የኒቂያ ጉባኤ ራሱ “በእግዚአብሔር አብ እናምናለን” እንጂ “አንድ እግዚአብሔር በሚሆኑት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” አይልም።  

 


2. ዶክተር ፓውል እንዝ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በአርዮስ ትምህርት የተነሳ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት በ325 ዓ.ም ኒቅያ በተባለው ስፍራ አንድ ጉባኤ ተካሄደ ፡፡ በጉባኤው ላይ 300 ጳጳሳት ተገኝተው ነበር፡፡ ጉባኤው አርዮስንም ሆነ አርዮሳዊነትን የሚቀበሉትን ሁሉ አውግዟል፡፡ በንጉሡ ካስፀደቀ በኋላም የሚከተለውን የሃይማኖት መግለጫ አወጣ፡-

ሁሉን በሚችል የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በአንዱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከአብ ብቻውን በተገኘው ከአብ ጋር መገኛው (ኡሲያስ / ousias ) አንድ በሆነው፣ ከአምላክ በተገኘው አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነትኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፣ ከአብ ጋር በማንነት (Homoousion) አንድ በሆነ፣ ሁሉ በእርሱ በሆነ፣ በሰማይም ይሁን በምድር ባለው፣ ለእኛ ለሰው ልጆች ደህንነት ወርዶ ሥጋ በሆነ፣ ሰውም በሆነ፣ መከራን በተቀበለበት በሦስተኛውም ቀን በተነሳ፣ ወደ ሰማይ ባረገ፣ በሙታንና በሕያዋን ላይ ሊፈርድ በሚመጣው እናምናለን፡፡” ( ዶክተር ፓወል እንዝ ፣ ታሪካዊ ሥነ- መስኮት አመጣጡና ትንተናው ፣ ገጽ 33 – 34)፡፡

ሀ. ይህ የኒቂያ ጉባኤ ራሱ “በእግዚአብሔር አብ እናምናለን” እንጂ “አንድ እግዚአብሔር በሚሆኑት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡” እንደማይል አስተውለዋልን?

የኒቅያ ጉባኤ ትኩረት ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ነው (Homoousion) ወይስ ተመሳሳይ (Homoiousion)? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ስለነበር መግለጫው የሥላሴን ትምህርት በመተንተን ላይ አላተኮረም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የኒቅያ የእምነት መግለጫ ውስጥ “ከአብ ጋር በማንነት (Homoousion) አንድ በሆነ” ተብሎ የተተረጎመው “በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል” ተብሎ ቢተረጎም የተሻለ ይሆናል፡፡ የአገራችን የሥነ መለኮት ሊቃውንትም ከጥንት ጀምሮ ይህንን ቃል ሲተረጉሙ የነበሩት በዚያው መልኩ ነው፡፡

ለ. በዚህ መግለጫቸው ኢየሱስን “ከአምላክ በተገኘው አምላክ” ሲሉት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለውንና ኢየሱስ ራሱ ያላስተማረውን በመግለጫቸው ስላካተቱ እውነት ይሆናል? “ከአምላክ በተገኘው አምላክ” ሲሉም የተገኘ መሆኑን አምነዋል፡፡ ነገር ግን መልሰው ያልተገኘውን ኢየሱስን (እንደነርሱ አባባል) “አምላክ” አሉት፡፡ አምላክ ሕልውናው ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ኢየሱስ ግን የተገኘ ነው፡፡ የተገኘና ዘለዓለማዊ ያልሆነው ኢየሱስ “አምላክ” ስለተባለ ብቻ አምላክ ሊሆን ይችላልን?

“የተገኘ” የሚለው ቃል በጊዜ የተገደበ መገኘትን ሳይሆን ዘለዓለማዊ መገኘትን ስለሚያመለክት የኢየሱስ ሕልውና ዘለዓለማዊ አለመሆኑን አያመለክትም፡፡ ይህ መገኘት ዘለዓለማዊና በጊዜ ያልተገደበ ሲሆን የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ ከአብ አያሳንስም፡፡ አብ ያሉት ባሕርያተ መለኮት ሁሉ ወልድም አሉት፡፡ አብ በጊዜ ባልተገደበ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት ሲያበራ በነበረ ኮከብ የሚመሰል ሲሆን ወልድ ደግሞ ከኮከቡ በሚወጣው ብርሃን ይመሰላል፡፡ በኮከቡና በብርሃኑ መካከል የጊዜ መቀዳደም የለም፡፡ ነገር ግን ብርሃኑ ከኮከቡ የተገኘ ነው፡፡ ኮከቡ ያለብርሃን እውነተኛ ኮከብ ሊሆን አይችልም፡፡ ብርሃኑም ያለ ኮከቡ ሊኖር አይችልም፡፡ አብና ወልድም እንደዚያው ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተገኘ መሆኑን ደጋግሞ በመናገሩ ጠያቂው ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለና ኢየሱስ እዳላስተማረ መናገራቸው ቅጥፈት ነው፡፡ “ኢየሱስ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ…” (ዮሐንስ 13፡3)፡፡ “እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና” (16፡27-28)፡፡ “ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና” (8:42)፡፡ “ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ” (16:28)፡፡ “ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ” (17፡8)፡፡

 ለተጨማሪ ማብራርያ ለጥያቄ ቁጥር 75 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ፡፡

ሐ. “ኢየሱስ የተወለደ ነው” ግና አልተፈጠረም ሲሉ፡- “በተፈጠረው ሳይሆን በተወለደ” ብለዋል፡፡ “ተወለደ” ስንል ከመወለዱ በፊት ነበርን? “በተፈጠረ ሳይሆን” የተባለበት ምክንያት “ተፈጠረ” ካልን “ፍጡር” እንዳይሰኝ ነውን? “ፍጡር” ስላላልን መሆኑ ይቀራልን?

“መወለድ” የሚለው ቃል ኢየሱስ ከአብ ባሕርይ በዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) የተገኘ መሆኑን ለማመልከት በመሆኑ ጊዜን አያመለክትም፡፡ ጠያቂው ቃላትን በራሳቸው መንገድ ከመተርጎም ይልቅ የእምነት መግለጫውን ያወጡት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለማለት የፈለጉትን ለመረዳት ቢሞክሩ መልካም ነበር፡፡

መ. በመግለጫው እንደተባለው “ለእኛ ለሰው ልጆች ደህንነት ወርዶ ሥጋ በሆነ፣ ሰውም በሆነ” ኢየሱስ ለሰው ልጅ ደህንነት ሲል ወርዶ ሥጋ ከሆነ ወደ ሰማይ አርጎ ለምን ሰውነቱን (ሥጋውን) ትቶ ከመውረዱ በፊት ለምድነው “ነበር” ወደተባለበት ሁናቴ ያልተመለሠው? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ሆነ በእለተ ትንሳኤ ሰው ሆኖ (ሥጋ ሆኖ) እንጂ ቀድሞ በነበረበት ሁናቴ ይመጣል አይልም፡፡ ታድያ ኢየሱስ ለሰው ልጅ ሲል አምላክነቱን (ባህሪውን) ሙሉ ለሙሉ ትቶ (ሥጋ ለባሽ) ሆኖ ቀረ ማለት ነው?

ጠያቂው ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ከአምላክነት ወደ ሰውነት ተለውጧል የሚል የተሳሳተ መረዳት ስላላቸው ጥያቄውን ያቀረቡት ከዚህ የተሳሳተ መረዳት በመነሳት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ሰብዓዊ ባሕርይን በመለኮታዊ ባሕርዩ ላይ አከለ እንጂ ሰው ወደመሆን አልተለወጠም፡፡ ወደ ሰማይ ያረገውም በትንሣኤው አካል ነው፡፡ አምላካዊና ሰብዓዊ ባሕርያቱ ሳይነጣጠሉና ሳይደባለቁ ይኖራሉ፡፡

ሠ. እውን ኢየሱስ “በሦስተኛው ቀን በተነሳ” እንደተባለው በሦስተኛው ቀን ተነሥቶአልን?

 አዎ በሦስተኛው ቀን ተነስቷል፡፡ “ሦስተኛው ቀን” የተባለው በአይሁድ መረዳት መሠረት በመሆኑ ከኛ ልማድ በመነሳት መተርጎም የለብንም፡፡

ረ. ይህ የኒቅያ ጉባኤ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ሲያወሳ “ከአንዱ አምላክ እግዚአብሔር ክፍል ነው፤ ራሱም አምላክ ነው” የሚባለውን መንፈስ ቅዱስን ለምን ዘነጋ? እስከዚያ ጊዜ ድረስ የመንፈስ ቅዱስ “አምላክነት” በኒቅያ ጉባኤ ለተሳተፉት 300ዎቹ ጳጳሳት አልታያቸውም ነበርን?

የኒቅያ ጉባኤ ዋና ትኩረት የክርስቶስ ማንነት እና ከአብ ጋር ያለው የባሕርይ አንድነት በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት ላይ አላተኮረም፡፡ ነገር ግን ጠያቂው እንዳሉት የኒቅያ ጉባኤ መንፈስ ቅዱስን አልዘነጋነም፡፡ የመጨረሻው አንቀፅ “በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን” በማለት ይዘጋል፡፡ በወቅቱ በመንፈስ ቅዱስ ማንነት ላይ ጥያቄ ስላልተነሳ ዋና የመወያያ ርዕስ አልሆነም፡፡ ኋላ ላይ አርዮስ “የወልድ የመጀመርያ ፍጡር መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት አዲስ ትምህርት ማስተማር በመጀመሩና መቅዶንዮስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ “ልክ እንደ መላእክት ፍጡር የሆነና የወልድ ተገዢ ነው” በማለት በማስተማሩ ምክንያት በ381 ዓ.ም. የቁስጥንጢንያ ጉባኤ እነዚህን ኑፋቄዎች ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ አውጥቷል፡፡[8]

ሰ. የሥላሴ ምስጢር ለምን እስከ አራተኛው ክ/ ዘመን ሳይታወቅ ቀረ? ለምንስ በኒቅያ ጉባኤ በማስረጃ ብልጫ ሳይሆን በድምፅ ብልጫ ተወሰነ?

የሥላሴ አስተምህሮ እስከ ኒቅያ ጉባኤ ድረስ አልታወቀም የሚለው የጠያቂው አባባል ፍፁም ቅጥፈት ነው፡፡ ሥላሴ (Trinity) የሚለውን የላቲን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀመው ጠርጡሊያኖስ የተሰኘ (160-220 ዓ.ም.) የቤተ ክርስቲያን አባት ሲሆን ከኒቅያ ጉባኤ ከመቶ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኒቅያ ጉባኤ ዋና የመወያያ ነጥብ የነበረው ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ነው ወይንስ ተመሳሳይ? የሚል እንጂ የሥላሴ አስተምህሮ ትንተና አልነበረም፡፡ ጠያቂው የሥላሴ አስተምህሮ በማስረጃ ብልጫ ሳይሆን በድምፅ ብልጫ እንደፀደቀ የተናገሩት ነጥብ በራሱ ማስረጃ አልባ አሉባልታ ነው፡፡

ሸ. የክርስትና ሃይማኖት ጸሐፊው “በኒቅያው ጉባኤ የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ ከሥላሴ አካላት የአንዱ የመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ በግልጥ አልተቀመጠም፡፡ መግለጫው ያረጋገጠው “በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” የሚለውን ብቻ ነበር፡፡ የቆስጠንጢኒያው ጉባኤ በ381 ዓ.ም. “ጌታ በሆነና ህይወት በሚሰጥ፣ ከአብ በሚወጣና ከአብና ከወልድ እኩል አምልኮን በሚቀበል፣ በነቢያትም በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” የሚለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው መንፈስ ቅዱስ በህልውና ከወልድና ከአብ ያነሰ ሳይሆን እኩል መሆኑን በፅኑ አረጋግጧል፡፡” ይላሉ፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስም እንደወልድ ከአብ የሚወጣ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም የፈጣሪ ልጅ ነውን? ካልሆነስ ለምን?

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በመንፈስ ቅዱስና በአብ መካከል ያለው ሕብረት በአባትና በልጅነት አልተገለፀም፡፡ በሥላሴ አካላት መካከል ያለውን ሕብረት የመምረጥና የመግለፅ መብት የሥላሴ እንጂ የሰው ልጆች ባለመሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከሰፈረልን በማለፍ አንናገርም፡፡