“ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ሚለው ጥቅስ ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች
23. ዕብራውያን 1፡13 ላይ“እግዚአብሔር፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከቶ ለማን ነው?” ይላል፡፡ ይህ ጥቅስ እንደሚነግረን “በቀኜ ተቀመጥ ” የተባለው ኢየሱስ ብቻ ከሆነ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያሻል ፡-
ሀ. ኢየሱስም አምላክ ነው እየተባለ እንዴት በጊዜ ተወስኖ ከእግዚአብሔር ቀኝ እንዲቀመጥ ይፈቀድለታል? ከአምላክ ማን በልጦ ይህን ያዘዋል?
ክርስቶስ ፍጥረትን የመዋጀት ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ይህም ትቶት ወደመጣው ክብሩ መመለሱን የሚያመለክት ተምሳሌታዊ ንግግር እንጂ እግዚአብሔር መንፈስ በመሆኑ በዚህ መልኩ ሊገለፅ የሚችል ግራና ቀኝ አለው ማለት አይደለም፡፡ ቀኝ በመጽሐፍ ቅዱስ የኃይልት፣ የከፍታ፣ የፅድቅ፣ የመልካምነት፣ የአንድነት፣ ወዘተ. ተምሳሌት ነው (ዘጸአት 15፡6፣ 12፣ መዝሙር 20:6፣ 98፡1፣ መክብብ 10፡2፣ ኢሳይያስ 48፡13፣ 62፡9፣ ማቴዎስ 26:4, ማርቆስ 14፡62፣ ሉቃስ 22፡69፣ ገላትያ 2፡9፣ ዕብራውያን 1፡3)፡፡
ለ. ጠላቶቹን የእግሩ መረገጫ ካደረገ በኋላ ኢየሱስን እግዚአብሔር ከቀኙ ያነሳዋል ማለት ነው፡፡ ለምን? ቢሉ “የእግር መረገጫ እስከማደርግልህ” ነው ያለውና፡፡ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ቀኝ ከተነሳ በኋላ ምን ይሆናል?
“የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ” ስለተባለ ከዚያ በኋላ ይነሳል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡-
“እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና” (ዘፍጥረት 28፡15)፡፡ ከዚያ በኋላ ይተወዋል ማለት ነው?
“የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” (1ሳሙኤል 6፡23)፡፡ ከዚያ በኋላ መውለድ ትችላለች ማለት ነው?
“እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ” (ማቴዎስ 5፡18)፡፡ ከተፈፀመ በኋላ ያልፋል ማለት ነው?
“እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡20)፡፡ ከዚያ በኋላ ይለያቸዋል ማለት ነው?
“እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ” (የሐዋርያት ሥራ 7፡17-18)፡፡ ከዚያ በኋላ መብዛት አቆሙ ማለት ነው?
እንዲህ ዓይነት አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቁርኣንም ውስጥ ይገኛል፤ ለምሳሌ፡-
“አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡” (ሱራ 3፡55)፡፡ ከዚያ በኋላ የበታቾች ይሆናሉ ማለት ነው?
“እርግማኔም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ባንተ ላይ ይኹን” (ሱራ 38፡37)፡፡ ከፍርዱ ቀን በኋላ የአላህ እርግማን ከሰይጣን ላይ ይነሳል ማለት ነው?
ስለዚህ “እንዲህ እስኪሆን ድረስ” የሚል ሐረግ ስለገባ ብቻ ድርጊቱ የሆነ ጊዜ ላይ ያቆማል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተባለው ነገር እስኪፈፀም ድረስ ድርጊቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የሚገልፅ የተለመደ አባባል ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥም በዚሁ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ሐ. ኢየሱስ ከመላእክት ቢለይም ያው ከእግዚአብሔር እገዛን የሚሻ አይደለምን?
ኢየሱስ የመላእክት ጌታ መሆኑ ጠያቂው በጠቀሱት በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ተነግሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆን መላእክት ግን የእርሱ ተፈጣሪዎችና አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህንን ነጥብ ከቀጣዩ ጥያቄ በኋላ ያሰፈርነው የዕብራውያን 1 ሙሉ አውድ የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል፡፡
መ. አምላክ እግዚአብሔር ነው ወይንስ በጊዜ ገደብ ከ “ቀኝ” እንዲቀመጥ የተፈቀደለት ኢየሱስ?
የኢየሱስ በቀኝ መቀመጥ በጊዜ የተገደበ ስለመሆኑ ጠያቂው ያቀረቡት ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁርኣን መሠረት ውድቅ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይህ ጥያቄ ከነጠላ አሃዳዊነት አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ አብ አምላክ ከሆነ ኢየሱስ አምላክ ሊሆን አይችልም የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን አብም ኢየሱስም የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት በመሆናቸው አብ አምላክ መሆኑ ኢየሱስን አምላክ እንዳይሆን አያደርገውም፡፡ ለዚህ ነው የዕብራውያን ጸሐፊ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ኢየሱስ አምላክ፣ ጌታ፣ የሁሉ ፈጣሪና ዘለዓለማዊ መሆኑን እግዚአብሔር አብ እንደመሰከረ የጻፈው፡፡ አሕመዲን አንዷን ጥቅስ ብቻ ነጥለው ከሚጠቅሱ ሙሉውን ቢጠቅሱ ኖሮ እግዚአብሔር አብ ስለልጁ ጌትነት፣ አምላክነት እና ፈጣሪነት የመሰከረውን ማየት በቻሉ ነበር፡፡ እሳቸው ቆርጠው የጣሉትን ታማኝነት ማጉደላቸውን የሚያጋልጠውን የምዕራፉን ቀዳማይ ክፍል ጨምሮ ሙሉውን ምዕራፍ እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡-
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል፡፡ ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡ ስለ መላእክትም፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል፡፡ ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡ ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን? (ዕብራውያን 1)፡፡
የተከበሩት ጠያቂያችን የኢየሱስን አምላክነት፣ ፈጣሪነት፣ የመላእክት ጌታ መሆኑን እና ዘለዓለማዊነቱን እንዲህ ባለ ሁኔታ ከሚናገር ክፍል ውስጥ አምላክነቱን የሚቃወሙበትን ሐሳብ መፈለጋቸው መታወር እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?