ዘፍጥረት 1፡26 ላይ “በአምሳላችን” ሲል ሰው በየትኛው አምሳል ነው የተፈጠረው ሊባል ነው? በአብ፣ በወልድ ወይስ በመንፈስ ቅዱስ?

 


9. ክርስቲያኖች እንደሚሉት ዘፍጥረት 1፡26 ላይ “ሰውን በመልካችን፤ በአምሳላችን እንፍጠር” ሲል ሥላሴን ለማመልከት ከሆነ ታዲያ “በአምሳላችን” ሲል ሰው በየትኛው አምሳል ነው የተፈጠረው ሊባል ነው? በአብ፣ በወልድ ወይስ በመንፈስ ቅዱስ? አልያም በሦስቱ አካላት ውህደት ተፈጠረ? ብሉይ ኪዳንን “ጠብቀው አቆዩ” የሚባሉት አይሁዶችስ ይህንንም ሆነ መሰል በሥላሴ በሚያምኑ ክርስቲያኖች ለማስረጃነት የሚቀርቡ ጥቅሶች ሳይረዱና በሥላሴ ሳያምኑ መጽሐፉን “ጠብቀው አቆዩ” ማለት ያስኬዳልን?

መጽሐፉን ጠብቆ ማቆየት እና መጽሐፉ የሚለውን መረዳት በምን ይገናኛሉ? “ሰዎች በእጃቸው የሚገኘውን መጽሐፍ ትርጉም በትክክል ሳይረዱ ጠብቀው ማቆየት አይችሉም” ማለት ምን የሚሉት አመክንዮ ነው? ጠያቂው የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም ወደ ዋናው ቋንቋ በመሄድ የማስረዳት አቅም ስለሌላቸው አይሁድ ጥቅሱን ክርስቲያኖች በሚረዱት መንገድ አለመረዳታቸውን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ አወናብደው ለማለፍ ጥረት አድርገዋል፡፡[9] የሥላሴን ትምህርት የማይቀበሉ ወገኖች ይህንን ጥቅስ በሁለት መንገዶች ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ የመጀመርያው እግዚአብሔር “እንፍጠር” ሲል ከመላእክት ጋር መማከሩ ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ራሱን በማክበር ልክ ነገሥታት “እኛ” በሚሉት መንገድ መናገሩ ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ ምላሾች በፍፁም የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡ ሰው በመላእክት መልክ እንደተፈጠረ ቅዱሳት መጻሕፍት አያስተምሩም፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን በመፍጠር ሂደት ውስጥ መላእክትን እንዳሳተፈ የሚገልፅ አንድም የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ አናገኝም፡፡ እንዲያውም በተጻራሪው እግዚአብሔር ብቻውን ፍጥረትን እንደፈጠረና አጋዥ እንዳልነበረው ይናገራል (ኢሳይያስ 44፡24)፡፡ ራስን ለማክበር በብዙ ቁጥር መናገር በጥንቱ እብራይስጥ ውስጥ ስለማይታወቅ ሁለተኛውም ምላሽ ሊያስኬድ አይችልም፡፡ እንዲህ ያለ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ቢሆን ማስረጃ የለውም፡፡ ስለዚህ ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ከአንድ በላይ አካላት እንዳሉት የሚያመለክት ነው፡፡ ሰው የሥጋ፣ የነፍስ እና የመንፈስ ጥምረት በመሆኑ በእግዚአብሔር የሥላሴያዊ ባሕርይ አምሳል ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ የእግዚአብሔር ሥላሴያዊነት አንዱ ማስረጃ ነው፡፡