ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እና አምላክ ሥላሴ (ሦስትም አንድም) ከሆነ እንዴት አንዱ አምላክ “ከኔ በቀር ሌለ አምላክ የለም” ይላል?

 


68. በኢሳይያስ 44:7 ላይ አምላክ እንዲህ ማለቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፦ “የእስራኤል ንጉሥ ቤዛ እግዚአብሔር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛው እኔ ነኝ፣ የኋላኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እስቲ እንደኔ ማን አለ? ይናገር፡፡” ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እና አምላከ ሥላሴ (ሦስትም አንድም) ከሆነ እንዴት አንዱ አምላክ “ከኔ በቀር ሌለ አምላክ የለም” ይላል? እንዲሁም እንዴት “እስቲ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር” ይላል? ምናልባት ያኔ አየሱስ ገና ስላልተወለደ ይሆንን? በፍጹም! እንዲህማ ቢሆን ኖሮ “የፊተኛው እኔ ነኝ፤ የኋላኛውም እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም” ሲል ይናገራልን??

ጠያቂው አምላክ በአካልም በመለኮትም ነጠላ ነው የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ስለያዙ “ከእኔ በቀር አምላክ የለም” የሚለውን አባባል “አምላክ አንድ አካል ብቻ አለው” ለሚለው ማስረጃ አልባ አመለካከታቸው እንደ ማስረጃ ቆጥረዋል፡፡ በክርስቲያኖች ግንዛቤ መሠረት ግን ይህንን እየተናገረ ያለው አሐዱ ሥሉስ የሆነው አንድ አምላክ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንኑ አባባል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በመድገም የራሱ አድርጎ የተናገረው (ዮሐንስ 8፡56-58፣ ራዕይ 1፡8፣ 17 አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥”)፡፡

እስልምና አጥብቆ እንደሚያስተምረው ፈጠሪን የሚመስል ምንም ነገር የለም ከተባለ በአንድነቱም የሚመስለው ምንም ነገር መኖር የለበትም፡፡ ነገር ግን የአሕመዲን አምላክ አንድነት በብዙ ምሳሌዎች ሊገለፅ የሚችል ተራ አንድነት ነው፡፡ የአምላካቸው አንድነት ከበሀኢዎች፣ ከሰይጣን አምላኪዎች ከዞራስትራውያን፣ ከአርዮሳውያን፣ ወዘተ. አማልክት አንድነት ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአምላካቸው አንድነት እንደ ሰው፣ እንደ መላእክት፣ እንደ ሰይጣን፣ እንደ እንስሳት፣ ወዘተ. አንድነት ነው፡፡ ስለዚህ በራሳቸው እምነት መስፈርት እንኳን አምላካቸው እውነተኛ አምላክ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ የክርስትናን አምላክ አንድነት በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ የሚመስል ምንም ነገር የለም፡፡ በአፅናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ፍጥረት ምሳሌ ሆኖ ሊገልፀው አይችልም፡፡