ኢየሱስ “ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ” ከሆነ ሁለት ተቃራኒ ነገር ሊሆን ይችላል?

 


94. አንድ የክርስትና እምነትጸሐፊ እዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ምንም እንኳ የእስልምና ሃይማኖት ባይቀበልም፣ ለክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆንና ፍጹም ሰው መሆን ከተልዕኮው አኳያ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ የክርስቶስ ዋና ተልዕኮ ደግሞ የሰው ልጅን ከኃጢያታቸው ማዳን በመሆኑ ምንም እንኳን ክርስቶስ ሁለት ባህሪያት አሉት ማለት ለሰው አዕምሮ ከበድ ያለ ነገር መስሎ ቢታይም እግዚአብሔር በሁሉን ቻይነቱ ያደረገው የክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆን እውነት ነው ፡፡” (ምህረቱ ጴ. ጉታ፣ መልስ ይኖረው ይሆን? ኤስ አይ ኤም ማተምያ ቤት ታትሞ፣ 4ኛ ዕትም፣ 1998፣ ገፅ 63)

ሀ) እዴት ኢየሱስ “ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ” ይሆናል? እንዴት ሁለት ነገር ፍፁም ይሆናል? አንድን ሰው “ከሰዎች ሁሉ ረጅሙ እርሱ ነው፡፡ አጭሩም እርሱ ነው፡፡” ማለት ይቻላል?

አሕመዲን ለመፈላሰፍ ቢሞክሩም ነገር ግን እሳቸው የሰጡት ምሳሌና ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ የሚያምኑት አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከሰው ሁሉ ረጅም እና ከሰው ሁሉ አጭር የማይባልበት ምክንያት ርዝመት እና እጥረት ከአንድ መደብ፣ ማለትም የወርድ ርዝመት ስለሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ውፍረት እና ርዝመት ሁለት የተለያዩ ፅንፎች በመሆናቸው አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሰዎች ሁሉ አጭር እና ከሰዎች ሁሉ ወፍራም ወይም ከሰዎች ሁሉ ረጅም እና ከሰዎች ሁሉ ቀጭን ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውና አምላክ እንደ ርዝመት እና እንደ እጥረት ከአንድ መደብ ስላልሆኑ ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ሰውም አምላክም መሆን የማይችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡

ለ) “ኢየሱስ ፍፁም ሰውም ፍፁም አምላክም ነው” ከተባለ ይህ አስተሳሰብ ከሎጂክ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስም ጭምር የሚጋጭና የማያስኬድ ነው፡፡ አምላክ ፍፁም ኃያል፣ ሁሉን አዋቂ፣ ፍፁም ጥበበኛ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በተቃራኒው ኃያል ያልሆነ፣ ሁሉን የማያውቅ፣ ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው፡፡ “አምላክ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው” ማለት፦ “አምላክ (ኢየሱስ) ሁሉን አዋቂ የሆነና ሁሉን አዋቂ ያልሆነ ነው፡፡ አምላክ ኃያል የሆነና ኃያል ያልሆነ ነው፡፡ አምላክ ፍፁም ጥበበኛ የሆነና ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው” ማለት ነው፡፡ ይህ ትርጉም የሚሰጥ ነውን?

ክርስትና ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን እንጂ ጠያቂው ባስቀመጡት መንገድ “አምላክ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው፤ አምላክ ሁሉን አዋቂ የሆነና ሁሉን አዋቂ ያልሆነ ነው፤ አምላክ ኃያል የሆነና ኃያል ያልሆነ ነው፤ አምላክ ፍፁም ጥበበኛ የሆነና ፍፁም ጥበበኛ ያልሆነ ነው” በማለት አያስተምርም፡፡ ውሱንነት የሚታይበት ባሕርዩ ስለ እኛ ሲል የለበሰው ሥጋው እንጂ መለኮቱ አይደለም፡፡

ሐ) የሆነ ነገርን “ፍጹምም ነው፤ ፍጹምም አይደለም” ማለት ልክ የሆነን ነገር “ይህ ነገር ክብም፣ አራት ማአዘንም ነው፤” እንደ ማለት ነው፡፡ “አራት ማዕዘን ነውም” ስንል “ክብ አይደለም” ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ሁለት የማይገናኙትን ባህሪያት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ፍፁም መሆን ይችላልን?

አሁንም አሕመዲን ለመፈላሰፍ ይሞክራሉ ነገር ግን ፍልስፍናውን አላወቁበትም፡፡ ክብ እና አራት ማዕዘን ከአንድ መደብ፣ ማለትም ከቅርፅ መደብ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ክብ እና አራት ማዕዘን ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ክብ እና አረንጓዴ ወይም አራት ማዕዘን እና ቀይ ሊሆን ይችላል፡፡ ቅርፅ እና ቀለም ሁለት የተለያዩ መደባት እንደሆኑት ሁሉ ሰውና አምላክም ሁለት የተለያዩ መደባት በመሆናቸው ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑ ምንም የሚያስከትለው የሥነ አመክንዮ ችግር የለም፡፡ የአሕመዲን ምሳሌ የተሳሳተና ስለ ኢየሱስ ከተነገረው ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፡፡

መ) ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች በአንድነት ነው ማለት በፍፁም የማይሆን ነው፡፡ ለምሳሌ “አምላክ አለ” ብንል አንድ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ “አምላክ የለም” ብንል ደግሞ ሌላ ተቃራኒ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ ሁለቱም ትክክል ሊሆኑ በፍፁም አይችሉም፡፡ ክርስቲያኖች እንደ ሚሉት “ሁለት ተቃራኒ ነገሮች በአንድነት ሊኖሩ ይችላሉ” ብንልና “አምላክ አለ፤ እንደዚሁ አምላክ የለም፡፡” ብንል፤ ሁለት ተቃራኒ ዐረፍተ ነገሮች ናቸው፡፡” አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ምን አለበት፣ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ምን ይሳነዋል?” ማለት ይቻለናልን?

ጠያቂው ሰውና አምላክ ፍፁም ተቃራኒ ባሕርያት እንዳላቸው ማሰባቸው ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ አምሳል ስለፈጠረ የተወሰነ ዕውቀት፣ የተወሰነ ኃይል እና የተወሰነ ጥበብ ሰጥቶታል፡፡ ፍቅርን፣ ዕውቀትን፣ ነፃ ፈቃድን እና ምጋቤን ጨምሮ ውሱን በሆነ መጠን በሰዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ የእግዚአብሔር ባሕርያት አሉ፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ባሕርያት በሰው ውስጥ ከመኖራቸው የተነሳ ሰውና አምላክ ተቃራኒ እንደሆኑ እንድንናገር የሚያስችለን የሎጂክ ሕግ የለም፡፡ ኢየሱስ ሰውም አምላክም ነው የሚለው አባባል አምላክ አለ እንደዚሁም አምላክ የለም ከሚለው እርስ በርሱ የተፋለሰ አባባል ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡ ኢየሱስ ሰው በመሆኑ ሰብዓዊ ባሕርይን አከለ እንጂ እንደ አምላክ የነበረው ሕልውና አልጠፋም፡፡