እውነተኛው አምላክ ኢየሱስ ወይስ እግዚአብሔር?

 


5. እውነተኛ አምላክ ኢየሱስ ነው ወይንስ እግዚአብሔር? የሚከተሉት ጥቅሶች እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ይገልጻሉ ፦

  • ? ”እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ክብር ይሁን አሜን፡፡” (ሮሜ 16:27) ይህ ጥቅስ “እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ” ይላል ጥበበኛው የኢየሱስ አምላክ ብቻ ከሆነ ኢየሱስ ምን ሊባል ነው?

እግዚአብሔር አብ ብቻ ጥበበኛ አምላክ ከሆነ ኢየሱስ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡- “ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው (1ቆሮንቶስ 1፡24)፡፡ እግዚአብሔር አብ ጥበብ አልባ የነበረበት ጊዜ ባለመኖሩ ኢየሱስን ከእርሱ ልንነጥል አንችልም፡፡

  • ? “እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም፡፡” (ኤርምያስ 10፡10)

ይህ ጥቅስ ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነውንና እውነተኛ አምላክ የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያገለለ ስለመሆኑ ጠያቂው ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ጌታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛ አምላክ ተብሎ ተጠርቷል፡- “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው” (1ዮሐንስ 5፡20)፡፡

  • ? ኢየሱስ እንዲህ ይላል“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት” (የዮሐንስ ወንጌል 17:3)፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለአምላኩ ሲፀልይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት፡፡” ለምን አለ? ኢየሱስ እውነተኛው አምላክ ራሱ ሳይሆን የላከው አምላክ መሆኑን እንዴት ገለፀ?

ሙስሊም ሰባኪያን የኢየሱስን አምላክነት በማወጅ ከሚጀምረው መጽሐፍ፣ ከዮሐንስ ወንጌል ውስጥ አምላክነቱን የሚፃረር ሐሳብ መፈለጋቸው በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ የዘለዓለም ሕይወት የሚገኘው እርሱንና አብን በማወቅ መሆኑን “ካይ”[2] የሚለውን የግሪክ መስተፃምር በመጠቀም ከአብ ጋር ያለውን እኩልነት ግልፅ አድርጓል፡፡ አንድ ሰው የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ፈጣሪና ፍጡርን አንድ ላይ ደምሮ ማወቅ አለበት የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ እስልምናም ቢሆን እንደርሱ አያስተምርም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምዕራፉን በሙሉ ስናነብ ጌታችን ስለ ራሱ የተናገራቸው ብዙ ነገሮች አምላክነቱን የሚያሳዩና ለጠያቂው የተሳሳተ ትርጓሜ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው፡-

  • ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው (The Son, not a son) (ቁ.1-2)፡፡
  • የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣል (ቁ.1-2)፡፡ (ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል ማን ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔርስ ይህንን ችሎታ ለፍጡራን ያጋራልን?)
  • ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በክብር ከአብ ጋር ነበር (ቁ.5)፡፡
  • አብ እንዲያከብረው ጠይቋል (ቁ.1-2)፡፡ ፍጡር እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የማቅረብ መብት አለውን?
  • የአብ የሆነው ሁሉ የእርሱ መሆኑን ተናግሯል (ቁ.10)፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር በድፍረት መናገር የሚችል ከፍጡራን መካከል ሊገኝ ይችላልን?

አሕመዲን ጀበል ይህ ሁሉ የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳይ ሐሳብ ከሞላበት ምዕራፍ ውስጥ አንድ ጥቅስ ነጥለው በማውጣት በራሳቸው የነጠላ አሃዳዊነት መነፅር በመመልከት የኢየሱስን አምላክነት ለመካድ ይሞክራሉ፡፡ የሚመቸንን ብቻ በራሳችን መንገድ በመተርጎም የማይመቸንን መጣል ህሊና ቢስነት መሆኑን እያስገነዘብን ይህ ጥቅስ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን ለማሳየት ፈፅሞ ሊጠቀስ የማይችልባቸውን አምስት ምክንያቶች እንደሚከተለው እናስቀምጣለን፡-

  • በክርስትና አስተምህሮ መሠረት በሥላሴነት የሚኖረው አንዱ አምላክ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ የአጠቃላዩ ገንዘብ (General Property) የእያንዳንዱ ገንዘብ (Particular Property) በመሆኑ የብቸኛው ግፃዌ መለኮት ተካፋይ የሆነ እያንዳንዱ የሥሉስ አካል ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ ይህ እርስ በርሱ እንደማይጣረስ ለመረዳት መሠረታዊ የሥነ አመክንዮ ዕውቀት በቂ ነው፡፡
  • ኢየሱስ በአካል ከአብ ልዩ ቢሆንም የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ቃል (ሎጎስ) ስለሆነ በመለኮት ከአብ የተነጠለ ባለመሆኑ ምክንያት አብ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ከሆነ የአብ ዘለዓለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው (ዮሐንስ 1፡1)፡፡
  • ኢየሱስ ክርስቶስ አብን ብቸኛ እውነተኛ አምላክ እያለ ያለው ከሌሎች አማልክት አንፃር እንጂ በመለኮት ከእርሱ ጋር አንድ ከሆነው ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በማነፃፀር አይደለም፡፡
  • ይህ ሐሳብ የተነገረው ሥጋ በመሆን ወደ ምድር ከመጣው ከወልድ ዕይታ (Perspective) አኳያ እንጂ ከሌሎች ሰዎች ዕይታ አኳያ አይደለም፡፡
  • ወልድም “ብቸኛ” ተብሎ የተጠራባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህ የቋንቋ አጠቃቀም ሌሎች የሥላሴ አካላትን ለማግለል የታለመ አለመሆኑን ግልፅ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ፡-“ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ” (ይሁዳ 1፡4)፡፡

የጠያቂውን ሙግት ከተቀበልን ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ብቻውን ያለ ንጉሥና ጌታ እንደሆነ በመነገሩ ምክንያት አብ ጌታ አይደለም ልንል ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያን ከጠያቂው በተፃራሪ እንዲህ ዓይነቱ የቋንቋ አጠቃቀም ከእግዚአብሔር ማንነት አኳያ ችግር ሊፈጥር እንደማይችል ተገንዝበዋል፡፡ ጠያቂው የነጠላ አሃዳዊነት መነፅራቸውን ማውለቅ እስካልቻሉ ድረስ ይህንን ግንዛቤ ሊያገኙ አይችሉም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ