ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎዋልን? እንዴትስ ታግሎ አሸነፈ? 

 


6. ዘፍጥረት 32:22-28 “…አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ፡፡ ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤  በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመገጠሚያው ላይ ተናጋ፡፡ በዚያን ጊዜ ሰውየው፤  “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆን ልቀቀኝና ልሂድ” አለው፡፡ ያቆብም፤ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው፡፡ ሰውየውም፤  ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ አይባልም” አለው” ይላል፡፡ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎዋልን? እንዴትስ ታግሎ አሸነፈ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ ይህ ነው ማለት ነው?

የያዕቆብ ሕይወት ከመጀመርያው እስከዚያች ዕለት ድረስ በትግል የተሞላ ነበር፡፡ ያዕቆብ በተፈጠሮው እንደ ስሙ በማታለል ይኖር የነበረ ሰው ሲሆን ያንን ሁሉ ትግል ያደርግ የነበረው እውነተኛውን በረከት ፍለጋ ነበር፡፡ እውነተኛውን በረከት ሳያገኝ ዕድሜው ቢገፋም አሁን ግን ምንጩን አግኝቶታል፡፡ እግዚአብሔር በተመጠነ ኃይል ሆኖ በአካል ተገልጦ ተገዳደረው፡፡ ያዕቆብ ማንነቱን ስለተገነዘበ እንዲባርከው አጥብቆ ያዘው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በያዕቆብ አቅም ልክ የገለጠው ፅናቱን ለመፈተን ሲሆን ያዕቆብም የመጨረሻ እንጥፍጣፊ አቅሙን በመጠቀም በረከቱን ለማግኘት በመታገል ፅናቱን አሳይቷል፡፡ እግዚአብሔርም “ተሸነፈለት”፡፡ ይህ “መሸነፍ” ግን በያዕቆብ ኃይል የሆነ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመመጠን ተገልጦ ለያዕቆብ ፅናት ማረጋገጫ ሲል መሸነፍን ስለፈቀደ ነበር፡፡ (አባቶች ልጆቻቸውን ፅናትና በራስ መተማመንን ለማስተማር የሆነ ነገር በእጃቸው ይዘው እንደሚታገሉትና በመጨረሻም ለልጆቻቸው እንደሚሸነፉት ዓይነት ማለት ነው፡፡) ይህ እግዚአብሔር አምላካችን ምን ያህል ለኛ የቀረበና እንደ አባት የሚወደን መሆኑን የሚያሳይ እጅግ ውብ ታሪክ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ ወደ ምድር በመምጣት ከእኛ ጋር እንዲኖርና እንዲሞትልን ያደረገው ለኛ ያለው ፍቅር ነው፡፡ ሙስሊሞች የሚያመልኩት አምላክ ከሰው ልጆች እጅግ ሩቅ የሆነና የግል ሕብረት ለማድረግ የማይፈቅድ በመሆኑ ምክንያት መሰል ታሪኮች ጥያቄ ቢፈጥሩባቸው አያስገርምም፡፡