ሐዋሪያት የኢየሱስን ተአምራዊ ምልክት አይተው የዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚሉት “ኢየሱስ ጌታ ነው! አምላክ ነው!” ነበር ያሉት?

 


7. ዮሐንስ 6፡14 “ሰዎቹም ኢየሱስ ያደርገውን ተአምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው አሉ” ይላል፡፡ የኢየሱስን ተአምራዊ ምልክት አይተው የዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚሉት “ኢየሱስ ጌታ ነው! አምላክ ነው!” ነበር ያሉት? ጥቅሱ የሚነግረን “የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው” እንዳሉ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ታድያ ምን ነው ይህን ማመን አልፈለጉም?

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ያምናሉ ነገር ግን ነቢይ ብቻ ነው አይሉም፡፡ ሕዝቡ በገባው መጠን መስክሯል ነገር ግን የሕዝቡን ምስክርነት መሠረት አድርገን ለድምዳሜ አንፈጥንም፡፡ ጠያቂው ኢየሱስን በቅርበት የማያውቀውን ሕዝብ ምስክርነት ከተቀበሉ ኢየሱስን በቅርበት የሚያውቁትን የሐዋርያቱን ምስክርነት ይበልጥ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ሐዋርያቱ ተዓምራቱን ካዩ በኋላ የሰጡት ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡- “በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት፡፡” (ማቴዎስ 14፡33)፡፡ እኛም ከእነርሱ ጋር በመስማማት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንመሰክራለን፤ እንደ ጌትነቱና እንደ አምላክነቱ መጠን የሚገባውንም ስግደት እንሰጠዋለን፡፡