ኢየሱስ ስለ ራሱ “እውነቱን የነገርኳችሁን ሰው” ካለ ለምን አምላክ ትሉታላችሁ?

 


35. በዮሐንስ ወንጌል 8:40 ላይ “ኢየሱስ እንዲህ ሲል ለአይሁዶች ተናገረ፡- «ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፡» ይላል፡፡ ታዲያ እርሱ “ከእግዚአብሔር የሰማሁት፡” ሲል እርሱ እንደማን ሆኖ ነው ከእግዚአብሔር የሚሰማው? እንደ ክርስትና አስምህሮት “እግዚአብሔር፡” ማለት ሥላሴ የሆነና ኢየሱስን የሚጨምር አይደለምን? ስለ ኢየሱስ ከርሱ የበለጠ ክርስቲያኖች ያውቃሉ ማለት ነው? እርሱ ስለ ራሱ “እውነቱን የነገርኳችሁን ሰው” ሲል “ሰው” መሆኑን ገልጿል፡፡ ክርስቲያኖች ግን “አምላክ” ይሉታል፡፡ ማንኛው ነው የዋሸው?

አሕመዲን ኢየሱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ፍፁም ሰው በመሆን ከአብ እየሰማ መሲሃዊ አገልግሎቱን ሲፈፅም ነበር፡፡ አምላክ እንደመሆኑ የዘለዓለምን ሕይወት እንደሚሰጥ (ዮሐንስ 10፡27-28)፣ በምድር ላይ እንኳ እያለ በዚያው ቅፅበት በሰማይ እንደሚኖር (ዮሐንስ 3፡13)፣ ፀሎትን እንደሚሰማና እንደሚመልስ (ዮሐንስ 14:13-14)፣ በመጨረሻው የትንሣኤ ቀን በሁሉም ላይ እንደሚፈርድ (ማቴዎስ 25፡30-46)፣ ለአብ የሚገባው ክብር ሁሉ ለእርሱም እንደሚገባ (ዮሐንስ 5፡22-23)፣ ወዘተ. ቢናገርም ነገር ግን ደግሞ እንደ ሰው ከአብ እንደሚሰማና የአብን ፈቃድ ብቻ እደሚፈፅም ተናግሯል፡፡ አሕመዲን እነዚህ ሁለቱ የኢየሱስ ባሕርያት እና ግብራት ባይምታቱባቸው ኖሮ ድንግርታ ውስጥ ባልገቡ ነበር፡፡ አሁን ግን የዚህ ሃቅ ውሉ ስለጠፋባቸው በጨለማ ውስጥ እንደሚዳብስ እውር ሆነዋል፡፡ እስኪ ኢየሱስ ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ሁለት ነጥቦች ከዚህ ምዕራፍ እንመልከት፡-

“እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው፡፡ እንግዲህ፦ አንተ ማን ነህ? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ (ዮሐንስ 8፡24-26)፡፡

“አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው፡፡ አይሁድም፦ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው፡፡ ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡” (ዮሐንስ 8፡56-59)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ ከመጀመርያው ለአይሁድ የተናገረው እንደሆነና “እኔ አለሁ” በማለት ተናግሯል፡፡ የእነዚህ ንግግሮች ትርጉም ስለገባቸው አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከያሕዌ እግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊናገራቸው የማይችላቸውን ንግግሮች በመናገር ለአይሁድ አምላክነቱን ግልፅ አድርጓል፡፡ “እኔ አለሁ” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ “እኔ ነኝ” ተብሎ ቢተረጎም የበለጠ ትክክል ይሆናል፡፡ ግሪኩ “ኢጎ ኤይሚ” የሚል ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተተረጎመው የሰብዓ ሊቃናት (ሰብቱጀንት) ትርጉም ኢሳይያ 48፡12 ላይ የሚገኘውን “ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ” በማለት ያሕዌ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል በተመሳሳይ መንገድ ተርጉመዋል፡፡ እንደርሱ በማለት መናገር የሚችለው ያሕዌ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው አይሁድ የኢየሱስን ንግግር እንደ ክህደት በመቁጠር ሊወግሩት ድንጋይ ያነሱት፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ