ጌታ የተባሉ ብዙዎች አሉ፤ ታድያ ኢየሱስ ጌታ መባሉ ለአምላክነቱ እንዴት ማስረጃ ይሆናል?

 


13. የጥያቄው የመጀመርያ ክፍል በቁጥር 7 ላይ መልስ የተሰጠበትን ሐሳብ የሚደግም በመሆኑ ታልፏል፡፡ የጥያቄው ቀጣይ ክፍል እንዲህ ይላል፡- ኢየሱስ “ጌታ” ስለተባለ አምላክ ሊባል ይቻላልን? እንዲህማ ከተባለ በመጽሐፍ ቅዱስ እነ ሙሴ (ዘኊልቁ 12፡11፣ ዘኊልቁ 11፡28) መላዕክት (ዘካርያስ 6፡4 ኢያሱ 5፡13-14)፣ ዮሴፍ (ዘፍጥረት 42፡33፣ ዘፍጥረት 45፣8-9)፣ ዳዊት (1ኛ መጽሐፍ ነገስት 1፡11-13፣ ኢዮአብ (2ኛ ሳሙኤል 11፡11)፣ ኤልያስ (1ኛ ነገስት 18 ፡7) እና ሳኦል (1ኛ ሳሙኤል 24፡8 ) “ጌታ” ተብለው የተጠሩትን ሁሉ “ጌታ” ስለ ተባሉ ለምን አምላክ አንላቸውም?

“ጌታ” መባል ብቻውን አምላክ እንደማያሰኝ ያስማማናል፡፡ ነገር ግን ቃሉ የተጠቀሰበት አውድ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎችና መላእክት አምላክ ተብለው ሊጠሩ የማይችሉበት ምክንያት አውዱ ክቡራን ፍጥረታት እንጂ ፈጣሪ መሆናቸውን ስለማያሳይ ነው፡፡ አሕመዲን በዚህ ጥያቄያቸው የመጀመርያው ክፍል ላይ 1ቆሮንቶስ 8፡6 ላይ አብ “አምላክ” ተብሎ ኢየሱስ ግን “ጌታ” መባሉ ኢየሱስ እንደ አብ አምላክ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ለመሟገት ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን ጥቅሱ ኢየሱስ ፈጣሪ መሆኑን እንደሚናገር አላስተዋሉም፡፡ እኛን ጨምሮ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረው አካል አምላክ ካልተባለ ምን ሊባል ነው? ሐዋርያት ይህንን ስለተረዱ ነው ክርስቶስ አምላክ መሆኑን የመሰከሩት (ዮሐንስ 20፡27-29፣ ቲቶ 2፡12-13)፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ