ፈጣሪ ሁሉን አዋቂ አይደለምን? እንዴት የደም ምልክት ሳይጠቀም የእስራኤላዊያንን ቤት ከግብፃዊያን ለይቶ አያውቅም?

 


14. ዘጸአት 12:12-13 “እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብጽም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንሞ ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ” ይላል፡፡ እስራኤሎች በግብጻውያን ባርነት ውስጥ ለ400 ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በስተመጨረሻም እግዚአብሔር እስራኤሎችን በማዳን ግብፃዊያንን ሊያጠፋ ፈለገ፡፡ ይህን ዓላማውን ለማሳካት የተጠቀመበት መንገድ እስራኤሎችን የራሳቸውን ቤት ለይቶ ማሳየት የሚችል የደም ምልክት ደጃፉን እዲቀቡና እርሱም ደሙን ባየ ሰዓት ከነርሱ እያለፈ ሌሎች ሊያጠፋ ነው፡፡ ፈጣሪ ሁሉን አዋቂ አይደለምን? እንዴት የደም ምልክት ካልተጠቀመ አያውቅም እንላለን?

የደሙ ምልክት እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን ቤት ለይቶ እንዲያውቅ ሳይሆን ኃጢአታቸውን በመሸፈን ከእግዚአብሔር ፍርድ እንዲያድናቸው ነው፡፡ የደሙ ምልክት የሌላቸው ቤቶች ስላልተዋጁ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያስተናግዳሉ፡፡ ይህ የፋሲካ በግ የክርስቶስ ምሳሌ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (1ቆሮንቶስ 5፡7)፡፡ ክርስቶስ ራሱ የተሰቀለው የፋሲካው በግ በሚታረድበት የፋሲካ ዋዜማ ነበር፡፡