እግዚአብሔር ይፀፀታልን?

 


9. አሞፅ 7፡1-6 “ጌታ እግዚያብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ ፤ ምድሪቱንም በላ ፡፡ ከዚያም በኃላ ፤ “ጌታ እግዚያብሄር ሆይ! እንድትተወው እለምንሃለሁ ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ አልሁ ፡፡ 
እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተፀፀተ ፤ ጌታ እግዚአብሔር፤ “ይህም ደግሞ አይፈፀምም” አለ” ይላል ፡፡ አምላክ ይፀፀታልን?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ተፀፀተ” ሲል እንደ ሰው ያለ ፀፀት አለመሆኑን በሌሎች ቦታዎች ላይ ግልፅ አድርጓል፡- “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡” (ዘኍልቍ 23፡19)፡፡ “የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው፡፡” (1ሳሙኤል 15፡29)፡፡

በነዚህ ቦታዎች ፀፀትን ለማመልከት የገባው የእብራይስጥ ቃል “ናኻም” የሚል ሲሆን በተለያዩ አውዶች ውስጥ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች ተመልከቱ፡-

“እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ (ናኻም)፡፡” (ዘጸአት 32፡14)

“ግብፃውያንስ፦ በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ (ናኻም)፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ፡፡” (ዘጸአት 32፡12)

“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል (ናኻም)” (ዘዳግም 32፡36)

“ምሕረትህ ለመጽናናቴ (ናኻም) ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው፡፡” (መዝሙር 119፡76)

“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና (ናኻም)፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና፡፡” (መዝሙር 135፡14)

“በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል፡፡ እንግዲህ በዚህ ነገር አልቁጣምን (ናኻም)?” (ኢሳይያስ 57፡6)

“አጽናኑ (ናኻም)፥ ሕዝቤን አጽናኑ (ናኻም) ይላል አምላካችሁ፡፡” (ኢሳይያስ 40፡1)

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደ ሰው እንደማይፀፀት ከነገረን፤ ናኻም የሚለው የእብራይስጥ ቃል ደግሞ በብዙ መንገዶች ሊተረጎም ከቻለ (መራራት፣ መመለስ፣ ማዘን፣ መጽናናት፣ መፍረድ፣ መቆጣት)፤ ጠያቂው እግዚአብሔር “እንደተፀፀተ” የሚናገሩትን ጥቅሶች አጥብበው መተርጎማቸው ትክክል አይደለም፡፡ ዘፍጥረት 6፡6 እና 1ሳሙኤል 15፡35 ላይ የሚገኙት ጥቅሶች እግዚአብሔር ማዘኑን ለመግለፅ የተነገሩ ሲሆኑ (NIV ትርጉም “Grieved” ብሎ ተርጉሟቸዋል) አሞፅ 7፡1-6 ላይ የሚገኘው ደግሞ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሊፈፅመው ከነበረው ፍርድ መታቀቡን ያመለክታሉ፡፡