ኢየሱስ “የተወለድሁት” በማለት ስለራሱ መናገሩ የርሱ ህልውና ከመወለዱ ጋር የጀመረ መሆኑን አያሳይምን?

 


  1. ኢየሱስ በዮሐንስ 18፡37 ላይ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል፡፡” ብሏል፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ የተወለድሁት በማለት ስለራሱ መናገር መጀመሩ ምንን ያመለክታል? የርሱ ህልውና ከመወለዱ ጋር የጀመረ መሆኑን አያሳይምን?

አያሳይም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በመወለድ ወደዚህ ዓለም ቢመጣም ነገር ግን ከመወለዱ በፊት በሰማይ በአብ ዘንድ ይኖር እንደነበረ በብዙ ቦታዎች ላይ ተናግሯልና፡- (ዮሐንስ 3፡13፣ 6፡33-48፣ 6፡62፣ 8፡42፣ 56-58፣ 13፡3፣ በተጨማሪም ዮሐንስ 1፡1-3)፡፡

ኢየሱስ ከእናቱ ከማሪያም ተወልዶ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ለሰው ልጅ ኃጢአት ቤዛ ሊሆን ነውን? እርሱ ግን ምን አለ? “ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፡፡” ታድያ ክርስትያኖች ምነው ኢየሱስን ተቃረኑ?

ለእውነት መመስከር በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነው፡፡ “ሸሂድ” የሚለው ሰማዕትነትን የሚያሳየው የአረብኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “ምስክር” የሚል ሲሆን ጠያቂው በጠቀሱት ጥቅስ ውስጥ ጌታችን የተጠቀመው  “ማርቱሬኦ”[7] የሚለው “ለመመስከር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሰማዕትነትን ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ሰማዕት በመሆን ለእውነት መስክሯል፡፡ ኢየሱስ በሌሎች ቦታዎች ላይ ነፍሱን ለኃጢኣተኞች ቤዛ ለማድረግ መምጣቱን ስለተናገረ (ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 20፡28) ለእውነት ለመመስከር መምጣቱን መናገሩ ተልዕኮው ዘርፈ ብዙ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ በዚህ ብቻ የተወሰነ መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ጠያቂው የተቃርኖን ትርጉም መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡