ኢየሱስ አምላክ ከሆነ “ከፍጥረት በፊት በኩር” ለምን ተባለ?

 


4. ቆላሳይስ 1፡15 ላይ ስለ ኢየሱስ “እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤” ይላል፡፡ እንዲሁም በሮሜ 8፡29 ላይ “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፡፡ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው” ይላል፡፡ ኢየሱስ “የፍጥረት በኩር” ወይም መጀመሪያ የተፈጠረ ከሆነ እንዴት ከፍጡርነት አልፎ ፈጣሪ ይሆናል? ይህ ሁኔታ የክርስቶስን ማንነት እንድንፈትሽ አይጋበዝምን?

ይህ የሙግት ሐሳብ “ከይሖዋ ምስክሮች” (አርዮሳውያን) የተቀዳ ነው፡፡ በአርዮሳውያን ትምህርት መሠረት ኢየሱስ በይሖዋ የተፈጠረ የመጀመርያው ፍጡር ነው፡፡ ነገር ግን የግሪኩን ንባብ፣ ማለትም አዲስ ኪዳን መጀመርያ የተጻፈበትን ቋንቋ እንዲሁም “በኩር” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለባቸውን የተለያዩ አውዶች ስንመለከት የእነርሱን ሐሳብ የሚደግፍ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ከዚያም አልፎ ኢየሱስ የመጀመርያው ፍጡር ነው የሚለው አባባል ፍጡርን ከጊዜና ከስፍራ ስለሚያስቀድም ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ከፈጣሪ በስተቀር ፍጡራን ሁሉ በጊዜና በቦታ የተገደቡ በመሆናቸው ኢየሱስ ፍጡር ከሆነ እንደ ሌሎቹ ፍጡራን ጊዜና ስፍራ ከተፈጠሩ በኋላ ነበር መፈጠር የነበረበት፡፡

አዲስ ኪዳን አስቀድሞ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ “መጀመርያ የተፈጠረ” ለሚለው ሐረግ አቻ ቃል “ፕሮቶኪቲሲስ” የሚል ሲሆን “በኩር” ለሚለው ደግሞ “ፕሮቶቶኮስ”[1] የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ የመጀመርያ ፍጡር መሆኑን ሊነግረን ፈልጎ ቢሆን ኖሮ የመጀመርያውን ቃል ይመርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን መጀመርያ መፈጠርን የሚያሳየው ቃል በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኢየሱስን ለማመልከት ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ይላል እንጂ “ኢየሱስን ፈጠረ” አይልም (ዘፍጥረት 1፡1)፡፡ “በኩር” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁለት መንገዶች ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የመጀመርያው በጊዜ ቀዳሚነትን ለማመልከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የበላይነትን ወይም ላዕላይ ደረጃን ለማመልከት ነው፡፡ ሁለተኛውን ሐሳብ የሚደግፉ ሁለት ጥቅሶችን እንጠቅሳለን፡-

“ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት… እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል” (መዝሙር 89፡20፣ 27)፡፡

ዳዊት በውልደት የቤቱ ታናሽ እንደሆነና ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከምድር ነገሥታት ሁሉ በኩር እንደሚያደርገው ተናግሯል፡፡

“…እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና” (ኤርምያስ 31፡9)፡፡

ኤፍሬም ሁለተኛው የዮሴፍ ልጅ መሆኑ ይታወቃል (ዘፍጥረት 49፡13-19)፡፡

ብኩርና ወራሽነትንና የበላይነትን ስለሚያመለክት ከአንዱ ወደ ሌላው ሊተላለፍ የሚች መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዕብራውያን 12፡16)፡፡

አሕመዲን በጠቀሷቸው ክፍሎች ውስጥ “በኩር” የሚለው ቃል ኢየሱስ የበላይና ወራሽ መሆኑን ለማመልከት እንጂ የመጀመርያ ፍጡር መሆኑን ለማመልከት አልገባም (ሮሜ 8፡17፣ 29፣ ዕብራውያን 1፡1-3፣ ማርቆስ 12፡6-8)፡፡ ከአርዮሳውያን በተኮረጀው የጠያቂው ሙግት መሠረት ኢየሱስ የመጀመርያው ፍጡር ቢሆን በአላህ አማካይነት በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንደተፈጠረ የሚናገረው የእስልምና ትምህርት ውድቅ ስለሚሆን ሙግታቸው እስልምናን የሚያፈርስ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ