360 መገጣጠሚያዎችና የሙሐመድ ሐሰተኛነት
ፈጠራ የማይሰለቻቸው ሙስሊም ሰባኪያን “በሰው ውስጥ 360 መገጣጠሚያዎች እንዳሉ ነቢያችን አስቀድሞ ነግሮናል ስለዚህ እውነተኛ ነቢይ ነው” እያሉን ነው። በርግጥ በሳሂህ ሐዲሳት እንደተዘገበው ሙሐመድ በሰው ልጆች ውስጥ 360 መገጣጠሚያዎች እንደሚገኙ ተናግሯል። ነገር ግን ሙስሊም ወገኖቻችን ይህንን ጉዳይ ለነቢይነቱ ማረጋገጫ አድርገው ማምጣታቸው በእጅጉ አስቂኝ ነው። የተወሰኑ ምክንያቶችን ልንገራችሁ፦
- የሰውን ልጆች መሠረታዊ አናቶሚ ለማወቅ ነቢይ መሆን አይጠበቅብንም። የዘመናችን የኅክምና ባለሙያዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሰውን አካል ከፍቶ መመልከት ብቻ በቂ ነው። የሰውን አካል ከፍቶ ጥልቅ ምልከታ (autopsy) ማድረግ ቀላል ሥራ ባይሆንም በሙሐመድ ዘመንም ሆነ ከዚያ በፊት ሲደረግ የነበረ ተግባር ነው። አረቦችም ሆኑ ቀደምት ሙስሊሞች እንዲህ ያለ ዕውቀት ቢኖራቸው ምንም አይደንቅም።
- በሙሐመድ ዘመን ይህ ዕውቀት አልነበረም ከተባለ ቻይኖች ከሙሐመድ ዘመን ቢያንስ ከ800 ዓመታት በፊት የሰው ልጆች 360 መገጣጠሚያዎች እንዳሏቸው እንዴት አወቁ? (ማስረጃዎቹን ከምሑራዊ መጻሕፍት ገጾች ላይ በምስል አያይዣለሁ። ከታች ይመልከቱ።)
- በርግጥ ቻይኖች የሰው ልጆች 360 መገጣጠሚያዎች አሏቸው የሚል እምነት ያዳበሩት የሰው ልጆች የፅንፈ ዓለሙ ነፀብራቅ እንደሆኑ ስለሚያምኑ ነበር። በዚህም መሠረት የጨረቃ ዘመን አቆጣጠራቸው በአማካይ 360 ቀናት ስላሉት እንዲሁም የሰማይን ክበብ በ360 ነጥቦች ስለሚከፍሉ በሰው ውስጥም 360 መገጣጠሚያዎች አሉ ብለው ያምኑ ነበር። የአረቦቹም ከዚህ የተለየ አይሆንም። ሙሐመድ ስለ ሰው መገጣጠሚያዎች የተናገረው በያንዳንዱ ቀን መልካምን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ለማሳሰብ ከመሆኑ አንጻር አረቦቹም ከቻይኖቹ ጋር ተመሳሳይ እምነት እንደነበራቸው መረዳት ይቻላል። (በዓመቱ ቀናት ቁጥር ልክ የተሠሩ በመካ የነበሩትን 360 ጣዖታትንም እዚህ ጋ ማስታወስ ያስፈልጋል።)
- ከሙሐመድ ዘመን ከክፍለ ዘመናት በፊት እንኳ ከቻይና እስከ አውሮፓ ድረስ የነበረው ዓለም በንግድ የተሣሠረ ስለነበረ ከ800 ዓመታት በፊት በቻይና ሲታመን የኖረ ጉዳይ አረቦች ዘንድ አልደረሰም ማለት የዋህነት ነው። ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ አልፎ እስከ አውሮፓ ድረስ በተዘረጋው “የሐር መንግድ” (Silk Road) በተሰኘው የንግድ መስመር አማካይነት ከ130 ቅድመ ክርስቶስ እስከ 1453 ዓ.ም. ድረስ ከሌላው ዓለም ጋር የጠበቀ የንግድ ትስስር እንደነበራት ከታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል። https://www.history.com/topics/ancient-middle-east/silk-road በዚህ መካከል የዕውቀት ሽግግር መኖሩ ግልፅ ነው። አረቦች የቻይኖችን ዕውቀት መስማት የማይችሉበት አንዳች ተዓምር ሊኖር አይችልም።
- ሙሐመድ የተናገረው ነገር ከቻይኖች የተገኘ አይደለም ቢባል እንኳ በብዙ ክፍለ ዘመናት የቀደሙ ሕዝቦች ስለ ጉዳዩ ማወቅ ከቻሉ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን አረቦች ማወቅ መቻላቸው እንደ ተዓምር የሚቆጠርበትን ምክንያት ማሰብ ያዳግታል። የቻይኖቹ ዕውቀት ተዓምር ካልተባለ የአረቦችም ሊባል አይችልም፤ ሙሐመድም በየ ቦታው የሚወራውን ጉዳይ ማወቅ አይችልም አይባልም። (ሙስሊም ወገኖች ሙሐመድ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር የሚለውን ተረት እዚህ ጋ አምጥታችሁ እንዳታስቁን። ነጋዴው ሙሐመድ ጆሮ አልነበረውም ካላችሁ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች “ጆሮ” በሚል የቅጽል ስም ይጠሩት እንደነበር ቁርአን 9:61 ይነግራችኋል)።
- በሰው ውስጥ 360 መገጣጠሚያዎች አሉ የሚለው አባባል እንደ ቋሚ እውነታ ተቆጥሮ መደበኛ በሆኑት የኅክምና መማርያ መጻሕፍት ውስጥ በስፋት የምናገኘው አባባል ሳይሆን በጥቂት አጫጭር መጣጥፎችና የኢንተርኔት ገጾች ላይ የምናገኘው መረጃ ነው። የመገጣጠሚያ ብዛት በዕድሜና በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ከሰው ሰው የሚለያይ መሆኑ ስለሚታወቅ ምሑራን በመደበኛ የኅክምና መማርያ መጻሕፍት ውስጥ እንዲህ ያለ ጥቅላዊ አባባል አለማስቀመጣቸው ተገቢ ነው። ካስቀመጡም ከዚህ እስከዚህ የሚል እንጂ ቁርጥ ያለ ቁጥር አይሰጡም።
- በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ አጫጭር የኅክምና መረጃ መጣጥፎችም ቢሆኑ በሰው ውስጥ ያለው መገጣጠምያ ቁጥር 360 ነው የሚል የተስማማ መረጃ አይሰጡም። ለምሳሌ ያህል Scott Frothingham የተሰኘ ዶክተር ሜይ 17, 2019 “How Many Joints Are in the Human Body?” በሚል ርእስ በጻፈው ጽሑፍ “In short, there’s no definite answer to this question. The estimated number is between 250 and 350” “በአጭሩ ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ የለም። የሚገመተው ቁጥር ከ250 እስከ 350 ነው” በማለት አስቀምጧል። ሌሎች በጣም በርካታ ምንጮች 200፣ 248፣ 147፣ 100፣ 143፣ ወዘተ. የሚሉ መረጃዎችን ይሰጣሉ። (እነዚህን ቁጥሮች “joints” የሚል ቃል ጨምሮ ኢንተርኔት ላይ ፍለጋ በማድረግ ውጤቶቹን ማግኘት ይቻላል።) እንደ ሙስሊም ሰባኪያን አባባል ከነዚህ ቁጥሮች መካከል አንዱን እንደ እድል የተናገረ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ሰው ነቢይ ሊሆን ነው። አስቂኝ ነው።
- የመገጣጠሚያ ቁጥር ከሰው ሰው የሚለያይ ሆኖ ሳለ ሙሐመድ በ360 ገድቦ መናገሩ ስህተት ነው። ዕድሜና ሌሎች ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የመገጣጠሚያ ቁጥር ከሰው ሰው ይለያያል። ሙሐመድ ግን በሐዲስ የተናገረው ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት የመገጣጠሚያ ቁጥር እንዳው በማስመሰል ነው፦ “Every one of the children of Adam has been created with three hundred and sixty joints” “የአዳም ልጆች ሁሉ የተፈጠሩት ከሦስት መቶ ስድሳ መገጣጠሚያዎች ጋር ነው” (Sahih Muslim Book 5, Hadith 2199)። ይህ ሐሰት ነው። ሙሐመድ በዘመኑ የሚታወቀውን ጉዳይ ደግሞ እየተናገረ እንጂ የተለየ መለኮታዊ መገለጥ መጥቶለት አይደለም። ቢሆን ኖሮ ሁሉንም የሰው ልጆች በአንድ ቋት ጠቅልሎ ስህተት የሆነ ንግግር ባልተናገረ ነበር። አባባሉ የሙሐመድን እውነተኛነት ከማረጋገጥ ይልቅ ሐሳተኛነቱን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህንን ሐዲስ በመጥቀስ ሙግቱን በስፋት ያስተዋወቀው ኦሳማ አብደላ የተሰኘ ሙስሊም አፖሎጂስት ሲሆን ከክርስቲያን ወገኖች ጋር በነበረው የተራዘመ ውይይት ስህተቱን አምኖ ተቀሎ ነበር፤ ጽሑፉንም ከገጹ ላይ አጥፍቶ ነበር። ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ስህተቱን ያመነበትን ጽሑፍ ከገጹ ላይ በመሰረዝ እንደገና ጽሑፉን አሻሽሎ ለጥፏል። ስህተቱን አምኖ በተቀበለበት ወቅት ግን የተለያዩ የሐዲስ ጸሐፍትን እየተቸ በመጻፉ ምክንያት ከብዙ ሙስሊሞች ጋር የሐሳብ ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር። ኦሳማ ይህንን ሙግት አንዴ ሲክድ አንዴ ሲያሻሽል ከየት ተነስቶ የት እንዳደረሰው ለማወቅ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ https://www.answering-islam.org/…/360joints_revisited.htm
ሙስሊም ወገኖቻችን እንዲህ ባለ የሞተ ሙግት የነቢያችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ መሞከራችሁ ሐሰተኛነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ምንም ዓይነት ፋይዳ ስለሌለው ቢቀርባችሁ የተሻለ ነው።