አምላክ እንዴት የት እንደተደበቁ ማወቅ ተስኖት አዳምን “የት ነህ?” ሲል ይጠይቃል?
2. መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ላይ እንዲህ ይላል፦ “ቀኑ መሸትሸት ሲል፤ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሔዋን ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፤ “የት ነህ”? አለው፡፡” አዳምም፤ “ድምጽህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ፡፡” ዘፍጥረት (3፡8-10)፡፡ እግዚአብሔር “ዕራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ በላህን?” አለው፡፡” (ዘፍጥረት 3፡11)፡፡ ይህ አንቀፅ እውን የአምላክ ቃል ነውን? ከሆነስ አምላክ እንዴት የት እንደተደበቁ ማወቅ ተስኖት አዳምን “የት ነህ?” ሲል ይጠይቃል? የተከለከለውን ዛፍ ይብላ ወይም አይብላስ ጠይቆ ነው የሚያረጋግጠው?
እግዚአብሔር አምላክ አዳም ያለበትን ቦታ በራሱ አንደበት እንዲናገር ፈልጎ እንጂ የት እንዳለ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ የተከለከለውንም ዛፍ ስለመብላቱ በገዛ አንደበቱ እንዲናዘዝ ፈልጎ እንጂ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው የፈፀሙትን ጥፋት እያወቁ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ማናዘዝ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጥፋታቸውን እንዲገነዘቡና እንዲፀፀቱ በማድረግ ረገድ በቀጥታ ከመውቀስ የተሻለ ነው፡፡ አሕመዲን እንደ ሙስሊምነታቸው ይህንን የሚጠይቁ ከሆነ አምላካቸው አላህም በተመሳሳይ መንገድ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ በተደጋጋሚ ስለሚታይ እርሱንስ ምን ሊሉት ነው?
ሱራ 38፡75 “(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! በሁለት እጆቼ (በኃይሌ) ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ?» አለው፡፡”
ምን እንደከለከለው እንዴት ማወቅ አልቻለም? የከለከለው ኩራት መሆን አለመሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን ተሳነው? ኩራት መች እንደጀመረው ጠይቆ ነው የሚያረጋግጠው?
ሱራ 2፡260 “ኢብራሂምም «ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ፡፡) አላህ ፡- «አላመንክምን?» አለው፡፡ «አይደለም (አምኛለሁ)፤ ግን ልቤ እንዲረጋ» ነው አለ፡፡
ማመን አለማመኑን እርግጠኛ ስላልሆነ ይሆን ይህንን ጥያቄ የጠየቀው?
አሕመዲን ይህንን ደካማ የሆነ ጥያቄ ማንሳታቸው የገዛ መጽሐፋቸውን እንኳ በወጉ አለማወቃቸውን ያመለክታል፡፡