ክርስቶስ በአምላክ የሚላክ፣ ሟች፣ ምንንም ማድረግ የማይችል ከሆነ እንዴት ዘለዓለማዊ አምላክ ይሆናል?

 


43. በመጽሐፍ ቅዱስ አብ ኃያል፣ አዳኝ፣ ላኪ፣ ፈጣሪ፣ ልዑል መሆኑ ሲገለፅ ኢየሱስ ደግሞ ከራሱ ምንም ማድረግ የማይችል ኃይል የለሽ ሟች እና መልዕክተኛ መሆኑን እናነባለን ፡፡ እንደሚባለው ክርስቶስ በአምላክ የሚላክ፣ ሟች፣ ምንንም ማድረግ የማይችል ከሆነና ሁሉም ነገር በአብ የተሠጠው ከሆነ እንዴት ዘለዓለማዊ አምላክ ይሆናል?

በዚህ ጥያቄ ውስጥ የተዘረዘሩት ነጥቦች ሁሉ ቀደም ሲል መልስ የተሰጠባቸው በመሆኑ ራሳችንን መድገም ጉንጭ ማልፋት ይሆንብናል፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ የተዘረዘሩት የአብ ባሕርያት ሁሉ እንዳሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን በመስጠት ይህንን ጥያቄ እናልፈዋለን፡-

  • ሃያል ስለመሆኑ፡- “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳይያስ 9፡6)፡፡
  • አዳኝ ስለመሆኑ፡- “…እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴዎስ 1፡21)፡፡
  • ላኪ ስለመሆኑ፡- “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ” (ማቴዎስ 13፡41)፡፡ “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” (ዮሐንስ 16፡7)፡፡
  • ፈጣሪ ስለመሆኑ፡- “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” (ዮሐንስ 1፡3)፡፡ “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፡፡” (ቆላስይስ 1፡15)፡፡
  • ልዑል ስለመሆኑ፡- “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል” (ቆላስይስ 2፡9-10)፡፡ “እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ” (ራዕይ 17፡14)፡፡ “እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” (1ጴጥሮስ 3፡22)፡፡ እነዚህ ሁሉ የሉዓላዊነት ባሕሪያት የፈጣሪ ብቻ ስለመሆናቸው የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቦ መረዳት ይቻላል (1ዜና 29፡11፣ መዝሙር 83፡18 95፡3-7፣ 97፡5-9፣ 113፡5፣ ዘፍጥረት 14፡19-22)፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ