በሥላሴ ማመን እና በርሱ ስም መጠመቅ ብቸኛ የመዳኛው መንገድ ከሆነ ኢየሱስ ለምን በግልፅ ትኩረት ሰጥቶ አላስተማረበትም?

 


11. በሥላሴ ማመን እና በርሱ ስም መጠመቅ ብቸኛ የመዳኛው መንገድ ከሆነ ኢየሱስ ለምን በግልፅ ትኩረት ሰጥቶ አላስተማረበትም? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ሥላሴ” የምትለው ቃል ስላልሰሙና በወቅቱ የማትታወቅ ስለነበረች እነርሱም አልዳኑም ማለት ነውን?

አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የሚሉትን መጠርያዎች ለመጀመርያ ጊዜ በአንድነት አጣምሮ የጠቀሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማቴዎስ 28፡19-20)፡፡ በዚሁ ቦታ በሥላሴ ስም የመጠመቅን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ እነዚህ ሦስቱ አካላት አንድ ስም እንዳላቸው በማመልከት የባሕርይ አንድነታቸውን አስታውቋል፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለመገኘቱ አስተምህሮው የለም ማለት አይደለም፡፡ የነገረ መለኮት ሊቃውንት የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶችን ጨምቀው ለማስቀመጥ የሚጠቀሟቸው ብዙ ቃላት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አይገኙም፡፡ ቃላቱ ፅንሰ ሐሳቦቹን እስከገለፁ ድረስ መጠቀም ስህተት አይደለም፡፡ ጥቅም እንጂ ጉዳትም የለውም፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን ብዙ ጊዜ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህና እንዲያ የሚሉ ነገሮችን አሳዩን” የሚሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ መጠበቃቸውና ክርስቲያኖችን በእስላማዊ መረዳት ልክ በተሰራ ጠባብ ክፍል ለመገደብ መሞከራቸው ልክ ካለመሆኑም በላይ አስፍቶ አለማሰብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ለመቀበል አስተምህሮው እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት የሚያምኑ ከሆነና ሥላሴ የሚለውን የመሳሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ፅንሰ ሐሳቦችን የሚወክሉ ሥነ-መለኮታዊ ቃላት ክርስቲያናዊ ለመሆን የግድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀስ አለባቸው የሚሉ ከሆነ ይህንኑ መስፈርት በቁርኣን ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን የሚሞክሩትን መስፈርት ለቁርኣን የማይጠቀሙ ከሆነ ለእውነት ታማኞች ያልሆኑ በአባይ ሚዛን የሚመዝኑ ግብዞች መሆናቸውን በራሳቸው ላይ ያስመሰክራሉ ማለት ነው፡፡ እነኚህ ወገኖች ጥያቄዎቻቸው እና መስፈርቶቻቸው ኢ-ምክንያታዊ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድ ራሳቸው የቀመሙትን መድኃኒት ማቅመስ መተኪያ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ በማስከተል በተደጋጋሚ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ወደ እነርሱ በማዞር እንጠይቃቸዋለን፡፡ ዛሬ ሙስሊሞች እየተከተሏቸው የሚገኙት በርካታ ሥርኣቶች እና የሚጠቀሟቸው ጥቂት የማይባሉ እስላማዊ ቃላት በቁርኣን ውስጥ የማይገኙ ናቸው፡፡ ስለ አላህ፣ ስለ ዒሳ እና ስለ ሙሐመድ የሚያምኗቸው በርካታ ነገሮች በእነዚህ አካላት ቃል በቃል በቁርኣን ውስጥ በቀጥታ ያልተነገሩ ናቸው፡፡ ሙስሊም ወገኖች አንድን አስተምህሮ ለመቀበል ወይም አንድን ቃል ለመጠቀም የግድ እነርሱ በሚፈልጉት ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ መገኘት እንዳለበት ካመኑ የሚከተሉትን ቃላት፣ አስተምህሮዎች፣ ንግግሮች እና ትዕዛዛት ከቁርኣን በማውጣት እንዲያሳዩን እንጠይቃቸዋለን፡፡

  • ተውሂድ የሚለውን ቃል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ፅንሰ ሐሳብ ሥላሴ እንደሚሰኝ ሁሉ የቁርአኑ የአላህ ፅንሰ ሐሳብ ተውሂድ በመባል ይታወቃል፡፡)
  • ሦስቱን የተውሂድ ክፍሎች፣ ማለትም ተውሂድ አሩቡቢያ፣ ተውሂድ አል ኡሉሂያ እና አስማ ወስሲፋት፡፡ (ተውሂድ የሚለውም ቃል ሆነ ሦስቱ ክፍሎቹ ቃል በቃል በቁርኣን ውስት ተጠቅሰው አናገኝም፡፡)
  • “ላ ኢላ ሀኢለላህ መሐመደን ረሱልአላህ” (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም መልዕክተኛው ናቸው) የሚለው እስላማዊ የእምነት መግለጫ ልክ በዚህ ሁኔታ የተጻፈበትን ቦታ፡፡ የተቆራረጠውን በማገጣጠም እንድታሳዩን አንፈልግም፡፡
  • በቀን አምስት ጊዜ ስገዱ የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም መገረዝ አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ዝሙት የሰራ ሰው በድንጋይ ተወግሮ መሞት አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ሙስሊም የካዕባን ድንጋይ መሳም አለበት የሚል ትዕዛዝ፡፡
  • ኢብራሂም ለመስዋዕትነት ያቀረበው ልጅ ኢስማኤል ነበር የሚል አንድ ጥቅስ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ መሲህ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ከድንግል ነው የተወለድኩት ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ የአላህ ቃል እና ከእርሱ የሆንኩ መንፈስ ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ሙስሊም ነኝ ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በምድር ላይ እያለ በራሱ አንደበት እኔ አምላክ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡ (ወደ ፊት አላህ ሲጠይቀው ይናገራል ተብሎ በቁርኣን ውስት የተጠቀሰ ነገር ካለ አንቀበልም ምክንያቱም ዒሳ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የተናገረው አይደለምና፡፡ ወደ ፊት ይናገራል ተብሎ የተጠቀሰው ንግግር እውነትም ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እንደ ዒሳ ንግግር ሊቆጠር አይችልም፡፡)
  • ዒሳ በራሱ አንደበት ቃል በቃል እኔ የአላህ ልጅ አይደለሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • ዒሳ በራሱ አንደበት እኔ ስለ ሰው ልጆች ኃጢኣት ለመሞት እና በሦስተኛው ቀን ለመነሳት አልመጣሁም ያለበትን ቦታ፡፡
  • አላህ ያወረዳቸው የቁርኣን ሱራዎች 114 ብቻ እንደሆነ የተጻፈበትን ቦታ፡፡
  • የቁርኣን ሱራዎችን ስሞች አላህ እንደገለጣቸው የተነገረበትን ቦታ፡፡
  • የአደም ሚስት ስም ማን መሆኑን የሚናገር ቦታ፡፡ (ቁርኣን ከማርያም ውጪ የትኛዋንም ሴት በስም አልጠቀሰም፡፡ በአማርኛ ቁርኣን ወይንም በሌሎች ትርጉሞች ውስጥ በቅንፍ ተጠቅሰው የምታገኟቸው የሴት ስሞች ሁሉ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ አይገኙም፡፡ የተርጓሚዎቹ ጭማሬዎች ናቸው፡፡)

ውድ አሕመዲን፤ እነዚህን ነገሮች ከቁርኣን አውጥተው ሊያሳዩን የማይችሉ ከሆነ መሰል ጥቄዎችን መጠየቅ ለትክክለኛ ውይይት እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ውጤት እንደሌለው ተረድተው ከደረቅ ክርክር ይቆጠቡ ዘንድ እንመክርዎታለን፡፡ ጥያቄዎችዎ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲመለሱ በመጠበቅ ክርስቲያኖችን በጠባብ ክፍል ውስጥ ለማሰር የሚሞክሩ ከሆነ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ሲጠየቁ መግቢያ ይጠፋዎታልና አያዋጣዎትም እንላለን፡፡