የቢሾፕ ተክሌ የሐሰት ዶክትሬት
በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ጉያ የተሸሸገ የማጭበርበር ወንጀል
ይህ ጽሑፍ የማንንም ስብዕና የመንካት ወይንም የማንንም የእምነት ተቋም የማንኳሰስ ዓላማ እንደሌለው በማሳሰብ መጀመር ተገቢ ነው። ማንንም ማሸማቀቅና ማሳጣትን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ አይደለም። የአንድን ቤተ እምነት መሪና የድርጅታቸውን ሃቀኝነት ለመፈተሽ በቅንነት እውነቱን ለማወቅ የተደረገ ምርመራ ውጤት ብቻ እንደሆነ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። ይህንን ካልኩ ዘንዳ ወደ ፍሬ ሐሳቡ ልግባ።
“የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” ወይም በተለምዶ “ኦንሊ ጂሰስ” የተሰኘው ቤተ እምነት በኢትዮጵያ መስራች የነበሩት ቢሾፕ ተክለማርያም ገዛኸኝ በአስተምህሯቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሃቀኝነታቸውም ላይ ጭምር ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድዱ አንዳንድ ጉዳዮች መሰማት ከጀመሩ ሰነባብቷል። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ከሰሞኑ አንድ ወዳጄ ቢሾፑ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀበሉ ከተባለበት ኮሌጅ ጋር የተለዋወጠው የኢሜይል መልዕክት ነው። ቢሾፑ ከአንድ በእምነት ከሚመስላቸው ተቋም ተቀበሉ ከተባለው የክብር ዶክትሬት በተጨማሪ በትክክል ተምረው የዶክትሬት ዲግሪ እንደጫኑ በመግለፅ ከመጠርያ ስማቸው በተቀፅላ ዶ/ር እንዲሁም PhD የሚል ማዕርግ ሲጠቀሙ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ጉዳይ ሊጣራ እንደሚገባው ለመጀመርያ ጊዜ ጥቆማ በመስጠት ጥያቄ የሚያጭር ሐሳብ የሰነዘሩት በዚህ ቤተ እምነት እንዲሁም በመሰሎቻቸው ዙርያ ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ አቃቤ እምነታዊ መጻሕፍትን በማዘጋጀት የሚታወቁት የሀገራችን የነገረ መለኮት ምሑር ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ ናቸው። ቀደም ሲል የጠቀስኩት ወዳጄ ጉዳዩን ለማጣራት ከኮሌጁ ጋር የተለዋወጠው ኢሜይልና ያገኘው ምላሽ እንዲሁም የኮሌጁ ኦፊሴላዊ ድረገጽ ላይ የሚታየው መረጃ ቢሾፑ ተቀበልኩ ያሉት የዶክትሬት ዲግሪ የሐሰት መሆኑን ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከአፍታ በኋላ እነዚህን መረጃዎች የማጋራችሁ ሲሆን አስቀድመን ቢሾፑ ዶክትሬታቸውን በትምህርት ያገኙ በማስመሰል የሚናገሩ ከቤተ እምነቱ የወጡ መረጃዎችን እንመልከት።
በማስከተል በሚገኘው ምስል ላይ እንደሚታየው ቢሾፑ “Genesis Institute of Theology, Evangelism & Leadership” ከተሰኘ ተቋም “Theocentric Psychology” በተሰኘ የጥናት ዘርፍ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል።
በዚሁ የሳቸውን ሕይወት ለመዘከር በተጻፈ ቡክሌት ላይ ቢሾፑ የዶክትሬት ዲግሪ ምሩቃን የሚለብሱትን ጋወን ለብሰው ይታያሉ፤ ነገር ግን የትምህርት ደረጃቸውን የሚገልጸው ክፍል ከገጽ 21 በሚጀምረው የቡክሌቱ የእንግሊዝኛ ክፍል አልተካተተም።
በቢሾፑ የተዘጋጁትን የሕትመት ሥራዎች ስንመለከት “PhD” ወይም “ዶ/ር” የሚለውን ተቀፅላ ከስማቸው ጋር በኩራት ሸክፈው እናገኛቸዋለን። ለአብነት በቤተ እምነቱ ድረገጽ ላይ ማስታወቂያው የተቀመጠለትን ይህንን መጽሐፍ መመልከት ይቻላል፦
የክብር ዶክትሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ዓይነቱ ባልተገለጸበት ሁኔታ በተለይም በሕትመት ሥራዎች ላይ አንድ ሰው ማዕርጉን መጠቀም እንደሌለበት ይታወቃል። ቢሾፑ በሕትመት ሥራዎቻቸው ላይ የዶክትሬቱን ዓይነት ሳይገልጹ ሲጠቀሙ መኖራቸው በትምህርት አገኘሁት ያሉትን ዶክትሬት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው።
በዚህ ሳያበቃ የቀብር ሥርዓታቸው በተፈጸመ ዕለት የሕይወት ታሪካቸው ሲዘከር ከ“Genesis Institute of Theology, Evangelism & Leadership” በ“Theocentric Psychology” የጥናት ዘርፍ እንደተመረቁ የሚገልጽ ዓረፍተ ነገር በንባብ ተሰምቷል። ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ቢሾፑ ዶክትሬታቸውን በትምህርት አግኝተዋል የሚለው ጉዳይ በስህተት የተነገረ ሳይሆን እሳቸው አምነውበት የተናገሩት፣ የቅርብ ሰዎቻቸው እንዲሁም ቤተ እምነታቸውም ጭምር እርግጠኛ ሆነው የተቀበሉት ጉዳይ መሆኑን ነው። ነገሩ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይህ ጉዳይ ሐሰት ሆኖ መገኘቱ የድርጊቱ ተባባሪ የሆነው ድርጅታቸውንም ተጠያቂ የሚያደርግ ወንጀል ይሆናል።
ቀደም ሲል እንደተገለጸው የቢሾፑ ዶክትሬት ዲግሪ ትክክለኛነት ጥያቄ ከተነሳበት ውሎ አድሯል። ነገር ግን የተመረቁበትን የምስክር ወረቀት ወይም ያጠኑትን ጥናት (dissertation) በእማኝነት በማቅረብ ክሱን ውድቅ ለማድረግ የተሞከረበት ምንም ዓይነት ምላሽ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከቤተ እምነቱ ዘንድ አልታየም። በቅርቡ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ በአንድ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ በነበረ ውይይት አንድ የቅርብ ዘመዳቸው እንደሆነ የገለጸ ግለሰብ ቢሾፑ በዶክትሬት ዲግሪ እንደተመረቁ እርግጠኛ ሆኖ የተናገረ ሲሆን ማስረጃ ማቅረብ ይችል እንደሆን ተጠይቆ የቢሾፑን ፎቶግራፍ በእማኝነት በመጥቀስ ፈገግታን የሚጋብዝ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የድምጽ ቅጂው በእጃችን ስለሚገኝ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሌላ በሰሜን አሜሪካ የሚኖር አንድ የቤተሰባቸው አባል [የግል መረጃ ለመጠበቅ ስንል ስሙን የማንጠቅሰው የቢሾፑ ልጅ] ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ የተመረቁበት የምስክር ወረቀት በእጁ እንደማይገኝና ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ጉዳዩን እንደሚያረጋግጥ በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ የመልዕክት ልውውጥም ስለ ጉዳዩ በሀገረ ካናዳ የሚገኘውን ኮሌጅ ጠይቆ ማጣራት የተሻለ እንደሚሆን ምክር ቢጤ ለግሷል፡፡ በግለሰቡ ምላሽ ውስጥ እርግጠኛነት የማይታይ ሲሆን በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን የምስክር ወረቀቱን ለመመልከት የግዴታ ረዥም ርቀት መሄድ እንደማያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡ የመልዕክት ልውውጡ በማስከተል የሚታየው ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ የግለሰቡን ማንነትና የመልዕክቱን ትክክለኛነት ማጣራት ለሚፈልግ አካል መግለጽ ይቻላል፡፡
የእውነት ቢሾፕ ተክሌ በወጉ ተምረው የዶክትሬት ዲግሪ ተቀብለው ከነበረ ለብዙ ዓመታት በሕትመት ሥራዎችና በተለያዩ ማሕበራዊ ሚድያዎች ጥያቄ ሲነሳበት የኖረውን ሃቀኝነታቸውን በማረጋገጥ ከክሱ ነጻ ሊያደርጋቸው የሚችለውን የዓይን ጥቅሻ ያህል ቀላል የሆነውን ተግባር ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ቤተ እምነታቸው መፈጸም አለመቻላቸው አስገራሚ ነው። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የቢሾፑ ዶክትሬት የሐሰት መሆኑ እንደሆነ የሚያሳዩ የማይታበሉ ማስረጃዎች እጃችን ገብተዋል። በመጀመርያ የማቀርብላችሁ ቢሾፑ ተማሩበት ከተባለው የትምህርት ተቋም ጋር ፌብሩዋሪ 21/2024 የተደረገውን የኢሜይል ልውውጥ ነው።
በምስሉ ላይ የሚታየው ወዳጄ የላከው ኢሜይል የሚለው እንዲህ ነው፦ “ሰላም፣ ስሜ [የግል መረጃ ለመጠበቅ ያልተገለጸ] ትምህርት ቤታችሁ በ Theocentric Psychology የዶክቶራል ዲግሪ የሚሰጥ ከሆነ ወይም ከዚህ ቀደም ሰጥቶ የሚያውቅ ከሆነ ለመጠየቅ ፈልጌ ነበር። የናንተን መርሃ ግብር መቀላቀል በእጅጉ እፈልጋለሁ፤ በቅርቡ እንደምትመልሱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ! ተባረኩ!”
ከምስሉ እንደሚታየው ቸሪን ግሪፊትስ የተሰኙ የትምህርት ቤቱ ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ በአንድ ሰዓት ውስጥ መልስ ሰጥተዋል። መልሳቸው እንዲህ የሚል ነው፦ “ሰላም ለእርስዎ ይሁን ___፟. ስለ ኢሜይሎና ስለ ጥያቄዎ በጣም አመሰግናለሁ። የምንሰጠው ትልቁ የትምህርት ደረጃ የቅድመ ምረቃ [የመጀመርያ ዲግሪ] መሆኑን እንዲረዱ በትህትና አሳውቃለሁ። ተባረኩ!”
ይህ የኢሜይል ልውውጥ የተደረገው በሀገረ ካናዳ ከሚገኘው ቄስ ተክሌ ተምሬበታለሁ ካሉት ተቋም ጋር መሆኑን በምስሉ ላይ የሚገኘውን አድራሻ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል። የተቋሙ ድረገጽ ላይ ገብተንም ስንመለከት በዲፕሎማና የመጀመርያ ዲግሪ ደረጃ እንጂ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ምንም ዓይነት ትምህርት እንደማይሰጥ በግላጭ ይታያል፦
ታድያ ቢሾፑ በተቋሙ በማይሰጥ የትምህርት ዓይነትና ደረጃ “ሊመረቁ” እንዴት ቻሉ? ጉዳዩ ወዲህ ነው። ቢሾፕ ተክሌ በ“Theocentric Psychology” ተመርቄያለሁ ያሉት የተቋሙ መስራች በግል ፍላጎት ያጠኑትን ርዕስ በመቅዳት ነው! የተቋሙ መስራች ዶ/ር ትሬቨር ቢ. ኔይል የተሰኙ ግለሰብ ሲሆኑ ቢሾፕ ተክሌ እንደተመረቁበት ሲገልጹ የነበሩትን የጥናት ርዕስ (Theocentric Counseling & Psychology የተሰኘ የሙያ ዓይነት) በግል ፍላጎት ይለማመዱ እንደነበር በድረገጻቸው ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ይህም በተቋሙ ድረገጽ ላይ እንዲህ ይነበባል፦
Dr. Neil ministered in the Middle East, Europe, Africa, and North America. Dr. Neil’s life was marked by many accomplishments: He was a church planter, educator, prolific writer, mentor, entrepreneur, and a superintendent of the Canadian Plains District of the United Pentecostal Church International. He also had a private practice in Theocentric Counseling & Psychology.
https://www.genesisstudies.com/team-1-1
ይህ የትምህርት ዓይነት እንኳንስ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ይቅርና በዝቅተኛ ደረጃዎች እንኳ በተቋሙ ውስጥ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ከቢሾፕ ተክሌ ድርጅት የወጣው መረጃ በስህተት ይሁን ለማምታታት Counseling የሚለውን በመቀነስ Theocentric Psychology እንደተማሩ ቢገልጽም እንዲህ ያለ መጠርያ ያለው ትምህርት በተቋሙ ስለመሰጠቱ አሁንም ፍንጭ የለም። ምናልባት ቢሾፑ የተመረቁት ተመሳሳይ ስም ካለው ሌላ ተቋም ነው እንዳይባል ከዚህ ተቋም ውጪ በዚህ ስም የሚታወቅ የእርሳቸው ቤተእምነት (Oneness Pentecostalism) የሚመራው የስነ መለኮት ትምህርት ቤት የለም። ይህ ተቋም የተመሠረተው ቄስ ተክሌ “ሰማያዊ ሥጋ” የሚል አዲስ ትምህርት በማምጣታቸው ሳብያ ባወገዛቸው ቤተ እምነት፣ ማለትም የ United Pentecostal Church International አገልጋይ በነበሩ ግለሰብ ነው። ቄስ ተክሌ በሰላሙም ይሁን በጠቡ ጊዜ ሊማሩ የሚችሉ ከዚህ ትምህርት ቤት ውጪ ሊሆን አይችልም። ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ጉዳዩን ለማጣራት በተደረገ ፍለጋ Genesis Institute of Theology, Evangelism & Leadership የሚል ስም ያለው ከዚህ ተቋም ሌላ የትምህርት ተቋም ማግኘት አለመቻሉ ነው። የቢሾፑ አልጋ ወራሾች ትክክለኛው ተቋም ይህ መሆኑን የሚክዱ ከሆነ በዓለም ላይ ከሌለ ህልውና አልባ ተቋም ተመርቀዋል ማለት ስለሚሆን ከዚህ የከፋ ቅጥፈት ይሆናል። Genesis Institute of Theology, Evangelism & Leadership የተሰኘው ተቋም ድረገጽ እንደ ትክክለኛ የትምህርት ተቋማት .org ወይም .edu የሚል ዶሜን ከመሆን ይልቅ .com መሆኑ በራሱ የተቋሙን አናሳነት የሚያሳይ ነው።
የማጠቃለያ ሐሳብ
አንድ ሰው ባልተማረው የትምህርት ዘርፍ እንደተመረቀ በመግለጽ የማጭበርበር ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገራችን ሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው። ለአብነት በሀገራችን በኢንጂነሪንግ ሙያ እንደተመረቀ በማስመሰል ሲያጭበረብር ተይዞ ለእስር የተዳረገውን ግለሰብ መጥቀስ እንችላለን። ግለሰቡ ባልተማረው ሙያ እንደተመረቀ በማስመሰል በተለያዩ ሚድያና የትምህርት ተቋማት ንግግሮችን ሲያደርግ ከኖረ በኋላ ጉዳዩ ታውቆበት ሸሽቶ ከሄደባት ኬንያ ድረስ በእግረ ሙቅ ተቀፍድዶ እንዲመጣ በመደረግ በከባድ የማጭበርበር ወንጀል ለፍርድ ቀርቦ ለእስር ተዳርጓል።
ባልተማሩት ሙያ በመጠራትና የሐሰት ሰርተፊኬቶችን በማሠራት ማጭበርበር በማሕበረሰባችን ውስጥ የከፋ ችግር እያስከተሉ ከሚገኙት ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው። በዚህም ሳብያ ብዙ የሕዝብ አገልግሎቶች ተበድለዋል፣ ብዙ ዜጎችም ለጤና ጉዳት አልፎም ለህልፈት ተዳርገዋል። መንግሥት እንዲህ ያለውን ወንጀል ለመከላከል ደፋ ቀና በሚልበት ዘመን ለሕብረተሰቡ የግብረ ገብነት መሠረት ሊሆኑ የሚገባቸው መንፈሳዊያን ተቋማት በተመሳሳይ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ከሆነ በእውነቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ማንም ይሁን ማን እንዲህ ያሉ ወንጀሎችን ሠርቶ የተገኘ ግለሰብ በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀስ እንኳ ቢሆን መጋለጥና ለሠራው ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን ይገባዋል።
በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የማንንም ግለሰብ ስብዕና ለማጉደፍ ወይንም የየትኛውንም ተቋም ክብር ለመንካት አይደለም። መሰል የማጭበርበር ተግባር በማሕበረሰቡ ውስጥ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖር የራስን አስተዋፅዖ ለማበርከት የታለመ ለእውነት ካደረ ልቦና የመነጨ ፍለጋ ብቻ ነው። ደግሞም ይህ ክስ የሰነበተ ከመሆኑ አንጻር ጉዳዩን ማንሳት ለቤተ እምነቱ የራሱን ንጽህና ለማረጋገጥ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ የጠያቂነት መብቴን መጠቀሜ የተጠቀሱትን አካላት ጭምር የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አድርጌ አላስብም።
ቢሾፕ ተክሌ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ዓመታት ቢቆጠሩም የእርሳቸው ውርስ (Legacy) በቤተ እምነቱ ውስጥ እንደቀጠለ ነው። በእርሳቸው የተመሠረተችው የሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእምነት ተቋም ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እውነቱን በአደባባይ ተናግራ ለእውነት ያላትን ወገንተኝነት ታረጋግጥ እንደሆን በቀጣይ የምንመለከተው ይሆናል። የእውነት ቢሾፑ ከተባለው ተቋም በተባለው የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው ከሆነና ማስረጃውን ማሳየት ከተቻለ እሰየው። እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ከስህተቴ ታርሜ ይቅርታ በመጠየቅ ይህ ጽሑፍ በተሰራጨበት በዚሁ መድረክ የቢሾፑን እውነተኛነት የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። ነገር ግን እውነቱ በተጻራሪው ስለመሆኑ ከላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎች ምስክር በመሆናቸው ይህ ጉዳይ የእምነት ድርጅቱን ሃቀኝነት እንደሚፈታተን ጥርጥር የለውም። ይህ የማጭበርበር ወንጀል እውነት ሆኖ ከተገኘ የእምነት ድርጅቱ መሪዎች እውነቱን በግልጽ ለሕዝብ በመናገር የቢሾፑን ድርጊት አውግዘው ራሳቸውን ነጻ እንደሚያወጡ ይጠበቅባቸዋል። ካልሆነ ግን ግለሰቡ ከሚዛን ወርደው በቀለሉት መጠን በመቅለል የእምነት ተቋማቸውን ዋጋ የሚያስከፍል ጥበብ የጎደለው ምርጫ ስለሚሆን እውነትን በመሸፈን ከሚመጣው አውዳሚ መዘዝ ቤተ እምነታቸውን ለማትረፍ የሚሹ አማኞች ሁሉ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ተስፋ አለኝ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕግ አካላትና የእምነቱ ተከታዮች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ በማቅረብ አጠቃልላለሁ። ቸር ያሰማን!