ኢየሱስ የሚያስተምረው ትምህርት ከራሱ ሳይሆን ከላከው አምላክ መሆኑን እየገለጸ እንዴት ክርስቲያኖች ክርስቶስን አምላክ ሊሉት ቻሉ?

 


11. ዮሐንስ 7፡16-17 “ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው፡፡ ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል” ይላል፡፡ ኢየሱስ የሚያስተምረው ትምህርት ከራሱ ሳይሆን ከላከው አምላክ መሆኑን እየገለጸ እንዴት ክርስቲያኖች ክርስቶስን አምላክ ሊሉት ቻሉ?

ይህንን ጥቅስ ኢየሱስ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ራሱን ባዶ አድርጎ የባርያን መልክ ይዞ መምጣቱን በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አውድ ማየት ያስፈልጋል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ ኢየሱስ ራሱን ለማክበርና ከፍ ከፍ ለማድረግ ስላልመጣ በአምላካዊ ባሕርዩ ሳይሆን በሰብዓዊነቱ በሰዎች ፊት ለመታየትና ለማገልገል በመወሰኑ ምክንያት ፍፁም ሰው ሆኖ ተመላልሷል፡፡ ይህንንም በቀጣዩ ቁጥር ላይ አስታውቋል፡- “ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም፡፡” (ቁ.18)፡፡ ኢየሱስ የራሱን ክብር ለመፈለግ አለመምጣቱን ከአብ የሰማውን ብቻ በመናገር አሳይቷል፡፡