«ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል» ከተባለ ኢየሱስ እንዴት አምላክ ይባላል?

 


31. መጽሐፍ ቅዱስ ላይ «ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፡ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፡ መጀመሪያ በኩራት የሆነው ክርስቶስ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት፡፡ ከዚያም ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነገሥ ይገባዋልና፡፡» (1ኛ ቆሮንቶስ 15:22-24) እንዲሁም «ሁሉ ከተገዛለትበኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉንላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል» ይላል፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 15:28) (የ1980 አትም) ኢየሱስ ሥልጣን እንደ ተሰጠው ተናግሯል፡፡ ግን ይህ ጥቅስ በሚገርም መልኩ ስልጣኑን እንደሚያስረክብ ይገልፃል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ከስልጣን የሚወርድ ከሆነ ምኑ ላይ ነው የእርሱ አምላክነት? ኢየሱስ ከስልጣኑ ወርዶ ለአምላኩ የሚገዛ ከሆነ ምኑን አምላክ ሆነ? ክርስቲያኖች አሻፈረን አሉ እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለም አምላኩን ሲገዛ አልነበረም? ኢየሱስ የሚነግሠው በጥቅሱ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋል፡፡” በማለት እንደተገለፀው ከሆነ የእርሱ “ንግስና” በጊዜ የተገደበ ነው፡፡ አምላክ ግን ከዘለዓለም እሰከ ዘለዓለም ንጉስ ነው፡፡ ስልጣንን ለማንም አያስረክብም፡፡ ኢየሱስ ግን “መንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክበው፡ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡” ተብሎ እንደተገለፀው ስልጣኑን ያስረክበዋል፡፡ ታዲያ ኢየሱስን አምላክ ልንለው እንዴት ይቻለናል? ጥቅሱ እግዚአብሔርን ነው እንጂ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን” ያለው ኢየሱስን አይደለም፡፡ አልያም “አንድ እግዚአብሔር የሚሆኑት አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን” አላለም፡፡ ታዲያ እንዴት ኢየሱስ አምላክ ሊባል ይችላል?

1ኛ ቆሮንቶስ 15፡28 ላይ የኢየሱስን ለአብ መገዛት ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ሁፖታጊሰታይ” የሚል ሲሆን ደረጃን እንጂ ባሕርይን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ የግሪክ ቃል የሚነበብበት ድምፀት ወልድ ተገዶ ወይም ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳይሆን በፍቃደኝነት ራሱን በራሱ ለአብ እንዳስገዛ ያሳያል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የግሪክ ቋንቋ ሊቅ የሰጡትን ሐተታ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ይመልከቱ፡፡[6]

በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት ልጅ ለአባት እንደሚገዛ ሁሉ ወልድም ለአብ ይገዛል፡፡፡ ነገር ግን አባትና ልጅ እንደ ሰው ያላቸው እሴት (Value) እኩል እንደሆነ ሁሉ አብና ወልድም እኩል ናቸው፡፡ ወልድ በአምላካዊ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ አይደለም፡፡ አብም በአምላካዊ ባሕርዩ ከወልድ የበለጠ አይደለም፡፡ ስለ ሥላሴ አካላት እኩልነት ስንናገር በመለኮታዊ ባሕርይ ማለታችን እንጂ በሥራ ድርሻቸው (Function) ማለታችን አይደለም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ለአብ መገዛቱን መናገሩ የሥላሴን አስተምህሮ የሚያፀና እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ የኢየሱስ ፍፁም ሰው መሆን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ፍፁም ሰው የሆነውን ደግሞም ከሙታን የተነሳውንና የከበረውን ሥጋውን በመተው አይደለም፡፡ ይህ ማለት ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆኖ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ለአብ እንደሚገዛ ለመነገሩ እንደ ተጨማሪ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ኢየሱስ ከሥልጣን የሚወርድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ንግሥናውስ ይሻር ይሆን? የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም ከማስቀመጣችን በፊት እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ ንግሥና በተመለከተ ምን እንደሚል እንይ፡-

“እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” (ሉቃስ 1፡32-33)፡፡

“በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” (ዳንኤል 7፡13-14 ከማርቆስ 14፡61-62 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡

“ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው” (ዕብራውያን 1፡8)፡፡

“እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና” (2ጴጥሮስ 1፡11)፡፡

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” (ኢሳይያስ 9፡6-7)፡፡

“ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ” (ራዕይ 11፡15)፡፡

ሌላ ቦታ ላይ ቅዱሳን የሚወርሱት መጪው መንግሥት የአብ እና የወልድ መሆኑ ተነግሯል፡-

“ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም” (ኤፌሶን 5፡5)፡፡

ስለዚህ መጪው መንግሥት የክርስቶስ እና የእግዚአብሔር አብ መሆኑ ከተነገረ ኢየሱስ ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለአብ ማስረከቡ የተነገረው ለአብ መገዛቱን አፅንዖት ለመስጠት እንጂ ንግሥናው ጊዜያዊ እንደሆነ ለማመልከት አይደለም፡፡ ከዚህ ትርጓሜ በተፃራሪ መጽሐፍ ቅዱስ በመጪው ዓለም አብ እና ወልድ አንድ ዙፋን እንደሚኖራቸው ይናገራል፡-

“በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን [ነጠላ] የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ፡፡ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡ ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን [ነጠላ] በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፡፡” (ራዕይ 22፡1-7)፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ