ኢየሱስ “ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ይግዛ” ብሏል፡፡ ለምን? በሰይፍ እንዳይሰቀል እንዲከላከሉለት?

 


  1. ሉቃስ 22: 36 “እርሱም እንዲህ አላቸው: “አሁን ግን ኮሮጆም ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ “ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ይግዛ” ብሏል፡፡ ለምን? በሰይፍ እንዳይሰቀል እንዲከላከሉለት? ሊሰቀል “መጣ” የተባለው ሰው እንዴት ሃሳቡን ሊቀይር ቻለ?

ጠያቂው ከገዛ ምናባቸው ጋር ከሚነጋገሩ ክፍሉን ጨርሰው ቢያነቡ ኖሮ ከስህተት በዳኑ ነበር፡፡

“ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው፡፡ እርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ፡፡ እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ፡፡ እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቁጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው፡፡ እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት፡፡ እርሱም፦ ይበቃል አላቸው፡፡ (ሉቃስ 22፡35-38)፡፡

ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ ስለ መሲሁ መገደል የሚናገረውን የኢሳይያስ 53 ትንቢት ነው እየጠቀሰ ያለው፡- ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቁጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ” (ኢሳይያስ 53፡12)፡፡

ስለ መገደሉ የተተነበየውን ትንቢት ጠቅሶ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ “ሐሳቡን ቀይሯል” የሚለው የጠያቂው ድምዳሜ ያስኬዳልን? ለዚህ ድምዳሜያቸው ደግሞ እንደመነሻ የተጠቀሙት ምክንያት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዲያዘጋጁ ያሳሰበው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያ አስቸጋሪ ጊዜ ከፊት እየመጣ በመሆኑ ሳብያ የራሳቸውን ኃላፊነት በራሳቸው እንዲወጡ ቅኔያዊ በሆነ መንገድ ማሳሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ” የሚለው ትንቢት እንዲፈፀም ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ንግግር በመጥቀስ “እንዳይሰቀል በሰይፍ እንዲከላከሉለት ነው” የሚል ነገር ፈራ ተባ እያሉ ጽፈዋል፡፡ ኢየሱስ ግን  “በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ” ሲሉት “ይበቃል” የሚል መልስ ነበር የሰጣቸው፡፡ ሊይዙት ከሚመጡት ስልጡን ወታደሮች ጋር በሁለት ሰይፍ ተፋልመው እንደማያስጥሉት ሳያውቅ ቀርቶ ይሆን ሁለት ሰይፍ በቂ እንደሆነ የተናገረው? ጠያቂው በጠቀሱት በዚሁ ምዕራፍ ላይ ከአፍታ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ ተጠቅመው ሊያስጥሉት ሲሞክሩ ከልክሏቸዋል፡፡ በሰይፋቸው የጎዱትንም ሰው ፈውሶታል፡-

“በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት፡፡ ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቁረጠው፡፡ ኢየሱስ ግን መልሶ፦ ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው፡፡” (ሉቃስ 22፡49-51)

የዚህ ተጓዳኝ ንባብ በሆነው በማቴዎስ 26፡51-54 ላይ እንዲህ ይላል፡-

“እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቁረጠው፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፡፡ ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ፦ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?”

ኢየሱስ ለአስቸጋሪ ጊዜ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ቅኔያዊ በሆነ መንገድ መልዕክት ለማስተላለፍ እንዲሁም “ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ” የሚለው ትንቢት ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዲያዘጋጁ ቢነግራቸውም እርሱ እንዳይያዝ ለመከላከል እንዳይጠቀሙ ከመከልከልም አልፎ ያንን ለማድረግ ሲሞክሩ ገስጿቸዋል፡፡ አሕመዲን ኢየሱስን ሰይፍ የሚመዝ ጂሃዳዊ በማስመሰል ለማጠጋጋት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም፡፡