ገዢው ጌታ ኢየሱስ

ገዢው ጌታ ኢየሱስ

ወንድም ሚናስ


ቅዱስ መንፈሱ በዅላችን ላይ ለዘለዓለም ዐድሮ  ይኑርና፣ ኅብስተ ሕይወት፣  ወልደ ልዑል፣ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ፈጣሬ ዓለማት፣ እግዚአ ኵሉ ፍጥረት መኾኑ፣ በብሉይ እና በሐዲሳት እንዲሁም በሐዋርያት አበው የጸና መሠረታዊ የክርስትና ሰንደቅ ነው። ይህንን አስደናቂ እውነት ከሚያስተጋቡ የሐዲሳት መጻሕፍት መኻከል አንዱ፣ የይሁዳ መልእክት ተጠቃሽ ነው። ይህ መልእክት ከሌሎች የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዐጭሩ ቢኾንም፣ የክርስቶስን አምላክነት የሚያሳዩ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ አንድምታ ያላቸው ምንባባት በስፋት ይንጸባረቅበታል፤ ከእነዚህ ቊጥሮች መኻከል ቍጥር አራትን ብንወስድ፦ “…ርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው” ይላል። ሐዋርያው ይሁዳ በዚህ ኀይለ ቃል ውስጥ የተጠቀመው የጽርእ ቅጽል δεσπότην “ዴስፖቴን” የሚል ሲኾን፣ δεσπότης “ዴስፖቴስ” ከሚል ዘር  የወጣ ነው፤ ይህ ቅጽል በዐማርኛ ተርጒሚያን “ልዑል ገዢ”፣ “ገዢ”፣ “ንጉሥ”፣ ተብሎ የተተረጐመው ሲኾን፣ ሐዋርያው መልእክቱን በጻፈበት በሮማውያን ባሕልና ዕሳቤ ውስጥ ትልቅ ትርጒም የሚሰጠው ነው፤ ይኸውም በዚህ ቅጽል የሚጠራ ሰው  ያለውን እጅግ የላቀ የሥልጣን ደረጃ የሚያመለክት ነው፤ ለምሳሌ እንኳን ብንወስድ በዚህ ቅጽል የሚጠራው  ግለሰብ የአንድ ቤተሰብ አባወራ ቢኾን፣ ከሥልጣኑ የተነሣ ፣ የአብራኩ ክፋይ የኾነው ልጁ፣ የቱንም ያኽል ትልቅ እና ራሱን የቻለ ቢኾንም፣ δεσπότης “ዴስፖቴስ”  የተባለው አባት ደስ ካልተሰኘበት እስከ መግደል የደረሰ ሙሉ ሥልጣን አለው[1]።  ይልቁንም ይህ  δεσπότης “ዴስፖቴስ”  የሚለው ቅጽል፣ በቅዱሳት መጻሕፍት “ጌታ” (ጽርእ: κύριος “ኩሪዮስ”) ከሚለው ሌላ ቅጽል ጋር ተያይዞ የቀረበ እንደኾነ እውነተኛውን አምላከ እስራኤልን ብቻ ያመለክታል። በማሳያነት የሚከተሉትን ጥቅሶች ከሰባ ሊቃናት ትርጒም እንመልከት

አብራምም፣ “ገዢ ጌታ ሆይ (Δέσποτα Κύριε)፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለኹ?” አለ።”ዘፍ.15፥8

“እኔም፣ “ጌታ ገዢ ሆይ (δέσποτα Κύριε)   ፤ ሰይፍ ዐንገታቸው ላይ ተቃጥቶ ሳለ፣ ‘ሰላም ይኾንላችዃል’ ብለኽ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ለምን እጅግ አታለልኽ?” አልኹ።” ኤር.4፥10

“ስለዚህ የሠራዊት ገዢ (δεσπότης)  ጌታ (Κύριος) እንዲህ ይላል፦ ለእስራኤል ኀያላን ወዮላቸው። ቍጣዬ በጠላቶቼ ላይ አይወገድምና፥ በጠላቶቼም ላይ ፍርድን አደርጋለኹ” ኢሳ.1፥24

ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ በመልእክቱ፣ “ገዢ እና ጌታ” የሚሉትን ኹለት ቅጽሎች ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መጠቀሙ፣ መሲሑ ኢየሱስ፣ ያህዌ መኾኑን ካለ አንዳች ጥርጣሬ እየገለጸ መኾኑ ግልጽ ቢኾንም፣ አንድ ሙስሊም ጸሓፊ በቅርቡ ይህ ቍጥር የኢየሱስን አምላክነት አያሳይም ብሎ ዐሳቡን ያቀርባል፤ እኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ወድልዋኒክሙ ሀልዉ በኵሉ ጊዜ ታውሥእዎሙ ቃለ ለእለ ይሴአልክሙ በእንተ ዛቲ ተስፋክሙ”(1ጴጥ.3፥15)  ብሎ ባስቀመጠልን ሐዋርያዊ ትእዛዝ  መሠረት ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥላለን፤ አስቀድመን ግን የሙስሊሙን ጸሓፊ ሙግት እንዲህ እናቀርባለን፦

❝….”ብቻውን የሆነ ገዥ” የተባለው አብ ይሁዳ ላይ “ብቻውን ያለውን ጌታ” ተብሏል፦

ይሁዳ 1፥4 ብቻውን ያለውን ጌታ እና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። καὶ τὸν μόνον Δεσπότην καὶ Κύριον ἡμῶν Ἰησοῦν Χριστὸν ἀρνούμενοι.

“ዴስፖቴስ” δεσπότης ማለት “ጌታ” ማለት ሲሆን በግሪክ ሰፕቱአጀንት “ያህዌህ” יְהוָ֣ה የሚለው ቴትራግራማቶን ተክቶ የመጣ ነው…ብቻውን ያለውን ጌታ” የተባለው ኢየሱስ ስላልሆነ ኮዴክስ ቤዛይ ላይ፦ “ብቻውን ያለውን ጌታ አምላክ” በማለት አብ ለማመልከት የተቀመጠው፦

ይሁዳ 1፥4 ብቻውን ያለውን ጌታ አምላክ እና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። καὶ τὸν μόνον δεσπότην θεὸν καὶ κύριον ἡμῶν Ἰησοῦν χριστὸν ἀρνούμενοι.

“ቴዎን” θεὸν የሚለውን ቃል አትለፉት! ለዚያ ነው በ 1611 ድኅረ ልደት በታተመው ቅጂ The King James Version (KJV) ላይ “and denying the only Lord God, and our Lord Jesus Christ” ብለው ያስቀመጡት። “ዴስፖቴን ቴዎን” δεσπότην θεὸν እና “ኩርዮን ቶን ቴዎን” ማለት “ጌታ አምላክ” ማለት ሲሆን “ያህዌህ ኤሎሂም” የሚለውን ተክቶ የመጣ ነው።…ስለዚህ በቀላሉ “ብቻውን ያለውን ያህዌህ አምላክ እና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ” ማለት ነው። ይህን ከተረዳን ግራንቪል ሻርፕ የተሰኘ የግሪክ ስድስት ሰዋስው መርሕ መካከል አንደኛ መርሕ ላይ፦ “ሁለት ነጠላ የማዕረግ ስሞች “እና” በሚል መስተጻምር ተያይዘው ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው እና የመጀመሪያው የማዕረግ ስም ከፊቱ ላይ ውስን መስተአምር ካለ በተቃራኒው ሁለተኛው የማዕረግ ስም ከፊቱ ላይ ውስን መስተአምር ከሌለ የሚያመለክተው አንድ ማንነትን ነው” የሚል ነው።

በዚህ ሕግ ይሁዳ 1፥4 የመጀመሪያው የማዕረግ ስም “ዴስፖቴን” δεσπότην ሲሆን ከፊቱ ላይ “ቶን” τὸν የሚል ውስን መስተአምር አለው፥ በተቃራኒው ሁለተኛው የማዕረግ ስም ደግሞ “ኩርዮን” Κύριον ሲሆን ከፊቱ ላይ “ቶን” τὸν የሚል ውስን መስተአምር የለውም። “ዴስፖቴን” እና “ኩርዮን” በሚል ሁለት የማዕረግ ስሞች መካከል “ካይ” καὶ የሚል መስጻምር አለ፥ ቅሉ ግን ከካይ በፊት ያለው “ዴስፖቴን” ሙያው ተሳቢ ሙያ ሲሆን ከካይ በኃላ ያለው “ኩርዮን” ደግሞ “ሄሞን” ἡμῶν ማለትም “የእኛ” የሚል አገናዛቢ ሙያ ስላለ ሁለት የተለያየ ሙያዎች ናቸው። ስለዚህ “ጌታ” እና “ጌታችን” ሁለት የተለያየ ሙያ ሆነው ስለመጡ “ብቻውን ያለውን ጌታ አምላክ” የተባለው አብ እና ጌታችን የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ለየቅል የሆኑ ምንነት እና ማንነት ናቸው።❞

ከላይ የሰፈረው የሙስሊሙ ጸሓፊ ዐሳብ ብዙ ስሕተቶችን የሸከፈ መኾኑን ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

(1) ቀዳሚ የጸሓፊው ስሕተት፣ “ብቻውን ያለውን ጌታ” የተባለው ኢየሱስ ስላልኾነ ኮዴክስ ቤዛይ “ብቻውን ያለውን ጌታ አምላክ” በማለት አብ ለማመልከት ይጠቀማል ማለቱ ነው። ኮዴክስ ቤዛይ በመባል የሚታወቀውና፣ በዐምስተኛው ወይም በስድተኛው ምእተ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እንደተጻፈ የሚገመተው፣ በጽርእ እና ሮማይስጥ ቋንቋ የተጻፈው የብራና ጽሑፍ ቀደማይ ከኾኑትና “ርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው” ከሚሉት ከኮዴክስ ቫቲካነስ እና ከኮዴክስ ሳይናቲከስ፣ ጋር ሲወዳደር በቀዳሚነት ኾነ በጥራት አይነጻጸርም፤ ሙስሊሙ ጸሓፊ ከላይ ያስቀመጠው ሐረግ፣ የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኝበት ምክንያት ኬ.ጄ.ቪ  በ16ኛው ምእተ ዓመት በታተመውና Novum Instrumentum ከተባለው፣ የቤዛንታይን ቅጂ ስለተተረጐመ ነው፤ ይህ የቤዛንታይን ቅጂ ደግሞ ምድባቸው ከአሌክሳንድርያው ከኾኑት ከሳይናቲከስና ከቫቲካነስ ጋር የማይወዳደር ነው። ስለዚህ ትኽክለኛው ሐረግ ሊኾን የሚችለው፣ ቀዳማይ ጽሑፈ እድ እንደዘገቡት “ርሱ ብቻ  ገዣችንና ጌታችን የኾነውን” የሚል ንባብ ሲኾን፣ ርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

(2). በኹለተኛ ደረጃ ጸሓፊው ያቀረበው ሙግት፣ “ርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የኾነውን”  የሚለውን የጽርእ ትርጒም በሚከተሉ ጽሑፈ እድ ላይ በመጽናት ወደ  ግራንቪል ሻርፕን ሕግ ዐይኑን ያዞራል፤  በርግጥ ሙስሊሙ ጸሓፊ እንዳለው፣ በግራንቪል ሻርፕ ሕግ  (1).ኹለት ነጠላ የኾኑ ነገር ግን፣ (2).ስመ ተጸውዖን(የመጠሪያ ስም) ያልኾኑ፣ (3). “እና”(καὶ “ካይ”) በሚል የጽርእ አያያዥ ከተጣመሩ (4). በ “እና” የተያያዙት ቃላት ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው (5). በመጀመሪያ ስም ላይ ውስን መስተኣምር ኖሮ በኹለተኛው ስም ላይ ከሌለ ኹለቱም መስተኣምር ከሌላ ኹለቱም የማዕረግ ስሞች የሚያመለክቱት አንድን አካል ነው። በዚህ የሰዋስው ሕግ መሠረት፣ ይሁዳ 1፥4 ስንመለከት Δεσπότην  ከሚለው ቅጽል በፊት τὸν “ቶን” የሚል ተሳቢ፣ ነጠላ፣ የጽርእ መስተኣምር ሲኖር፣ “እና” (καὶ “ካይ”) ከሚለው አያያዥ በዃላ ያለው በሙያ ኾነ በቍጥር ከ Δεσπότην “ዴስፖቴን” ጋር ስምም የኾነው፣ Κύριον “ኩሪዮን” ላይ ግን ምንም ዐይነት መስተኣምር ስለሌለ፣ “ገዢ” እንዲሁም “ጌታ” የተባለው የክፍሉ ቀጥተኛ ተሳቢ (direct Object)  ኢየሱስ ክርስቶስ(Ἰησοῦν Χριστὸν) ነው። ሙስሊሙ ጸሓፊ ይህንን ግልጽ የኾነ የሰዋስው አወቃቀር ውድቅ ለማድረግ ማቅረብ የነበረበት ስሙር ሙግት፣ “እና” (ጽርእ: καὶ “ካይ”) ካለ በዃላ ያለው ቅጽል ከቀድሞ ቅጽል ጋር በሙያ ወይም በቊጥር አንድ አለመኾናቸውን በማሳየት ነበር ፤ ኾኖም ግን ጸሓፊው ሙግቱ መሠረት ያደረገው “እና” (ጽርእ: καὶ “ካይ”) ካለ በዃላ ያለው ቅጽል ላይ ሳይኾን፣ ይሁዳ ይህ “ልዑል ገዢ” እና “ጌታ” የተባለው አካልን “የእኛ ልዑል እና ጌታም ነው” የሚለውን ዐሳብ ለመግለጽ የተጠቀመውን ἡμῶν “ሄሞን” የሚለው አንደኛ ሰብኣዊ መደብን ነው ትርጒሙም “የእኛ” ማለት ነው ፤ ይህ ደግሞ ሊያስኼድ የማይችል ሙግት ነው ምክንያቱም አስቀድመን እንዳልነው የጸሓፊው ሙግት መመሥረት የነበረበት “እና” (ጽርእ: καὶ “ካይ”) ካለ በዃላ ባለው ቅጽል፣ ሰዋስዋዊ አገባብ ላይ እንጂ፣ ከ  “እና” በራቁ ቃላት ላይ አይደለም፤ ሌላው ሙስሊሙ ጸሓፊ እንዲሁ በተለምዶ ግራንቪል ሻርፕ ሕግ ሲባል ከመስማት በዘለለ የሊቁን መጽሐፍ ገልጦ ያነበበ አይመስለንም፤  ምክንያቱም ለሙግቱ ይረዳው ዘንድ የጠቀሰው ግራንቪል ሻርፕ ራሱ፣ አስቀድመን ለገለጽነው የሰዋስዋዊ ሐቲት(Grammatical Exegesis)  በማሳያነት ካቀረባቸው ጥቅሶች መኻከል አንዱ፣ ይሁዳ 1፥4 ነው። ሊቁ ግራንቪል ሻርፕ በመጽሐፉ ላይ ይሁዳ 1፥4 ላይ “ልዑል ገዢ” እና “ጌታ” (Δεσπότην καὶ Κύριον) የተባለው አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ይኸውም በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደሚያመለክት በግልጽ በመናገር ነበር። በአጠቃላይ የጌታ ሐዋርያ ይሁዳ ዋናው መልእክት፣ መለኮት የኾነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሚክዱ ሰዎች እንድንጠበቅ ነው፤ የዚህ ጽሑፍም ዋና መልእክት ይኸው ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነው ከሚል ባዕድ ትምህርት ተጠበቁ! ጸጋው ይደግፈን!


[1] Ann Shelton, As the Romans Did: ገጽ 17

[2] ግራንቪል ሻርፕ ይህንን የሰዋስው መርሕ ያቀረበበት የመጽሐፉ ርእስ “Remarks Of The Use Of Definite Article in The Greek Text of New Testament, Containing Many New Proofs of the divinity of Christ, from passages Which are Wrongly Translated the Common English Version” ይሰኛል።


መሲሁ ኢየሱስ