በኢየሱስ ተአምር አይነ ስውርነቱ የተወገደለተ ግለሰብ ኢየሱስን “ነብይ” ካለ ክርስቲያኖች ሙስሊሞች “ኢየሱስ ነብይ ነው” በማለታቸው እንዴት ሊያወግዙ ቻሉ?

 


13. ዮሐንስ 9፡17 “ስለዚህ አይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው አይንህን ስለከፈተው ሰው እንግዲህ አንተ ምን ትላለህን? አሉት፡፡ ሰውየውም “እርሱ ነብይ ነው አለ” ይላል፡፡ በኢየሱስ ተአምር አይነ ስውርነቱ የተወገደለተ ግለሰብ ኢየሱስን “ነብይ” ካለ ከዘመናት ቆይታ በኋላ የተነሱት ክርስቲያኖች ሙስሊሞች “ኢየሱስ ነብይ ነው” በማለታቸው እንዴት ሊያወግዙ ቻሉ?

ሙስሊሞች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን በማመናቸው አልተሳሳቱም፡፡ ይህንንም በማመናቸው ምክንያት በክርስቲያኖች አልተወገዙም፡፡ ነገር ግን “ነቢይ ብቻ ነው” በማለት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ አምላክነቱና የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለመሆኑ የተገለጡትን እውነቶች በመካዳቸው ነው የተሳሳቱት፡፡ አሕመዲን ንባባቸውን ባያቆሙ ኖሮ ኢየሱስ ማንነቱን ከገለጠለት በኋላ የተፈወሰው ሰው የሰጠውን ምላሽ ማየት በቻሉ ነበር፡- “ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም፦ አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ፡፡ ኢየሱስም፦ አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው፡፡ እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም፡፡” (ቁ. 35-38)፡፡ ሰውየው መጀመርያ ነቢይ መሆኑን ብቻ ነበር ያወቀው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሲገነዘብ ደግሞ ጌትነቱን ተቀብሎ በፊቱ በመስገድ የሚገባውን ክብር ሰጥቶታል፡፡