ሰይጣን የክርስቲያኖች ባለውለታ ነውን?

 

ሰይጣን የክርስቲያኖች ባለውለታ ነውን?

 


2. መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ ወንጌል 22: 3 -5 “ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ከተቆጠረው አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በተባለው በይሁዳ ገባበት፤  ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ፡፡ እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ፡፡ እርሱም በነገሩ ተስማማ” ይላል፡፡ ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ካደረገውና ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስም ተይዞ ከተሰቀለ ሰይጣን ለክርስቲያኖች ባለ ውለታ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ ክርስቲያኖች እንደሚሉት በኢየሱስ መሰቀል ነውና “ድነው ከኃጢአት ነጻ የወጡት፤ ገነትም ወራሽ የሆኑት፡፡”  ይህ ነው የክርስትና መዳኛ መንገድ፡፡ ስለዚህ ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ አደረገው፡፡ ከዚያም ክርስትና እንደሚለው ኢየሱስ ተይዞ ተሰቀለ፡፡ በጥሞና ካስተዋልነው ክርስቲያኖች “ድነናል” ያሉበት “ስቅለት” እንዲሳካ ሰይጣን ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የመዳኛውን መንገድ ዘርግቷል፡፡ ታድያ የክርስትና አብዩ አስተምህሮትና መዳኛው የሰይጣን ሊሆን አይደል? ሰይጣን በይሁዳ ገብቶ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ባያደርግ ኖሮ ስቅለት ይሳካ ነበር? ክርስትና እንደሚለው ክርስቶስ ባይሰቀል ክርስትያኖች ከኃጢአት ይነጹ ነበርን? ክርስትና የሚባል እምነትስ ይኖር ነበርን? በፍፁም!! ታድያ እንደ ሰይጣን ማን መልካም ሰሪ አለ? ኢየሱስን አሰቅሎ ክርስትያኖችን አድኖ የለም እንዴ?

አሕመዲን ጀበል ይህንን ጥያቄ ያቀረቡበት መንገድ ከምሑራዊ አካሄድ ያፈነገጠ፣ ድፍረትና ንቀት የታከለበት እንዲሁም የክርስትናን ትምህርት በሚያንቋሽሽ አነጋገር ነው፡፡ አካሄዳቸውን በማበላሸት ገና ከጅምሩ ኩሬውን መርዘውታል፤ የማስተማር ፍላጎታቸውንና ቅንነታቸውንም እንድንጠራጠር አድርገውናል፡፡

የክርስቶስ ወደ ምድር መምጣትና ስለ ሰው ልጆች ኃጢኣት መሞት የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እቅድ እንጂ የየትኛውም ፍጥረት ዕቅድ አልነበረም (ራዕይ 13፡8፣ የሐዋርያት ሥራ 4፡27-28)፡፡ ወደ ምድር የመጣውም በገዛ ፈቃዱ ነፍሱን ስለ ብዙዎች ቤዛ ለማድረግ እንጂ ተገዶ አይደለም (ዮሐንስ 10፡11፣ 10፡15፣ 10፡17-18 15፡13፣ ማርቆስ 10፡45)፡፡ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው አስቀድሞ መናገሩን በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ እናነባለን (ማቴዎስ 12፡38-40፣ 16፡21፣ 17፡22-23፣ 20፡18-10፣ 21፡33-46፣ 26፡21-32፣ 26፡36-40፣ 26፡61-62፣ ማርቆስ 8፡31፣ 9፡9፣ 9፡30-31፣ 10፡33-34፣ 10፡45፣ 12፡1-12 14፡18-28፣ 14፡32-40፣ ሉቃስ 9፡22፣ 11፡29-30፣ 13፡32-33፣ 20፡9-19፣ 22፡15-20፣ 22፡39-46፣ ዮሐንስ 3፡13-14፣ 8፡28፣ 12፡32-34)፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ሞት በሰይጣን የታቀደ አልነበረም፡፡ ሰይጣንም ሆነ በአፅናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ፍጥረት በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ፣ በእርሱ ሉኣላዊ ሥልጣን ስር እንደሚገኝና እግዚአብሔር አምላካችን የሁሉ የበላይ እንደሆነ ክርስትና ያስተምራል (ዳንኤል 4፡35፣ 2ዜና 29፡14፣ 20፡6፣ ዘዳግም 10፡14፣ ነህምያ 9፡6፣ ራዕይ 4፡11)፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ማሰብና የእግዚአብሔር ተፎካካሪ አካል አድርጎ መሳል የእግዚአብሔርን ሉኣላዊ ሥልጣን ያለማወቅ ነው፡፡ ሰይጣን የይሁዳን ክፉ ምኞት በመጠቀም ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ሲያደርገው የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ዕቅድ በመረዳትና የራሱን የሽንፈት መንገድ እያመቻቸ መሆኑን በማወቅ አልነበረም፡፡ ይህንን በማድረጉ እንደ ይሁዳ ሁሉ ሰይጣንም ራስን የማጥፋት ተግባር ፈፅሟል፡፡ የኢየሱስ ሞት ሰይጣንን አዋርዶታ፡፡ ትንሣኤው ደግሞ እስከ ወዲያኛው ኃይሉን አንኮታኩቶታል! ሰይጣን በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ለማበላሸት ቢሞክርም እግዚአብሔር ግን የዕውቀቱን ምጡቅነት እና የጥበቡን ልቀት በማሳየት ሰይጣንን ሲያዋርደው እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ሰይጣን ኢዮብን ሲፈትነው ፃድቅ የሆነውን ኢዮብን ከእግዚአብሔር በመለየት ለማጥፋ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የሰይጣንን ፈተና የኢዮብን እምነትና ፅድቅ ለመግለጥ እና ለትውልዶች ሁሉ ማስተማርያ ለማድረግ ተጠቅሞበታል፡፡ ሰይጣንም ዕቅዱ ግቡን ሳይመታ ቀርቶ አፍሯል፡፡ የኢየሱስም ስቅለት እንደዚያው ነው፡፡ የተዋረደው ሰይጣን ዛሬ በእነ አሕመዲን በኩል በመምጣት ውርደቱንና ሽንፈቱን ለማስተባበል ቢሞክር አንሰማውም፣ አንቀበለውም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ