ኢየሱስ ”አምላክ” ነው ወይንስ ይህ ጥቅስ (ማቴዎስ ወንጌል 12:18) እንደሚለው የአምላክ አገልጋይ?

 


69. የማቴዎስ ወንጌል 12:18 ስለ አየሱስ ፦ “እነሆ የመረጥሁት የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ እርሱ ለአሕዛብ ፍትህን ያውጃል፤” ሲል ይገልጻል፡፡ በዚህ ጥቅስ ኢየሱስ የአምላክ አገልገይ መሆኑ ተጠቅሶዋል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ ”አምላክ” ነው ወይንስ ይህ ጥቅስ እንደሚለው የአምላክ አገልጋይ? አምላክ ”አገልጋዬ” አያለው ክርስቲያኖች እንዴት አምላክ ነው ይሉታል?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ በባሕርዩ አምላክ ቢሆንም ነገር ግን ሥጋን በመልበስ እንደ አገልጋይ ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ማቴዎስ መሲሁ አገልጋይ ሆኖ ስለመምጣቱ በነቢዩ ኢሳይያስ የተተነበየውን ትንቢት በጠቀሰበት በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ኢየሱስ የሰንበት ጌታ መሆኑን የተናገረውን ቃል አስፍሯል (ቁ. 8)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ ክብርና አምልኮ በፈጠረው ቀን ላይ ጌታ መሆን የሚችለው እርሱ ብቻ በመሆኑ ይህ ንግግር ኢየሱስ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ማቴዎስ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ስለ ኢየሱስ ጌትነትና አገልጋይነት ተናግሯል፡፡ ጌትነቱ መለኮት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን አገልጋይነቱ ደግሞ እንደ መሲህ የነበረውን ግብር ያመለክታል፡፡