ሥላሴ አስተምህሮቱም ሆነ ምስጢርነቱ የቱ ጋር ነው የተገለጸው?

 


16. የሥላሴ አስተምህሮ “ምስጢር” ነው ይባላል፡፡ ሥላሴ አስተምህሮቱም ሆነ ምስጢርነቱ የቱ ጋር ነው የተገለጸው? የሚገርመው ግን ምስጢር ነው እየተባለ ማስተማሩን ይቀጥሉበታል፡፡ ጥያቄ ሲነሳ ግን “ምስጢር ነው” ይባላል፡፡ እምነትና አምልኮ ምን ምስጢር ያስፈልገዋል?

ሙስሊም ወገኖች በድፍረትና በግብታዊነት ከሚናገሯቸው ነገሮች መካከል የከፋው ይኸኛው ነው፡፡ በፈጣሪ የሚያምን ሰው ስለ ፈጣሪ ምስጢራዊነት ሲነገር እንዴት ግራ ይገባዋል? ሥላሴ ምስጢር ነው ስንል ከሰው አዕምሮ በላይ ነው ማለታችን እንጂ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ በድብቅ የሚያዝ፣ ለሌላው ሕዝብ የማይነገር ጉዳይ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ መሠረታዊውን የሥላሴ ትንተና መረዳት ቢቻልም ነገር ግን ወደ ውስጥ ጠልቀን ለመረዳት የማይቻልና ከአዕምሮ በላይ የሆነ ነው፤ ምክንያቱም ሥላሴ እግዚአብሔር ነውና! መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በሰው አዕምሮ ሊመረመርና ሊለካ እንደማይችል አጥብቆ ያስተምራል፡- “እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም፡፡ የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም፡፡” (ኢዮብ 36:6)፡፡

በፍጥረተ ዓለም ውስጥ እንኳ ብዙ ያልተፈቱ ምስጢራት ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕዋ ተመራማሪዎች በሕዋ ውስጥ የሚገኙትን አካላት አንድ ላይ አጥብቆ ሊይዝ የሚችል በቂ ስበት እንደሌለ ደርሰውበታል፡፡ ነገር ግን የአፅናፈ ዓለም 26.8 ከመቶ ፀሊም ቁስ (Dark Matter) በተሰኘ ምንነቱ በማይታወቅና በዓይን በማይታይ ነገር እንደተሞላና ይህ ነገር በስበት መልክ ሳይሆን ልክ እንደ ፈሳሽ ማጣበቂያ (Glue) አፅናፈ ዓለምን አንድ ላይ አጣብቆ እንደያዘ ይናገራሉ፡፡[10] በተጨማሪም የአፅናፈ ዓለም 68.3 ከመቶ ደግሞ ፀሊም ኃይል (Dark Energy) በተሰኘ ምንነቱ በማይታወቅ ኃይል የተሞላ መሆኑን፣ ይህም ኃይል አፅናፈ ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት ስፋቱ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለ እነዚህ ነገሮች ሲናገሩ “ምስጢር ናቸው” ይላሉ፡፡[11] የፍጥረቱን ምስጢር መርምሮ ያልደረሰበት ውሱን የሆነው የሰው ልጅ ሃያሉ ፈጣሪ ምስጢር አለመሆኑን ለማሰብ እንኳ መድፈሩ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡