ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ ሐዋርያት ሥራ 12፡24 «የእግዚአብሔር ቃል ግን እንደገና እየሰፋ ሄደ» ይላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ይሰፋል?

 


32. የሐዋርያት ሥራ 12፡24 «የእግዚአብሔር ቃል ግን እንደገና እየሰፋ ሄደ» ይላል፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮት «ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃልና ራሱም አምላክ ነው፡፡» የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ አምላክ ከሆነ እንደዚህኛው ጥቅስ የእግዚአብሔር ቃል እያደገና እየሰፋ ሄደ ማለት ነው፡፡ ታድያ ይህ የሚመስል ነውን?

የአንድ ቃል ትርጉም የሚወሰነው በአውዱ ነው፡፡ በዚህ ቦታ “ቃል” የተባለው ወንጌል ነው፡፡ እየሰፋ መሄዱ የተነገረው በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ለማመልከት ነው፡፡ ዮሐንስ 1፡1-18 ደግሞ “ቃል” ሲል ፍጥረትን የፈጠረውን፣ የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነውን አንድያ ልጁን ለማለት ነው፡፡ የሁለቱ አውድ ለየቅል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን የአላህ ቃል መሆኑን ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ዒሳም የአላህ ቃል ነው ይላሉ (ሱራ 4፡171)፡፡ ስለዚህ ዒሳ ቁርኣን ነው ማለት ነውን?