የሰው ልጅ በአደም ምክንያት ኃጢአት የመስራት ዝንባሌንና ባህሪን ከወረሰ በኢየሱስ ስቅለት በደሙ ከነፃ ለምን ያ ዝንባሌ አሁንም ቀጥሎ ሰው ወንጀል እየሰራ ሊቀጥል ቻለ?

 


  1. የሰው ልጅ አደም በፈፀመው ኃጢአት ምክንያት ኃጢአት የመስራት ዝንባሌንና ባህሪን ከወረሰ እንዲሁም ይህ ዝንባሌ በኢየሱስ ስቅለት በደሙ ከነፃ ለምን ያ ዝንባሌ አሁንም ቀጥሎ ሰው ወንጀል እየሰራ ሊቀጥል ቻለ?

ጠያቂው ቀደም ሲል ሲቃወሙት የነበሩትን የውርስ ኃጢአት ተቀብለው ሲሟገቱ መታየታቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው (ምዕራፍ 4 ጥያቄ ቁጥር 12ን ይመልከቱ)፡፡

በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው በሕይወቱ ከሚከናወኑት የጸጋ ሥራዎች መካከል ኃጢአትን እምቢ የማለት ችሎታ አንዱ ነው (ሮሜ 8 ፡ 3-4፣ ገላትያ 5፡24፣ ቲቶ 2፡11-12)፡፡ ከአሮጌው ሥጋችን ተለይተን የተለወጠውንና አዲሱን የትንሣኤ ሥጋ እስክንለብስ ድረስ ከኃጢአት ጋር የምናደርገው ትግል ቀጣይነት ያለው ቢሆንም ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ ዕለት በዕለት እንድንቀደስና እርሱን ወደ መምሰል እንድናድግ ይረዳናል፡፡

ደሙ ስለሰው ልጆች ሁሉ የፈሰሰ ቢሆንም በደሙ የመንጻት መብት ያለው የክርስቶስን መስዋዕትነት አምኖ የተቀበለ ብቻ ነው (ዮሐ 1፡12)፡፡ መድኃኒት የሚሰራው ለበሽተኛ ሁሉ ነው፤ ነገር ግን ፈውሱን የሚያገኘው በሽተኛ እንደሆነ አምኖ መድኃኒቱን የተጠቀመ ብቻ ነው፡፡ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው “መድኃኒት ስላለ ሁሉም ለምን አልተፈወሰም?” ብሎ እንዴት ይጠይቃል?