ስለ ኢየሱስ ጭራሽ ያልሰሙት ከርሱ መወለድ በፊት የነበሩ ህዝቦች በምን ሊድኑ ነው?

 


  1. ኢየሱስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ ሰውን ነፃ ለማውጣት ከመጣ ስለ ኢየሱስ ጭራሽ ያልሰሙት ከርሱ መወለድ በፊት የነበሩ ህዝቦች በምን ሊድኑ ነው?

እግዚአብሔር በሰዎች ላይ የሚፈርደው በተገለጠላቸው መጠን ነው፡፡ ሕግ የተሰጣቸው ለሕጉ ታማኝ በሆኑት መጠን ሕግ ያልተሰጣቸው ደግሞ ለተሰጣቸው የኅሊና ሕግ ባሳዩት ታማኝነት መጠን የእግዚአብሔርም ፍርድ እንደዚያው ይሆናል (ሮሜ 1፡18-32፣ 2፡14-16)፡፡ እነዚህ ሰዎች በእምነት ፋንታ እንደ ሞግዚት በሚያገለግለው በሕግ ስር ሲኖሩ ሳሉ ለሕጉ የሚያሳዩት ታማኝነት ወደ ክርስቶስ ያደርሳቸዋል (በክርስቶስ ሥራ ውስጥ እንዲጠቀለሉ ያደርጋቸዋል) እንጂ በራሱ አያድናቸውም (ገላቲያ 3፡22-25)፡፡ ለኅሊና ሕግና ለተጻፈው ሕግ ታማኞች የሆኑትን ሰዎች እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ሰምተው ያመኑትን ሰዎች ሁሉ ሊያድን ኢየሱስ ደሙን አፍስሷል (ዕብራውያን 9፡22-28)፡፡ ስለዚህ የሰው ልጆችን ታሪክ እንደ ረጅም መስመር ብንስል የክርስቶስ መስቀል መካከል ላይ ቆሟል፡፡ ከመስቀሉ በፊት የሚገኙት ሰዎች ስለ መስቀሉ ባያውቁም ነገር ግን ለሕገ እግዚአብሔር ታማኞች በመሆን ወደፊት በሚመጣው የመስቀሉ ሥራ ውስጥ ይጠቀለላሉ፡፡ ከመስቀሉ በኋላ ያሉት ደግሞ የምስራቹን በማመን መስቀሉን ወደ ኋላ ተመልክተው ይድናሉ፡፡ ከመስቀሉ ውጪ ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም! ለዚህ ነው እስልምናን የመሳሰሉት መለኮታዊ ምንጭ የሌላቸው ሃይማኖታት መስቀሉን የሚቃወሙት፡፡