ኢየሱስ አምላክ ከሆነ “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር” እንዴት ይባልለታል? አምላክ ይጨነቃል?

 


50. ሉቃስ 22:43-44 ላይ «መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታው፡፡ አጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፡፡ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር፡፡» ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ከሆነ ላለመሞት ፈርቶ ይሄን ያህል ሲጨነቅ የአምላክ ፍጡር የሆነውን መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት ከሚያበረታታው የራሱ አምላካዊ ባህሪው አለለት አይደለምን? ለምን እራሱን አያበረታውም ነበር? “አምላክ” እጅግ ሲጨነቅ መልአክ ያበረታታዋል ማለት ነውን? ምንስ አስጨነቀው? ክርስቲያኖች እንደሚነግሩን ሞትን የፈጠረው ራሡ አይደለምን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው እንደመሆኑ ከፊቱ የነበረው የመስቀል መከራ አስፈርቶታል፡፡ የመስቀሉን የሥቃይ ስሜት በሙሉ በሥጋው ያስተናግዳል፡፡ ከዚህም በላይ የመላውን ዓለም ኃጠአት በመሸከም ነው የሚሰቃየው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ስሜት አልባ ሮቦት ሳይሆን ፍፁም ሰው በመሆን ሰዎች ሊሰማቸው በሚችለው የሥቃይ ስሜት ሁሉ ውስጥ በማለፍ ነው ሊሞት ያለው፡፡ በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደመሆኑ የስቃይ ስሜቱንም ሆነ ፍርሃቱን ማስወገድ ይችል ነበር ነገር ግን ያንን ሊያደርግ አልወደደም፡፡ በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ በሮማውያን ልማድ መሠረት የሥቃይ ስሜቱን ሊቀንስ የሚችል መጠጥ ሲሰጠው ሊጠጣው አለመፈለጉ የተዘገበው ያለምክንያት አይደለም (ማርቆስ 15፡23)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ኃይሉን ሳይጠቀም ፍርሀቱን፣ ጭንቀቱንም ሆነ ሥቃዩን ሊቀበል በመወሰኑ ምክንያት ሰብዓዊ ባሕርዩ እስከ መስቀል ይሄድ ዘንድ የሚያበረታታው መልአክ ከአብ ዘንድ ተልኮለታል፡፡ መለኮታዊ ሥልጣኑን ለመጠቀም አለመፈለጉ መለኮት አለመሆኑን አያሳይም፡፡ አሕመዲን ኢየሱስ ሞትን እንደፈጠረ ክርስቲያኖች ማመናቸውን ከየት እንደሰሙ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በቁርኣን መሠረት አላህ ሞትንና ሕይወትን እንደፈጠረ ስለተነገረ መጽሐፍ ቅዱስም ተመሳሳይ ትምህርት ያለው መስሏቸው ይሆናል (ሱራ 67፡2)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞት የሰዎች ያለመታዘዝ ውጤት እንጂ የእግዚአብሔር ፍጡር ስለመሆኑ የተጻፈ ነገር የለም፡፡ ጨለማ የብሃን አለመኖር እንደሆነ ሁሉ ሞትም የሕይወት አለመኖር ነው፡፡ እግዚአብሔር ብርሃንን እንጂ ጨለማን እንዳልፈጠረ ሁሉ ሕይወትን እንጂ ሞትን አልፈጠረም፡፡ የሕይወት እስትንፋስ የሆነችው ነፍሳችን ከሥጋችን ስትለይ ሥጋችን ይሞታል፡፡ ነፍሳችን ደግሞ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ስትለይ ትሞታለች፡፡ እግዚአብሔር ሞትን ፈጥሯል የምንል ከሆነ የሞት ምክንያት የሆነውንም ኃጢአትን ፈጥሯል ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ቅዱስ ከሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ይጣረሳል፡፡ ጠያቂያችን የራሳቸውን የተወላገደ አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባይጭኑ መልካም ነው፡፡