ኢየሱስ የአምላክ ባሪያና አገልጋይ ከሆነ እንዴት አምላክ ሊሆን ይችላል? የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎቹስ ምነው “የአምላክ አገልጋይ” የሚለውን፣ በ“ብላቴና” ለምን ለወጡት?

 


64. በሐዋርያት ሥራ 3:26፣ 4:27 እና 4:30 ላይ የእንግሊዝኛዎቹን መጽሐፍ ቅዱሳት ብንመለከት ኢየሱስን “የአምላክ ባሪያ” በማለት ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን የአማርኛዎቹ ይህን ትርጉም እንዳይዙ ሆነው “ባሪያ፣ አገልጋይ” በሚለው ምትክ “ብላቴና፣ ልጅ” በሚለው ተተክቷል፡፡ በማስከተል ከእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉት ሰባቱ ኢየሱስን “የአምላክ ባሪያ “ብለው መግለፃቸውንና “ባሪያ” በሚለው ቃል ላይ በማስመር እንመለከታለን፡- (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ሀ) “ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው” (የሐዋርያት ሥራ 3፡26)፡፡

ለ) “ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ” (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ሐ) “በእርግጥም ሄሮዶስና ጳንጥንዮስ ጲላጦስ ከአህዛብና ከእስራኤል ህዝብ ጋር በዚች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱስ ብላቴናህ ላይ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈፅም ነው፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 4:27) (ጠያቂው ‘Servant’ የሚለው ቃል የተጠቀሰባቸውን 7 የሚሆኑ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ጠቅሰዋል፡፡)

ከላይ የጠቀስናቸው የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጥቅሶች በሙሉ ስለ ኢየሱስ የአምላክ አገልጋይ እንጂ ስለ አምላክነቱ፣ አይደለም የሚገልፁት!!! ይህ እንግሊዝኛው ሲሆን የ 1980 ቀላል ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከበፊቱ በተለየ መልኩ ልክ እንደ እንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አገልጋይ ይለዋል፡፡ “በእርግጥም ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአረማውያንና ከእስራኤል ህዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው መሲህ ባደረግኸው በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 4፡27) እንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ “Your servant Jesus” “አገልጋይህ ኢየሱስ” ይላል፡፡ ለምን በአማርኛው ይህን አገልጋይህ የሚለውን በ“ብላቴናህ” ቀየረው??? ኢየሱስ የአምላክ ባሪያና አገልጋይ ከሆነ እንዴት አምላክ ሊሆን ይችላል?? የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎቹስ ምነው “የአምላክ አገልጋይ” የሚለውን፣ በ“ብላቴና” መለወጣቸው? ኢየሱስ አምላክ እንዲሆን ፈልገው ይሆን?

የአማርኛ ተርጓሚዎች “ብላቴና” በማለት መተርጎማቸው ስህተት አይደለም፡፡ “ፓሂስ”[5] የሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም “ብላቴና” ማለት ሲሆን በአማራጭነት “ልጅ (Child)” ወይም “አገልጋይ (Servant)” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ነገር ግን መብት አልባ ባርነትን በሚገልፅ መልኩ ሊተረጎም አይችልም፡፡[6] የተወሰኑ የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቃሉን “ልጅ (Child)” በማለት የተረጎሙ ሲሆን አሕመዲን ጀበል ግን ከዓላማቸው ጋር ስለማይሄዱ እነዚህን የእንግሊዘኛ ትርጉሞች በመተው ሌሎቹን ብቻ በመጥቀስ ከእነርሱ ውጪ ሌላ ትርጉም የሌለ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡[7] በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጌታችንን የእግዚአብሔር ልጅነት ለመግለፅ “ሁዮስ”[8] የሚል የተለየ የግሪክ ቃል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡[9] ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የባርያን መልክ ይዞ መለኮታዊ ክብሩን በመተው እንደ መመላለሱ አገልጋይ ተብሎ ቢጠራ ሰብዓዊ ባሕርዩን እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን ስለማይነካ አምላክነቱን ለማስተባበል የሚውል ሙግት ሊሆን አይችልም (ፊልጵስዩስ 2፡4-12)፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ቃሉን የሚለውጡበት ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ኡስታዙ በቁንፅል ዕውቀት ተነስተው ቃለ እግዚአብሔርን በጥንቃቄ እና በታማኝነት በተረጎሙልን አባቶች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ አልባ ውንጀላ መሰንዘራቸው ትልቅ ድፍረት ነው፡፡