ኢየሱስ አብ ነውን? ክፍል ሁለት

ኢየሱስ አብ ነውን?

ወንድም ዳዊት


ክፍል ፪

  “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት   
              ተገልጦ ይኖራልና፤”
        (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥9)

የሰባሊዮሳውያን (በተለምዶ Only Jesus) አማኞች ይህንን እምነታቸውን ለማረጋገጥና ሥላሴን ለመቃወም የሚጠቅሱት እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች እያጮሁ የሚጠቀሙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። እንደነርሱ አባባል ኢየሱስ አብ ለራሱ ማደሪያ ያዘጋጀው ሥጋ ነው፤ መለኮት የሆነው አብ ደግሞ በዚህ ሥጋ ውስጥ ማደሩን ቆላስይስ 2፥9 ስለሚናገር ኢየሱስ አብ ነው። ይህ ሙግታቸው ርዕቱ ሙግት ነውን? በማስከተል የምንፈትሸው ይሆናል።

አንደኛ፦ እነዚህ ወገኖች የሚገጥማቸው ቀዳሚው ችግር ኢየሱስ አብ ለማደሪያው ያዘጋጀው ሥጋ ነው የሚለው አቋማቸው በጥቅሱ ውስጥ የሌለ መሠረት ቢስ ፈጠራ ሆኖ መገኘቱ ነው። በክፍሉም ሆነ በሌላ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብ ለማደሪያው የሚሆን ሥጋ አዘጋጀ የሚል ቃል የለም። ኢየሱስ እነርሱ እንደሚሉት “የተዘጋጀ ሥጋ” ከሆነ አብ በውስጡ ማደሩ ኢየሱስን አብ አያደርገውም፤ የእግዚአብሔር ልጅም አያደርገውም፤ ከዚያ ይልቅ “የአብ ሥጋ” ነው ሊባል የሚችለው። ይህ ደግሞ የለየለት አራጥቃ (ኑፋቄ) ነው።

ሁለተኛ፦  የቆላስይስ 2፥9 መልዕክት ተደራሲያን እነማን እንደ ሆኑ ዘንግተዋል። እንደ ሁል ጊዜው የተጠቀሙት ሥነ-አፈታት ምክንያታዊነት የጎደለውና አውዳዊ ስርዓቱን ያልተከተ ነው። ይህንን ጥቅስ በዘመኑ ከነበሩት አስተምህሮዎች አንጻር ማየቱ ከተሳሳተ ትርጓሜ ታቅበን ወደ እውነት እንድንቀርብ ይረዳናል። በአጭር ቃል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልዕክት የጻፈው ኖስቲሲዝም በመባል የሚታወቀውን ኑፋቄያዊ ትምህርት ለማጋለጥ በማሰብ ነበር። ኖስቲክ (Gnostic) የሚለው ቃል “ዕውቀት” የሚል ትርጉም ካለው ኖሲስ (Gnosis) ከሚል የግሪክ ቃል የተዋቀረ ነው፤ ይህንንም ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ሰው ሄነሪ ሞር የተሰኘ በ17ኛዎ ክፍል ዘመን የኖረ ሰው ነበር[1]፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከክርስትና የሚለዩዋቸው ዋና ዋና ትምህርቶቻቸው ከታች የተዘረዘሩት ናቸው፡-

  • የብሉይ ኪዳን አምላክ ከአዲስ ኪዳን አምላክ የተለየ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አምላክ ክፉና ውሱን ሲሆን የአዲስ ኪዳን አምላክ ሁሉን ቻይ ነው፡፡
  • ፍጥረት የተፈጠረው በሶፍያ (ጥበብ) ውድቀት ምክንያት ነው፡፡
  • ቁስ የተባለ ሁሉ ክፉ ነው፡፡
  • ኢየሱስ በሥጋ አልመጣም፣ በመስቀል ላይ አልሞተም፣ ትክክለኛው ኢየሱስ መንፈስ ነው፡፡
  • የመንፈስ ትንሣኤ እንጂ የሥጋ ትንሣኤ የለም፡፡[2]

ስለእነዚህ ቡድኖች እምነት ይህን ካየን ዘንዳ የሐዋርያው ጳውሎስን መልዕክት ዋና ሐሳብ መረዳት እንችላለን ማለት ነው።

እነዚህ ቡድኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍፁም ሰውነት አይቀበሉም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰውነት አለመቀበል ስህተት መሆኑን ለማመልከት ሐዋርያው “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” የሚል ምላሽ መስጠቱ ምን ትርጉም እንዳለው ግልጽ ይሆንልናል (ቆላስይስ 2፥9)። ስለዚህ ሐዋሪያው “ቁስ አካል ሁሉ እርኩስ ነው ኢየሱስ በሚታይ በሚዳደሰስ አካል አልተገለጠም፤ በስቅለቱም ጊዜ መንፈስ ነበር” የሚል ስሁት አረዳድ ያላቸው ሰዎች ስለነበሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆን በመግለጽ በዘመኑ የነበረውን ምንፍቅና እያወገዘ እንጂ የዘመናችን ሰባልዮሳውያን እንደሚሉት “ኢየሱስ አብ ነው” እያለ እንዳልሆነ እንረዳለን ማለት ነው።[3]

ሦስተኛ፦  የሰባሊዮሳውያን አማኞች ግድፈት “የመለኮት ሙላት” የሚለውን ቃል በተሳሳተ መልኩ “አብ” ብለው መተርጎማቸው ነው። የመለኮት ሙላት የሚለው ቃል በምንም መንገድ አብ ተብሎ አይተረጎምም፣ ቃሉ Θεότητος (“ቴዎቴቶስ) ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ በሊቃውንት ዘንድ የአምላክነት ባሕርይ ወይም “ግጻዌ መለኮት” ማለት ነው።[4] በአዲስ ኪዳናችንም ቃሉ አምላካዊ ባሕርይን ለማሳየት እንደገባ ማየት እንችላለን። ስለዚህ እኛም የኢየሱስን መለኮታዊነት በዚህ ቃል መሠረት እናምናለን። የክፍሉን ትርጓሜ መሠረት አድርገን ከሄድን “የመለኮት ሙላት” የሚለውን አብ ወይም በግሪኩ  (ፓቴር) በሚለው ቃል ተክቶ መተርጎም ከሰዋሰው አወቃቀሩ ጋር የእጅ ስንዝር ያህል እንኳ አያስኬደንም። የቃሉ ትርጉም ኢየሱስ ከአምላካዊ ባሕርያት የጎደለ ባሕርይ እንደሌለውና ፍጹም አምላክ መሆኑን የሚገልጽ እንጂ በአብ የተሞላ ሥጋ መሆኑን የሚገልጽ አይደለም። እግዚአብሔር አብ መለኮታዊ ባሕርይ ሁሉ ያለው መለኮት የሆነ ማንነት እንጂ መለኮታዊ ባሕርይ አይደለም። እርሱ የመለኮታዊ ባሕርይ ባለቤት የሆነ ማንነት ነው። ለምሳሌ አንድን ሰው ሰው የሚያደርገው ሰብዓዊ ባሕርያት ሁሉ ያለው መሆኑ ነው። ስለዚህ ሰው ሰዋዊ ባሕርያት ያሉት ቅዋሜ ማንነት እንጂ ራሱ ሰዋዊ ባሕርይ አይደለም። ልክ እንደዚሁ አብም መለኮታዊ ባሕርያት ሁሉ ያሉት መለኮት የሆነ ማንነት እንጂ ባሕርይ አይደለም። ኢየሱስን በአብ የተሞላ ሥጋ አድርጎ የሚረዳው የሰባልዮሳውያን ኑፋቄ አብን ማንነት ነስቶ ባሕርይ የሚያደርግ ዓይን ያወጣ ክህደት ነው።

አራተኛ፦ “በሰውነት” የሚለውን ቃል በተንሻፈፈ መልኩ መረዳታቸው ወደ ምንፍቅና ወስዷቸዋል። በመጀመሪያ ሰውነት የሚለው ቃል bodily, physically የሚል ትርጉም እንጂ (in the flesh) የሚል ትርጉም የለውም። ስለዚህ አብ ባዘጋጀው ሥጋ ውስጥ አደረ የሚል ትርጉም ለመስጠት ትክክለኛው ቃል አይደለም። ስለዚህ ውስጥ ተብሎ የማይተረጎም ከሆነ ውስጥ ብለው ለምን ይተረጉማሉ? ይህ በቃሉ ላይ የመጨመር ከባድ ድፍረት ነው።
    
በመጨረሻም ቆላስይስ 2፥9ን በትኩረት ስንመለከት ኢየሱስ በሰዎች ዓይን የማይታየውን መለኮታዊ ማንነት በሰዎች ሊታይና ሊዳሰስ በሚችል ፍጹም ሰውነት የያዘ መለኮታዊ አካል (ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው) መሆኑን የሚያሳይ ክፍል ነው። ስለዚህ ከላይ በትንታኔ እንዳየነው የቆላስይስ መልዕክት ኢየሱስ አብ ነው እንድንል የሚያስችል የነፋስ መግቢያ ክፍተት እንኳ አይሰጠንም። ኢየሱስ የአብ ልጅ እንጂ የራሱ ልጅ አይደለም፤ አብም የኢየሱስ አባት እንጂ የራሱ አባት አይደለም፤ ስለዚህ አብና ኢየሱስ ሁለት ማንነቶች ናቸው።

ይቀጥላል


ማጣቀሻዎች

1] Doniger, W. (2008, April 3). Britannica Encyclopedia of World Religions. p. 380.

2] Geisler, N. L. (1999). Baker Encyclopedia of Christian Apologetics. p. 504.

3] Arnold, C. (2014). The Colossian Syncretism: The Interface Between Christianity and Folk Belief at Colossae. Wipf and Stock.

4] Joseph Thayer Greek English Lexicon. p. 288


መልስ ለሰባልዮሳውያን