የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ የኢየሱስ እህትና ወንድም ከሆነ አምላክ እህትና ወንድሞች አሉት?


  1. በማቴዎስ 12፡49-50 ላይ “በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፡፡ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፤ ወንድሜ፤ እህቴና እናቴም ነው፡፡” ይላል፡፡ ታድያ የአምላክን እህትና ወንድም ሊሆኑ ነዋ? ወይስ የእምነት ወንድምና እህት ለማለት ነው? እንዲያማ ከሆነ የኢየሱስ እምነት የሐዋርያት እምነት ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ክርስቲያኖች “ኢየሱስ አምላክ ነው” ስለሚሉ አምላክ ሃይማኖትን ይከተላል፤ አማኝ ነው ማለት ነውን? ገነት የሚገባው የራሱን ፊቃድ የሚደርገው ሳይሆን “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ” ነው በማለት የአባቱን ፍቃድ የፈጸሙት መሆኑን ሲገልጽ ሐዋርያቶች እርሱ ማን መሆኑን ያውቁ ዘንድ ፈልጎ ይሆን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፤ ወንድሜ፤ እህቴና እናቴም ነው” ሲል ሁለት ነገሮችን ለማመልከት ነው፡፡ የመጀመርያው በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንደ ማንኛውም ሰው ቤተሰብ ስለነበረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈፅሙትን ሰዎች እንደ ቤተሰብ እንደሚቆጥርና ከሥጋ ቤተሰቡ ለይቶ እደማያይ ለመናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አማኞች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል የመሆናቸውን የላቀ ክብር ለማሳየት ነው፡፡ በሰማያት ያለው የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ስለነገረን መገመት አያስፈልገንም፡- ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡” (ዮሐንስ 6፡39)፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል መሆን የሚቻለው በልጁ በማመን በመሆኑ ከእርሱ ጋር የሚኖረንን ቤተሰባዊ ቅርበት የገለጠበትን ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ቃል በቃል በመውሰድ ልጁን በአማኞች መደብ ውስጥ መደመር መሠረታዊ የግንዛቤ ችሎታን ከማጣት ይቆጠራል፡፡