“ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው” አምላክ ከሆነ ታድያ እንዴት “ኢየሱስ ሞትን ድል አደረገ“ ይባላል?

 


18. እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ “ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው” አምላክ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እነርሱም ፡- ሮሜ 10፡9፣ ገላቲያ1፡1፣ ኤፌሶን 1፡20-21፣ ቆላስይስ 2፡11-12፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡21፣ የሐዋርያት ሥራ 2፡23-24፣ 3፡15፣ 10፡40፣ 13፡33-34፣ 3፡26፣ 4፡10፣ 13፡37፣ 6፡14 ናቸው፡፡ በቀረበው ማስረጃ “ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው” አምላክ ከሆነ ታድያ እንዴት “ኢየሱስ ሞትን ድል አደረገ “ይባላል? እንዴትስ “በሞት ላይ ስልጣን ስላለው ተነሳ” ልንል እንችላለን?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ትንሣኤ የሦስቱም የሥሉስ አካላት ተግባር እንደነበር ይናገራል፡፡ ጠያቂው በጥያቄያቸው ውስጥ በጠቀሷቸው ጥቅሶች መሠረት የአብ ተግባር መሆኑ ተነግሯል፡፡ የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ የኢየሱስ ተግባር እንደነበር ይነግሩናል፡-

“ስለዚህ አይሁድ መልሰው፦ ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው፡፡ ስለዚህ አይሁድ፦ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ” (ዮሐንስ 2፡18-22)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ አይሁድ ቢገድሉት በሦስት ቀን ውስጥ መልሶ ራሱን እንደሚያስነሳ ተምሌታዊ በሆነ መንገድ እየነገራቸው ነው፡፡

“ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ” (ዮሐንስ 10፡17-18)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ በገዛ ፍቃዱ እንደሚሞትና ራሱን በራሱ እንደሚያስነሳ፤ የመሞትም ሆነ የመነሳት ሥልጣን የእርሱ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይናገራሉ (ሮሜ 8፡11፣ ሮሜ 1፡3-4)፡፡

ከነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር የክርስቶስ ትንሣኤ ሦስቱም የሥሉስ ቅዱስ አካላት የተሳተፉበት መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ አብ ኢየሱስን እንዳስነሳው መነገሩ ኢየሱስን ከአብ የሚያሳንስ አይደለም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ