አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ማንነት ናቸውን? ለሰባልዮሳውያን ቅጥፈት ምላሽ

አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ማንነት ናቸውን?

ለሰባልዮሳውያን ቅጥፈት ምላሽ


ይሁዲ፣ ክርስትናና እስልምናን የመሳሰሉ አሃዳውያን ሃይማኖታትን የሚያስማማቸው አንድ ጉዳይ ቢኖር የአምላክ አንድነት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊውና ታሪካዊው ክርስትና ስለ እግዚአብሔር አንድነት ያለው አስተምህሮ እግዚአብሔር ሥላሴ ወይም አንድ መለኮት በሦስት ማንነቶች የሚል ነው። ይህ አስተምህሮ አምላክ አንድ ማንነትና አንድ ባሕርይ ብቻ ነው ብለው ከሚያስተምሩ የነጠላ አሓዳዊነት ሃይኖታት ለየት ያደርገዋል። ይህንን የቅዱሳት መጻሕፍትን አጠቃላይ አስተምህሮ መቀበል የቸገራቸው የስህተት ትምህርቶች በየዘመናቱ ተነስተው በቤተክርስቲያን ውስጥ ችግር ሲፈጥሩ ታይተዋል። እንደ አርዮስ ያሉ የሐሰት መምህራን ወልድን የተፈጠረ አምላክና ፈጣሪ በማለትና የመንፈስ ቅዱስን ማንነታዊነት በመካድ አብ ብቻ እውነተኛ መለኮት እንደሆነ በማስተማር ከአሃዳዊነት ጋር የሚጋጭ ጣዖታዊነትን የፈጠሩ ሲሆን እንደ ሰባሊዮስ ያሉ ሐሳውያን ደግሞ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስን አንድ ማንነት በማድረግ እግዚአብሔርን ተለዋዋጭና አንዱ ማንነት ከራሱ ጋር የሚነጋገር፣ ራሱን የሚልክ፣ ወደ ራሱ የሚጸልይ፣ ራሱን በራሱ አንተ እርሱ እያለ በመጥራት “እወድሃለሁ” ብሎ የሚያሞካሽ፣ ወዘተ. ማንነቱን የመረዳት እክል የገጠመው አካል አድርገው ስለውታል። የቅዱሳት መጻሕፍትን ስልጣናዊነት የተቀበለና በትክክለኛ ስነ ፍታቴ የሚመራስ አስተምህሮን የሚሻ ማንኛውም ግለሰብ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር በሥላሴነት የሚኖር መሆኑን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም። በዚህች አጭር ጽሑፍ የሥላሴን ምንነት እንዲሁም ሦስቱ አካላት አንድ አለመሆናቸን የሚገልጹ የቅዱሳት መጻሕፍ ማስረጃዎ እንመለከታለን።

ዘዳግም 6፡4 “አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” በማለት ያውጃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብቻ መኖሩን በግልፅ ይናገራል፡፡ ነገር ግን በባሕርይ አንድ በሆኑና ዘላለማዊ እንዲሁም እኩል በሆኑ ሦስት አካላት ይኖራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሦስቱን አካላት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በማለት እኩል ያስቀምጣቸዋል (ማቴ. 28፡19፣ 1ጴጥ. 1፡2፣ 1ቆሮ. 12፡4-6፣ 2ቆሮ. 13፡14)፡፡ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ አንድ ሲሆን ይህንን አንድ መለኮታዊ ባሕርይ የሚካፈሉ የተካከሉ ሦስት አካላት ወይም ማንነቶች አሉ። እግዚአብሔር በምንነቱ አንድ ሲሆን በማንነት ግን ሦስት ነው። በምንነቱ አንድ ነው ስንል አንድ መለኮት የሆነ ባሕርይ ብቻ አለ ማለታችን ነው። በማንነት ሦስት ነው ስንል ወልድ አብ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስ አብና ወልድ አይደለም ማለታችን ነው።

እኛ ክርስቲያኖች መገለጥ ርምደታዊ ነው ብለን እናምናለን። እግዚአብሔር ስለ ራሱም ሆነ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ አልነገረንም። በሒደት ግን ገልጧል። እግዚአብሔር ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ስለ አንድነቱ ብቻ ሳይሆን ከአንድ በላይ አካላት እንዳሉት አስታውቋል፦

  • “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” ዘፍጥረት 1፥26
  • “ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።” ኢሳይያስ 48፥12-16

በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ መሠረት አብና ኢየሱስ አንድ ማንነት የላቸውም። የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ራሱ ኢየሱስ ነው ብላ ታስተምራለች። “ክርስቶስና አብ ምንም ልዩነት የላቸውም ወልድ ማለት አብ ነው። አብ ማለትም ወልድ ነው” የሚለው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ እጅግ የራቀ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድ ያላገናዘበ የስህተት ትምህርት ነው። የቤተ እምነቱ መሥራች የሆኑት ቄስ ተክለማርያም ገዛኸኝ “ስለዚህ ክርስቶስና አብ ምንም ልዩነት የላቸውም ወልድ ማለት አብ ነው። አብ ማለትም ወልድ ነው” በማለት በግልጽ ጽፈዋል (ቃሉ ይናገር፣ ገጽ 51 PDF ቅጂ)። ኢየሱስ አብ አለማትን የፈጠረበት ልጁ እና መለኮታዊ ቃል እንጂ አብ አይደለም። ኢየሱስ የአብ ልጅ እንጂ ራሱ አብ አይደለም፦

  • “ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።” (2ዮሐ. ቁ. 3)  

Robert Brent Graves የተሰኙ የዚህ ቤተ እምነት መምህር “God of Two Testaments” በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 51 ላይ እንደ ተናገሩት “ፓራ” (ከ From) የሚለው የግሪክ ቃል በእግዚአብሔር አብና በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሁለቴ መምጣቱ ሁለት አካላትን እንደሚያሳይ አምነዋል። ጸሐፊው እንዲህ የሚል ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖሩን ዕውቅና ያልሰጡ ቢሆንም የቋንቋው ሕግ ይህ መሆኑን በማመናቸው ምክንያት ይህ ጥቅስ አብና ኢየሱስ አንድ ማንነት ናቸው ለሚሉቱ የጎን ውጋት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ እንጂ ራሱ አብ አይደለም።

በአምስተኛው የግራንቪል ሻርፕ የግሪክ ቋንቋ ሕግ መሠረት ሁለት ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ስሞች ውሱን መስተአምር ከሌላቸውና በ “ካይ” መስተጻምር ከተያያዙ ሁለት ማንነቶችን ነው የሚያሳዩት። በአዲስ ኪዳን ሰላምታዎች ውስጥ አብና ኢየሱስ ሲጠቀሱ በብዙ ሁኔታዎች ይህንን ሕግ በመከተል ነው። ለምሳሌ፦

  • “…ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” (ሮሜ 1:7) ἀπὸ Θεοῦ Πατρὸς ἡμῶν καὶ Κυρίου Ἰησοῦ Χριστοῦ.
  • “…ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” (1ቆሮ. 1:3)
  • Robert Bowman Jr. የተሰኙ ምሑር ተመሳሳይ አወቃቀር ያላቸውን 11 ጥቅሶች ጠቅሰዋል፦ ( ሮሜ 1:7፣ 1 ቆሮ. 1:3፣ 2 ቆሮ. 1:2፣ ገላ. 1:3፣ ኤፌ. 1:2፣ ፊልጵ. 1:2፣ 2 ተሰ. 1:2፣ ፊልሞና 3፤ ኤፌ. 6:23፤ 1 ተሰ. 1:1፤ 2 ተሰ. 1:1፤ 1 ጢሞ. 1:1, 2፤ 2 ጢሞ. 1:2፤ ቲ. 1:4፤ ያዕቆብ 1:1፤ 2 ጴጥ. . 1:2፣ 2 ዮሐንስ 3 ይመልከቱ)።

ዝነኛው የዮሐንስ ወንጌል መግቢ የአብና የወልድ ማንነት ለሚያወዛግባቸው ወገኖች ጥሩ መፍትሄ ነው፦

  • በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ Ἐν ἀρχῇ ἦν ὁ λόγος, ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ καὶ ὁ λόγος ἦν πρὸς τὸν θεόνቃልም እግዚአብሔር ነበረ καὶ θεὸς ἦν ὁ λόγος” (ዮሐንስ 1:1)

ይህ ጥቅስ የሚነግረን፣ ቃል (ሎጎስ λόγος) እምቅድመ -ዓለም በዘለዓለማዊ ህላዌ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ እንደነበር ነው። በፅርእ πρός “ፕሮስ” የሚለው ቃል ከተሳቢ ሙያ (Accusative Case) ጋር ሲመጣ ሁልጊዜ አብርኦትን/ግንኙነትን/ ፊትለፊትነትን የሚያመለክት ነው። (H.E. Dana , Julius R. Mantey.  A Manual Grammar of the Greek New Testament ገጽ 110)

  • “ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ Οὗτος ἦν ἐν ἀρχῇ πρὸς τὸν Θεόν ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም πάντα δι’ αὐτοῦ ἐγένετο, καὶ χωρὶς αὐτοῦ ἐγένετο οὐδὲ ἕν ὃ γέγονεν” (ቁ. 2-3)።

በጥቅሱ ውስጥ ቃል “እርሱ”αυτούς ተብሎ ተጠቅሷል። ይህም ማንነት እንዳለው ያሳያል። ግሪክ ሦስቱንም ፆታዎች የሚያመለክቱ የተለያዩ ቃላት አሉት። ለወንድ ፆታ αυτούς ለሴት ፆታ αὐτή እና ለግዑዝ ፆታ αὐτό ይሰኛሉ።

መንፈስ ቅዱስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ባሕርያት ሁሉ እንዳሉት ተገልጿል፡፡ ለአብነት ያህል፡-

  • ፈጣሪ ነውኢዮብ 33፡4፣ መዝሙር 33፡6፣ መዝሙር 104፡29-30፣ ኢዮብ 33፡4
  • ምሉዕ በኲለሄ (በሁሉም ቦታ የሚገኝ) ነውመዝሙር 139፡7-10፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
  • አዕማሬ ኲሉ (ሁሉን አዋቂ) ነው – ኢሳይያስ 40፡13፣ ዮሐንስ 14፡16፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
  • ከኃሊ ኲሉ (ሁሉን ቻይ) ነውሚክያ 2፡7፣ መዝሙር 104፡30፣ ማቴዎስ 12፡28፣ ሮሜ 15፡18-19
  • ዘላለማዊ ነውኢሳይያስ 48፡16፣ ዮሐንስ 14፡16፣ ዕብራውያን 9፡14
  • መንፈስ ቅዱስ ማንነት ያለው (እኔ ማለት የሚችል) አካል መሆኑንና አንዳንዶች እንደሚሉት ኃይል ብቻ አለመሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ለአብነት ያህል፡-
  • ይናገራል:-2 ሳሙኤል 23:2፣ የሐዋርያት ሥራ 8:29፣ የዮሐንስ ራዕይ 2፡7
  • ይመራል:-ሮሜ 8 14፣ ዮሐንስ 16:13
  • ይጠራል፣ ተልእኮዎችንም ይሰጣል፡ሐዋርያት ሥራ 13፡2፣ 20:28
  • ያዛል፡– የሐዋርያት ሥራ 8፡29
  • በአማኞች ውስጥ ይኖራል፡ዮሐንስ 14 17፣ 1 ቆሮንቶስ 6:19
  • ያስተምራል፡ዮሐንስ 14 26; 1 ዮሐንስ 2:27
  • ይልካል፡የሐዋርያት ሥራ 13:4
  • ኃይልን ይሰጣል፡የሐዋርያት ሥራ 1:8፣ 2ጴጥሮስ 1:21
  • ይመሰክራል፡ዮሐንስ 15፡26፣ 27፣ 16: 13,14
  • ሊመረር ይችላል፡ኢሳይያስ 63:10
  • ያዝናል፡– ኤፌሶን 4፡30
  • ሰዎች ሊዋሹት ይችላሉ፡የሐዋርያት ሥራ 5 3
  • ሰዎች ሊሰድቡት ይችላሉ፡ማቴዎስ 12፡31
  • ይከበራል፡መዝሙር 51፡11
  • ስጦታን ይሰጣል፡1ቆሮንቶስ 12፡27-28
  • ያፅናናል፡ዮሐንስ 16፡7
  • ይወቅሳል፡ዮሐንስ 16፡8-11

ማንነት አልባ ኃይል ከላይ የተጠቀሱት ባሕርያት ሊኖሩት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚታየው መንፈስ ቅዱስ የማንነት መገለጫ የሆኑትን ሦስቱን ባሕርያት፤ ማለትም ዕውቀት፣ ፈቃድና ስሜት ስላለው ማንነት አለው፡፡

መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች መለኮታዊ ማንነቶች ጋር እኩል ተጠቅሷል

  • ስለ ጥምቀት ትዕዛዝ፡ ማቴ. 28፡19
  • በቡራኬ፡ 2ቆሮ. 13፡14
  • በሰላምታ፡ 1ጴጥ. 1፡2

መንፈስ ቅዱስ ሲጠቀስ ማንነትን አመልካች ተውላጠ ስም ጥቅም ላይ ውሏል

  • ዮሐ. 16፡14፣ 15፡26፣ 16፡7-8፣ 1ቆሮ. 12፡8-11፣ ሮሜ 8፡16፣26፣ ኤፌ. 1፡14

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ለሐዋርያቱ ሲያስታውቅ እንዲህ ነው ያላቸው፦

  • “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐንስ 14:15-17)
  • “ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14:25-26)

“እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” (ዮሐንስ 16:7-16)

አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በማንነት ልዩ ካልሆኑ ይህ የክርስቶስ ንግግር ትርጉም አልባ ይሆናል። የሐዋርያት ነን ባዮች የእምነት ተቋም አስተምህሮ አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ያላገናዘበ ቃለ እግዚአብሔርን የማረም ሰብዓዊ ጥረት እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።

ማጠቃለያ

እግዚአብሔር ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ አንድነቱንና ሦስትነቱን ገልጧል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር በብዙ ቁጥር የተገለጸባቸው በርካታ ጥቅሶች አሉ።

  • “የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።” ትንቢተ ኢሳይያስ 68
  • “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ…” ኦሪት ዘፍጥረት 322
  • ዘፍጥረት 35፡7  “በዚያም መሰውያውን ሠራ፡ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።” ይህ ጥቅስ በእብራይስጥ הָֽאֱלֹהִ֔ים אֵלָיו֙ נִגְל֤וּ שָׁ֗ם “ሻም ኒግሉ ኢላው ሀኤሎሂም” ይላል፡፡ נִגְל֤וּ ( ኒግሉ) የሚለው ቃል የ גֶּלֶה “ጋላህ” ሦስተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ “ተገለጡለት” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ጥቅሱ ሲተረጎም “ኤሎሂም በዚያ ተገለጡለት” የሚል ይሆናል።
  • ዘዳግም 4፡7 “በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?” በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ቅርብ” የሚለው ቃል በእብራይስጥ “ቃሩቢም” קְרֹבִ֣ים የሚል ሲሆን “የቃሮብ” קָרוֹב ብዙ ቁጥር ነው፡፡ ጥቅሱ በቀጥታ ሲተረጎም “ኤሎሂም ለእኛ ቅርብ እንደሆኑ” የሚል ትርጉም ይሰጣል።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱና የአብ አንድነት ምን እንደሚመስል በግልጽ ተናግሯል፦

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።” (ዮሐንስ 17:22-23)

“ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።” (ዮሐንስ 17:11)

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱንና የአብን አንድነት የገለጸው ሐዋርያቱ ባላቸው አንድነት ነው። ሐዋርያቱ አንድ ሆኑ ሲባል ተጨፍልቀው አንድ ማንነት ሆኑ ማለት ካልሆነና ኢየሱስ እንዲኖራቸው የጸለየላቸው አንድነት የአብና የእርሱ ዓይነት አንድነት ከሆነ አብና ኢየሱስም አንድ ማንነት አይደሉም ማለት ነው። አለበለዚያ የኢየሱስ ጸሎት አልተሰማም ልንል ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ ስፍራ እንዲህ ብሏል፦

“ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።” (ዮሐንስ 16:28)

አንዳንዶች “ከአብ ወጥቼ” የሚለውን ከአብ ውስጥ መውጣት አድርገው ይተረጉሙታል ነገር ግን በተመሳሳይ የሰዋሰው አወቃቀርና ቃል ሐዋርያው ዮሐንስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል ጽፏል፦

“ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።” (1ዮሐ. 2:19)

በዚህ ስፍራ መውጣት የሚለው ከውስጥ መውጣትን ሳይሆን ሕብረትን ለማሳየት ነው የዋለው። እነዚህ ወገኖች ወጡ ሲባል ከአማኞች ሰውነት ውስጥ ወጡ ማለት ሳይሆን ከሕብረት ተለዩ ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስም ከአብ ስለመውጣቱ ሲነገር አብ ካለበት ከዚያ ስፍራ መምጣቱን ለማሳየት ነው። ኢየሱስና አብን አንድ ማንነት ለማድረግ የሚመኙ ወገኖች ኢየሱስ ራሱ አብ ከሆነ አብ ከአብ ውስጥ ወጣ ሊሉን ይዳዳቸው ይሆነ? ኢየሱስ ወደ አብ ተመልሶ መሄዱንስ ሲናግር ወደ አብ ውስጥ ተመልሶ እንደ ገባ ይነግሩን ይሆን? ይህ ካልሆን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ አይደለም ማለት ነው።

  • “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (2ቆሮንቶስ 1፡3)
  • “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።” (ኤፌሶን 1፡3)
  • “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።” (1ጴጥሮስ 1፡3-5)

አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ ማንነት ናቸው የሚለው የሰባልዮሳውያን ትምህርት በቅዱሳት መጻሕፍት የማይታወቅ ከቋንቋ አገላለጽም ሆነ ከአመክንዮ አንጻር ትርጉምን የማይሰጥ የግለሰቦች ፈጠራ ነው።


 

መልስ ለሰባልዮሳውያን