ኢየሱስ ከኃጢአት በቀር በሁሉም ነገር እንደኛ ከሆነ፣ እንዴት አምላክ ይሆናል?

 


92. ዕብራውያን2:17 ላይ “ስለዚህ በሁሉም ነገር ወድሞቹን መምሰል ተገባው” ይላል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች እንደ ሚሉት ኢየሱስ በሁሉም ነገር እንደኛ ከሆነ፣ እንዴት ፍፁም (100°/°) ሰው እንደዚሁም ፍፁም (100°/°) አምላክ ይሆናል? እንደኛ ሲሆን እኛስ ፍፁም አምላክ ልንሆን ነው ማለት ነውን?

ይህ ቃል የተነገረው በእርሱ በማመን የልጅነትን ሥልጣን አግኝተው አብረው ወራሾች ለሆኑት ለክርስቲያኖች እንጂ የእግዚአብሔር ልጆች ተብሎ መጠራትን እንደ ክህደት ለሚቆጥሩት “የአላህ ባርያዎች” ባለመሆኑ አሕመዲን በዚህ መደብ ውስጥ ራሳቸውን መቁጠራቸው ስህተት ነው፡፡ ይህንን በማድረግ አላህ ልጅ እንደሌለው የተነገረውን የቁርኣን ቃል ስለተጣረሱ በሃይማኖታቸው ላይ ክህደትን ፈፅመዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሙስሊም ሰባኪያን የሚያቀርቡት ሙግት ክርስትናን የሚገዳደር መስሎ እስከታያቸው ድረስ በገዛ ሃይማኖታቸው ላይ እንኳ ክህደትን ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው፡፡

ኢየሱስ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን የመሰለው በሰብዓዊ ባሕርዩ እንጂ በመለኮቱ አይደለም፡፡ ይህንን የጥቅሱ አውድ ራሱ ግልፅ ያደርጋለ፡- “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው፡፡ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና፡፡” (ዕብራውያን 2፡14-18)፡፡