ኢየሱስ አጠገቡ የነበሩትን 12ቱን ሐዋሪያት “እናንተ ትፈርዳላችሁ” ሲል ይሁዳን ጨምሮ ነው የገለፀው፡፡ ታዲያ ይሁዳም ይፈርዳልን?

 


57. በማቴዎስ 19:28 ላይ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው «በእውነት እላችኃለሁ የሰው ልጅ በክብር ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት በአዲሱ ዘመን የእኔ ተከታዮች የሆናችሁ እናንተም በአስራ ሁለት ዙፋን ላይ ትቀመጣላችሁ በአስራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ተሾማችሁ ትፈርዳላችሁ፡፡» ይላል፡፡ ከነዚህ አስራ ሁለት ሐዋሪያቶች መካከል አንዱ ይሁዳ ኢየሱስን ክዶታል ፡፡ ነገርግን ኢየሱስ አጠገቡ የነበሩትን 12ቱን ሐዋሪያት “እናንተ ትፈርዳላችሁ” ሲል ይሁዳን ጨምሮ ነው የገለፀው፡፡ ታዲያ ይሁዳም ይፈርዳልን? ሌላ ሰው በካህዲው ምትክ ይተካል እንዳንል “እናንተም” ”ትፈርዳላችሁ” ”የሆናችሁ“ ”አላቸው” እና ”ትቀመጣላችሁ” የሚሉት ቃላት በወቅቱ እዚያ ለነበሩት ለ12ቱ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ታድያ ኢየሱስ ይህን አያውቅምን? ደግሞ ኢየሱስ ስለሚፈርድ ”አምላክ” ከተባለ አስራ ሁለቱም ሐዋርያትም አምላክ ሆኑ ማለት አይደለምን? አያውቅምን? ደግሞ ኢየሱስ ስለሚፈርድ “አምላክ” ከተባለ አስረሰ ሁለቱም ሀዋርያትም አምላክ ሆኑ ማለት አይደለምን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ ላይ ሁሉን ትተው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ የተስፋን ቃል እየሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን ይሁዳ ይህንን ዕድል በመተው ለሌላ ሰው ታልፎ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ አስቀድሞ የተተነበየ ነው (የሐዋርያት ሥራ 1፡15-26)፡፡ ኢየሱስም ይህንን እንደሚያውቅ በተደጋጋሚ ተገልጿል (ማቴዎስ 26፡21፣ ማርቆስ 14፡18፣ ሉቃስ 22፡21፣ ዮሐንስ 6፡64፣ 6፡70-71፣ 13፡11፣ 13፡21)፡፡ ስለዚህ ይሁዳ ጌታችን ይህንን ተስፋ ሲሰጥ ቢሰማም ስላልፀና ዕድሉ ለሌላ ሰው ተላልፏል፡፡ ጌታችን የመፍረድን ሥልጣን ከአብ የተቀበለው በሥጋ የተገለጠ መለኮት ስለሆነ ነው (ዮሐንስ 5፡27)፡፡ አብ የፍርዱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ አሳልፎ የሰጠው ሰዎች እርሱን በሚያከብሩበት በዚያው ሁኔታ ልጁንም ያከብሩ ዘንድ ነው (ዮሐንስ 5፡22-23)፡፡ አምላክ ሊከበር በሚገባው በዚያው ሁኔታ ሊከበር የሚገባው አምላክ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ መፍረድ መለኮታዊ መብቱ ነው፡፡ ለዚህ ነው ለሌሎች የመፍረድን ሥልጣን ለመስጠት የቻለው፡፡ ለሐዋርያት የተሰጠው ሥልጣን ውሱን በመሆኑ ምክንያት አምላካዊ መብት እንዳላቸው ሊቆጠር አይችልም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት የሚቆሙ ሰብዓውያን ናቸው (ሮሜ 14፡10)፡፡ ክርስቶስ ከአብ የተቀበለው የመፍረድ ሥልጣን ግን ያልተገደበና ፍፁም ነው (ዮሐንስ 5፡27)፡፡ እንዲህ ያለ ሥልጣን ለፍጡር ሊሰጥ አይችልም፡፡