ክርስቲያኖች አንድ አምላክ ካላቸው መጽሐፍ ቅዱስ በ2ኛ ጴጥሮስ 1:2 ላይ ለምን እግዚአብሔርንና ኢየሱስን ሁለት የተለያዩ አድርጎ አቀረበ?

 


55. መጽሐፍ ቅዱስ በ2ኛ ጴጥሮስ 1:2 ላይ «እግዚአብሔርና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ» ይላል፡፡ ክርስቲያኖች “በአንዱ በእግዚአብሔር እናምናለን” ሲሉ ይህ አባባል ኢየሱስን ይጨምራልን? ታዲያ ለምን በዚህኛው ጥቅስ እግዚአብሔርንና ኢየሱስን ሁለት የተለያዩ አድርጎ አቀረበ?

አዲስ ኪዳን “እግዚአብሔር” ሲል አውዱ ካላመለከተ በስተቀር በመደበኛነት አብን እንደሚያመለክት በተደጋጋሚ ገልፀናል፡፡ ሌሎች የሥላሴ አካላትን ወይም አንዱን ግፃዌ መለኮት ለማመልከት ከተፈለገ አውዱ ያንን ግልፅ ያደርጋል (ዮሐንስ 1፡1፣ የሐዋርያት ሥራ 5፡3-4)፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥፍራ የተጠቀሱት አብ እና ወልድ ናቸው፡፡ አሕመዲን ከጠቀሱት ጥቅስ በላይ የሚገኘው ቁጥር ሐሰተኛነታቸውን ስለሚያጋልጥ እንደልማዳቸው ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡ እኚህ ሰው ምን ያህል ለቃለ እግዚአብሔር ክብር የጎደላቸውና ሕሊናቸውን የጨቆኑ እንደሆኑ ሁሉም ሰው ማየት ይችል ዘንድ እንጠቅሰዋለን፡- የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ” (2ጴጥሮስ 1፡1)፡፡