አብ የወልድ ሕይወት ምንጭ አይደለምን? “ወልድ የሰው ልጅ ስለሆነ” ይላላ እንጂ አምላክ ስለሆነ ይላል?

 


  1. ዮሐንስ 5፡26-27 “አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡” ይላል፡፡ ወልድ ሕይወት እንዴት ሊኖረው ቻለ? ጥቅሱ “ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና” ይላል!
    አብ የወልድ ሕይወት ምንጭ አይደለምን? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ወልድ (ኢየሱስ) የመፍረድ ሥልጣን ያገኘው አምላክ ስለሆነ ነውን? ጥቅሱ ወልድ “አምላክ” ስለ ሆነ ነው ይላልን? በፍፁም! “ወልድ የሰው ልጅ ስለሆነም” እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡” ነው የሚለው፡፡ ሳይሰጠው በፊትስ? ታዲያ ክርስቲያኖች ምነው ቆም ብለው ቢያስተነትኑት?

በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘው ኢየሱስ እንደ አብ ሁሉ እርሱም በራሱ ሕይወት አለው፡፡ ይህ ማለት ለመኖር በማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነው የአብ ሕይወት የወልድም ሕይወት ነው ማለት ነው፡- “እግዚአብሔርም የዘለዓለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፡፡ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡” (1ዮሐንስ 5፡11-12)፡፡

“የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው” (ቁ. 27)፡፡ ጌታችን በዚህ ቦታ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚገዛው በዳንኤል 7፡13-14 ላይ የተጠቀሰው የሰው ልጅ ተብሎ የተጠራው መለኮታዊ አካል መሆኑን መናገሩ አምላክነቱን ያሳያል፡፡