የውርስ ኃጢአት እውነት ከሆነ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግስት  እንደነዚህ ላሉት ናትና” ለምን አለ?

 


  1. ማርቆስ 10፡13-14 ላይ “ኢየሱስም እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕጸናትን ወደርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው፤ ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግስት  እንደነዚህ ላሉት ናትና” ይላል፡፡ የውርስ ኃጢአት እሳቤ እንደሚለው ደግም ሰው ሁሉ ሲወለድ ከኃጢአት ጋር ነው፡፡ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ሕፃናት ከነውርስ ኃጢአታቸው ለምን  “የእግዚአብሔር መንግስት እንደነዚህ ላሉት ናት” አለ? ሕፃናቱ ራሳቸውን አውቀው ገና “በማመን” የውርስ ኃጢአታቸውን አላስተሰረዩ? በዚህም ላይ ደግም ኢየሱስ ይህን የተናገረው ገና ተሰቀለ ከመባሉ በፊት ስለሆነ እንዴት  የህፃናቱ ንፁህነት ገለፀ? ለመሆኑስ የውርስ ኃጢአት  የሚባል ነገር ለአእምሮ አይጎረብጥምን?

ጌታችን በዚህ ቦታ እየተናገረ ያለው እንደ ህፃናት በቅንነትና በየዋህነት እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል እንደሚገባን ነው፡፡ የጌታችን መልእክት አንኳር ነጥብ ይህ ሲሆን እግረ መንገዱን ህፃናት እንደሚድኑ ያመላከተ ይመስላል፡፡ የውርስ ኃጢአት እና የህፃናት ደህንነት ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ በመሆኑና በክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት ወቅት ተደጋግሞ ከመነሳቱ አንፃር በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ የምናምነውን ሐሳብ ማስቀመጥ አስፈላጊ መስሎ ይታየናል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ህፃናት ሲወለዱ ከኃጢአት ነፃ አይደሉም (መዝሙር 51፡5)፡፡ እያንዳንዱ ሰው የአዳምን የኃጢአት ውጤት ይወርሳል (ሮሜ 5፡12-21)፡፡ ሰው ሁሉ በፍጥረቱ የቁጣ ልጅ ነው (ኤፌሶን 2፡3)፡፡ ጌታችን ህፃንና አዋቂ በማለት ሳይለይ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ይችሉ ዘንድ ዳግመኛ መወለድ እንደሚያስፈልጋቸው አስተምሯል (ዮሐንስ 3፡1-12)፡፡  ይህ አቋም ህፃናት በክርስቶስ አምነው ዳግመኛ የመወለድን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችላቸው የአዕምሮ አቅም ስለሌላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገቡም ወደሚል ድምዳሜ የሚያመራ ይመስላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍርድ ደግሞ ፍትሃዊ ከሆነው አምላክ የሚጠበቅ ባለመሆኑ ጥያቄን ያስነሳል፡፡

ለዚህ ጥያቄ ሁለት መልሶች አሉ፡፡ የመጀመርያው እግዚአብሔር ለህፃናት ለደህንነታቸው የሚሆነውን እምነት የመስጠት ስልጣንና ችሎታ አለው የሚል ነው፡፡ ለዚህ ድጋፍ የሚሰጥ አንድ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል (መዝሙር 22፡9-10)፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ባይገባንም እግዚአብሔር ይህንን ማድረግ እንደሚችል በመጠራጠር ሁሉን ቻይነቱን መዘንጋት የለብንም፡፡

ሁለተኛው መልስ ክፉና ደጉን መርጦ የመሥራት አዕምሯዊ ብቃት የሌላቸውን ሰዎች እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ያስተሰርይላቸዋል የሚል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን ጥያቄ መልስ በሰጠ ጊዜ ይህንን ጉዳይ ግልፅ አድርጓል፡- “ኢየሱስም አላቸው፡- ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን፦ እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል፡፡” (ዮሐንስ 9፡41)፡፡ በሌላ አባባል ሰው ክፉውንና ደጉን የመለየት አዕምሯዊ ብቃት ከሌለው ኃጢአቱ አይኖርም (ይስተሰረይለታል) ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ያልሰሙ ሰዎች ለምን እንደሚፈረድባቸው በተናገረበት ክፍል ላይ ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ የሚመራ ነጥብ አስቀምጧል፡- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ፡፡” (ሮሜ 1፡21)፡፡ እነዚህ ሰዎች በተፈጥሮ ከሚገኘው መገለጥ የእግዚአብሔርን መኖር እና ታላቅነቱን ቢገነዘቡም ነገር ግን ተገቢውን ክብር ሊሰጡት ስላልወደዱ ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ ምንም የሚያመካኙት ነገር አይኖራቸውም፡፡ በሌላ አባባል የእግዚአብሔርን መኖር እና ታላቅነቱን ማወቅ የሚችሉበት ምንም መንገድ ባይኖርና ያንን የመገንዘብ ተፈጥሯዊ ችሎታ ቢጎድላቸው ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ የሚያመካኙት ነገር (Excuse) ይኖር ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ህፃናትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ቢሆኑም እግዚአብሔር የሚፈርደው ክፉና ደጉን የመምረጥ የግንዛቤ ደረጃ ባላቸው ሰዎች ላይ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን የመሥራት ዝንባሌ በተግባር የሚሠራበት ዕድሜ ላይ ያልደረሱትን ህፃናት እግዚአብሔር ወደ ገሃነም አይልክም፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህፃናት ወደ መንግሥቱ እንደሚገቡ ማመላከቻ የሰጠው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የውርስ ኃጢአት ስለሌለባቸው ሳይሆን የውርስ ኃጢአታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ስለሚነፃ ነው፡፡ ይህንን የምንልበት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለ ስለሚናገር ነው (የሐዋርያት ሥራ 4፡12፣ ዕብራውያን 9፡22-26)፡፡ መንገድም እውነትም ሕይወትም እርሱ ነው፡፡ በእርሱ በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ወደ አብ መምጣት አይችልም (ዮሐንስ 14፡6)፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ከእርሱ በፊት ለነበሩት ሰዎችም ሆነ ከእርሱ በኋላ ለመጡት ሰዎች ሁሉ የመዳን መንገድ ነው (ዕብራውያን 9፡26)፡፡ የኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት የተከናወነ ቢሆንም ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅድ ውስጥ የነበረ ነው (ራዕይ 13፡8፣ የሐዋርያት ሥራ 4፡27-28)፡፡

አንድ ነገር ልክ ወይም ስህተት መሆኑ የሚወሰነው በሰው ስሜት እና ምርጫ ላይ ተመስርቶ ባለመሆኑ የውርስ ኃጢአት እሳቤ ለአንዳንዶች አዕምሮ “መጎርበጡ” ትክክል እንዳይሆን አያደርገውም፡፡ በእስልምና የውርስ ኃጢአት እሳቤ እንደሌለ ቢነገርም ነገር ግን የእስልምና መጻሕፍት ይህንን አያመለክቱም፡፡ ሙስሊሞች የውርስ ኃጢአትን መካዳቸው በተፈጥሮ ከሚታያው እውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው ጋርም ጭምር እንዲጣሉ ያደርጋቸዋል፡፡

“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡ አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡ «ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱራ 2፡36-38)፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው “ሁላችሁም” የሚለው በአረብኛ ከሁለት በላይ ቁጥርን የሚያመለክት ሲሆን ፍርዱ በአዳም እና በሔዋን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያሳያል፡፡[1] አላህ የአዳምን ንስሐ እንደተቀበለ ተነግሯል ነገር ግን ከገነት መባረሩ አላህ ኃጢአቱን ይቅር እንዳላለ ያሳያል፡፡ ኃጢአቱን ይቅር ቢለው ኖሮ ለምን ወደ ገነት አልመለሰውም ነበር? ፀፀቱን ተቀብሎ ኃጢአቱን ይቅር ከማለት ይልቅ ፀፀቱን ተቀብሎ ወደ ፊት ለዘሮቹ የሚሆን መመርያ ለመስጠት እና ይህንን መመርያ የተከተለውን ሰው ብቻ ለመማር እንደወሰነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡

ቲርሚዚ ሐዲስ አዳም የሰራው ኃጢአት ወደ ዘሮቹ ሁሉ መተላለፉን እንዲህ በማለት ይገልፃል፡- “አደም ስለ ካደ ዘሮቹ ሁሉ ካዱ፡፡ አደም ዝንጉ በመሆን የተለከለከለውን ዛፍ ስለበላ ዘሮቹም ዝንጉዎች ሆኑ፡፡ አዳም ስለተሳሳተ ዘሮቹ ሁሉ ስህተት ፈፀሙ፡፡”[2]

አልቡኻሪ ደግሞ ሙሴ አዳምን “ከገነት እንድንባረር ያደረከን አንተ አባታችን ነህ” በማለት በወቀሰው ጊዜ አዳም መልሶ “አላህ ከመፈጠሬ ከአርባ ዓመታት በፊት ወስኖልኝ ለጻፈብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን?” በማለት እንደመለሰለት ዘግቧል፡፡[3]

ሳሂህ ሙስሊም “ከገነት ያስባረራችሁ የአባታችሁ የአደም ኃጢአት ነው” ይላል፡፡[4]

እስላማዊ ምንጮች ከዚህም አልፈው ሴቶች “እስከዛሬ ድረስ ለሚያሳዩት ጸባይ” ሔዋንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- በእስራኤል ልጆች ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሥጋ ባልበሰበሰ ነበር፡፡ በሐዋ ምክንያት ባይሆን ኖሮ የትኛዋም ሴት ባሏን ባልከዳች ነበር፡፡”[5]

በተጨማሪም አል-ጦበረኒ የተሰኘ ጥንታዊ ሙስሊም ጸሐፊ ሴቶች የወር አበባ የሚፈስሳቸውና “በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑት” በሔዋን ምክንያት እንደሆነ ጽፏል፡፡[6]

በቁርኣን መሠረት ሰው “ቅጠ ቢስ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 70፡19-24)፡፡ “ደካማ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 4፡28)፡፡ “በልፋት ውስጥ ሆኖ ተፈጠረ” (ሱራ 90፡4)፡፡ በነዚህ ጥቅሶች መሠረት አላህ ሰውን ከፍጥረቱ ጀምሮ አበላሽቶታል ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ እንደፈጠረ እንጂ ከነዚህ ጉድለቶች ጋር እንደፈጠረ አይናገርም (ዘፍጥረት 1፡26)፡፡ ሰው ለነዚህ ጉድለቶች የተጋለጠው ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ነው (ዘፍጥረት 3፡1-19)፡፡ ጠያቂያችን ክርስትናን ለመተቸት ከመነሳታቸው በፊት የገዛ ሃይማኖታቸውን መመርመር ነበረባቸው፡፡