ ኢስላማዊ መጽሐፍትን ለማንበብ ዕድሉን አግኝቻሁ። ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ ለማለት እስከሚያስደፍር ድረስ ሙስሊም ስላልሆኑ አካላት ወደር የማይገኝለት ጥላቻን ይሰብካሉ። ለክርስቲያኖች አዝነው፣ ክርስትያኖችን ወደው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እስልምናን የሚሰብኩ የሉም ባልልም በርካቶች ሰባክያን በፀጉራቸው ቁጥር ልክ ጥላቻ ይዘው “እንዴት ተደፈርን” በሚል የጋለ የጥላቻ ስሜት ከልክ በላይ ያንቋሽሹናል። ምናልባት በእነሱ ጽሑፎችና ንግግሮች ውስጥ የተጠቀስነው አካላት ጭራቅ እንጂ ሰዎች አንመስልም።
ቁርአንም ቢሆን እንዲህ በሚል ሙስሊም ያልሆኑትን ይስላቸዋል:-
“ከሚንቀሳቀሱ እንስሳዎች ሁሉ አላህ ዘንድ ይበልጥ ክፉዎቹ እነዚያ ዘወትር የካዱት ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ አያምኑም፡፡” የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ (8:55)
“«የማስፈራራችሁ በተወረደልኝ ብቻ ነው፡፡ ግን ደንቆሮዎች በሚስፈራሩ ጊዜ ጥሪን አይሰሙም » በላቸው፡፡” የነቢያት ምዕራፍ (21:45)
“ከተንቀሳቃሾች ሁሉ አላህ ዘንድ መጥፎ ተንኮለኞች እነዚያ የማያውቁት፣ ደንቆሮዎቹ፣ ዲዳዎቹ ናቸው፡፡” የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ (8:22)
“(እነሱ) ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አይመለሱም፡፡” የላሚቷ ምዕራፍ (2:18)
በዓለማዊ መተዳደርያ ሕግም ቢኾን የሙሐመድ ሐሳብ ያልተመቸው ሰው ሙሐመድን ያለመቀበል ሙሉ መብት አለው። ‘’ጥያቄም’’ ኾነ ‘’ኂስም” የመብት አንዱ አካል ነው። ሙስሊም ሰባክያን በዚህ ከሚገባው በላይ ለምን ስሜታዊ እንደሚሆኑ በእውነቱ ግራ የሚገባ ጉዳይ ነው። ሙሐመድ የተናገረው ትክክል ከሆነ ዘላለማዊ እረፍት መስሊሞች ሊያገኙ፣ ሙስሊም ያልሆኑት ደግሞ አላህ ለዘላለም ሊቀጣቸው በቁርኣን ሰፍሯል። ታድያ ሙስሊሞች በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ከሆኑ እዚህ ምድር ላይ ማን ታጋሽና ሆደ ሰፊ መሆን ነበረበት? ዛሬ ላይ እውነት ስለተነገረ ብቻ በየ አደባባዩ «ነቢያችን ተሰደቡ» እያሉ የ«በተገኘበት ይገደል» ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ ሰባክያን ስናይ እምነታቸው ላይ ምንም መተማመን እንደሌለ በቀላሉ እንረዳለን። ይህ ጉዳይ ድንገት ዛሬ ላይ የተከሰተ ሳይሆን ከሙሐመድ አንስቶ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው። እስልምናን ተችተው፣ እስልምናን ለቀው በሙሐመድ ትዕዛዝ ከተገደሉ አካላት የተወሰኑትን ብቻ በክፍል ሁለት አስቃኛችኋለሁ።
በክርስትና ገሃነም ሰዎች እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የመዳን መንገድ ባለመቀበል የሚመርጡት ምርጫ እንጂ በምድር ለተጠፋ ጥፋት ቅጣት ነው ተብሎ አይታመንም። «ክርስትና ምርጫቸው» ያልሆኑ ሰዎች ምድር ላይ ያሻቸውን ማድረግ ይችላሉ። እግዚአብሔር አምላክም ከጥፋታቸው ይመለሱ ዘንድ ይታገሳቸዋል።
“ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። “ (2ጴጥሮስ 3:9)
የቁርአን ሐሳብ ግን በተቃራኒው ኾኖ እናገኘዋለን፦
“እስከጊዜያቸውም ድረስ በጥምመታቸው ውስጥ ተዋቸው፡፡ ከገንዘብና ከልጆች በእርሱ የምንጨምርላቸውን ያስባሉን? በበጎ ነገሮች የምንቻኮልላቸው መኾንን (ያስባሉን) አይደለም፤ (ለማዘንጋት መኾኑን) አያውቁም፡፡” የምእመናን ምዕራፍ (23:54-56)
“እነዚያ የካዱት ሰዎች እነርሱን ማዘግየታችንን ለነፍሶቻቸው ደግ ነገር ነው ብለው አያስቡ፡፡ እነርሱን የምናዘገያቸው ኃጢኣትን እንዲጨምሩ ብቻ ነው፡፡ ለነሱም አዋራጅ ስቃይ አላቸው፡፡” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ (3:178)
አንድ የቁርአን ክፍል በማከል ጽሑፌን ልደምድም፦
“ቅርቢቱ ሕይወት ጫወታና ዛዛታ ብቻ ናት፡፡ ብታምኑም ብትጠነቀቁም ምንዳዎቻችሁን ይሰጣችኋል፡፡ ገንዘቦቻችሁንም (ሁሉ) አይጠይቃችሁም፡፡” የሙሐመድ ምዕራፍ (47:36)
እንደ እውነቱ ከሆነ የቁርአን ደራሲ ይህንን የተናገረው ተከታዮቹ እንዲዘምቱለት ፈልጎ ስለነበር ነው። ከላይ ባሰመርኩበት ሐሳብ ብቻ እስማማለሁ። ቅርቢቱ ዓለም እጅግ አጭር ናት። በዚህች አጭር ሕይወታቸው ላይ በደል ፈፅሞ ዘላለምም በሰዎቹ ላይ በደል እንዲፈፀምባቸው ከመጠበቅ በላይ ምን ዓይነት ጭካኔ ይኖር ይኾን? ሙስሊም ያልሆኑ አካላት የተዋረዱ ሆነው ግብርን ለሙስሊሞች እስኪከፍሉ ሙስሊሞች እንዲዋጉዋቸው ቁርአን ያዛል። በእስልምና ጥላ ስር በዚሚ ሕግ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች ከኗሪ በታች የተደረጉበትን ታሪክ የሚያወሳ አጠር ያለ ትንታኔ እዚህ ድረ-ገጽ ላይ ተጽፏል። እውነተኛውን የእስልምና መልክ ለመረዳት ከዚህ ጽሑፍ በመቀጠል እርሱን እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ። ሙስሊም ወገኖቻችን በዚህ ጉዳይ ሐሳብ እንዲሰጡበት እያበረታታሁ በክፍል ሁለት እስከምንገናኝ በዚሁ እሰናበታለሁ።