ምሁራን ስለ ወንጌላት ጻሐፊያን ግምት እንጂ እርግጠኞች አይደሉም!

 


2. ከላይ ያየናቸው የክርስቲያን ምሑራን ሁሉም በስምምነት የጻፉት በጥርጣሬና ግምት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ በመላምት ተንተርሰው ነው፡፡ ታድያ “ይሆናል” ፤ “ይገመታል” ፤ “ሊሆን ይችላል” ፤ “ይመስላል” ፤ “ሳይሆን አይቀርም” በሚሉ መላምቶች ተመስርተን እንዲሁም በማንና መቼ እንደተጻፈ ስምምነትና ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት የሉቃስ ወንጌል የአምላክ ቃል ነው፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ጻፈ” ወዘተ. ብለን በድፍረት መከራከር ከቶ እንደምን ይቻላል?

እነዚህን አስተያየቶች ከመጥቀሳቸው በፊት ጠያቂው ሉቃስ ስለ ወንጌሉ በመግቢያው ላይ የጻፈውን በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፡-

የሉቃስ ወንጌል 1፡1-4 “በእኛ መካከል ስለ ተፈፀሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸው ያህል ጽፈውት ይገኛል ፤ ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንስቶ የዐይን ምስክሮች የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላልፉልን ነው፡፡ ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ! እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ ፤ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ ፤ ይህንንም የማደርገው የተማርከው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው” ይላል፡፡ ታድያ ሉቃስ መቼ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ጻፈ? እዚህ ላይ “ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል” ይላል፡፡ ይህ የሚያሳየን የቻሉትን ያህል መጻፋቸውን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ያስጻፋቸውን ያህል እንዳልጻፉ ነው፡፡ ከችሎታቸው ጋር ነው የተያያዘው፡፡ ሉቃስ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቼ ጻፍኩ መቼ አለ? በጥንቃቄ እኔው ጻፍኩ ነው ያለው፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ምን ነካቸው?

ጠያቂው ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት መገለጥ ያላቸው ግንዛቤ እስላማዊ በመሆኑ ይህንኑ አመለካከታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ሙስሊሞች ቁርኣን “የተገለጠበትን” ሁኔታ ታንዚል ወይም ናዚል በማለት ይጠሩታል፡፡ ታንዚል ማለት “ከላይ የወረደ መገለጥ” ማለት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረው ክርስቲያናዊ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የወረደ መገለጥ ነው የሚል ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት (በመመራት) የጻፉት ቃል ነው የሚል ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የነበራቸውን እውቀት፣ ባህል እና ቋንቋ እንዲጠቀሙ መንፈስ ቅዱስ ፈቅዷል፡፡ ጸሐፊያኑ “የመንፈስ ቅዱስ የትየባ ማሽኖች” ስላልነበሩ ሲጽፉ በችሎታቸው መጠን እንጂ ከችሎታቸው በላይ እንዲጽፉ አልተደረጉም፡፡ አቅማቸውና ነባራዊ ሁኔታዎች በፈቀዱላቸው መጠን ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን መልዕክቱ የእግዚአብሔር ስለሆነ በሰዎቹ አቅምና በነበረው ሁኔታ ሳይገደብ ለትውልዶች ብርሃን መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ሉቃስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንደጻፈ ባይናገርም ነገር ግን  የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ጽሑፉን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመቀበል መስክረውለታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ የጻፈውንና ሉቃስ የጻፈውን አንድ ላይ አጣምሮ በማስቀመጥ ሁለቱም መጻሕፍት እኩል ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውን አረጋግጧል!

“መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና፡፡” 1ጢሞቴዎስ 5፡18፡፡

“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚለው ዘዳግም 25፡4 ላይ የሚገኝ ሲሆን “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” የሚለው ደግሞ ሉቃስ 10፡7 ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን የሐዋርያት ዘመን ከማለፉ በፊት ቢያንስ የሉቃስ ወንጌል ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ነው፡፡ ሐዋርያው እንደ ዘዳግም ሁሉ የሉቃስ ወንጌልን በስም አለመጥቀሱ በወቅቱ የሉቃስ ወንጌል በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ መካከል በሚገባ የሚታወቅ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የሉቃስ ወንጌል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ አረጋግጧል ማለት ነው![1]

የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ውጭያዊና ውስጣዊ መረጃዎችን ይጠቀማሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ሁለተኛ ክፍል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ዝርዝር ታሪካዊ ክስተቶችን በማካተቱ ምክንያት መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ ለዘብተኛ እንዲሁም አጥባቂ ከሆኑት ሊቃውንት መካከል የሚበዙቱ የሐዋርያት ሥራ ከ63 ዓ.ም. በፊት የተጻፈ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ኮሊን ሐመር የተሰኙ የሮም ታሪክ ሊቅ የሐዋርያት ሥራ በ61 እና 62 ዓ.ም መካከል የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ 17 ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡[2] ወንጌሉ ደግሞ ቀደም ሲል የተጻፈ በመሆኑ (ሉቃስ 1፡1 እና የሐዋርያት ሥራ 1፡1 ያነፃፅሩ) ቢያንስ ከ61 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፈ መናገር ይቻላል፡፡ ጠያቂው የዘነጉት ትልቁ ቁምነገር የሊቃውንት ዋና ትኩረት ወንጌሉ በተጻፈበት ቁርጥ ባለ ጊዜ ላይ ሳይሆን የተጻፈበት ዘመን (Era) ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ሐዋርያት እና የመስቀሉ ትውልድ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ከተጻፈ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ለማወቅ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑ ስለሚረጋገጥ ለተዓማኒነቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡

የሉቃስን ማንነት በተመለከተ በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ ከአዲስ ኪዳን ውጪ መረጃዎችን እናገኛለን፡፡ ሊቃውንት በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መገባደኛ አካባቢ እንደተጻፈ የተናገሩለት አንድ ምንጭ የሉቃስ የትውልድ ከተማ አንፆኪያ መሆኗን ይናገራል፡፡[3] የሐዋርያው ጳውሎስ ወዳጅ እና በሙያው ኀኪም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ፊልሞና 1፡24፣ ቆላስይስ 4፡14)፡፡ “እኛ” (We Sections) ተብለው የሚታወቁት የሐዋርያት ሥራ ክፍሎች ሉቃስ በፊልጵስዩስ ከተማ ይኖር እንደነበር፣ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱንና ወደ ሮም አብሮት መጓዙን ያስረዳሉ (16፡10-17፣ 2O፡5-I5፣ 21፡1-18፣ 27፡1-28፡16)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 4፡10-14 ላይ አርስጦኮስ፣ ዮስጦስ እና ማርቆስ “ከተገረዙት ወገን” አብረውት የሚያገለግሉ ብቸኛ ወንድሞች መሆናቸውን ከገለፀ በኋላ ኤጳፍራ፣ ሉቃስና ዴማስን መጥቀሱ ሉቃስ አይሁዳዊ ላለመሆኑ እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡ አሁን በእጃችን የሚገኘው ቀዳሚ የሆነው የሉቃስ ወንጌል የእጅ ጽሑፍ (180-200 ዓ.ም.)[4] የሉቃስን ስም ይዟል፡፡ “የሙራቶራውያን ቀኖና” በመባል የሚታወቀው በ170 ዓ.ም. አካባቢ የተጻፈው ጽሑፍ እና የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው የኤሬኔዎስ ጽሑፍ (180 ዓ.ም.) የወንጌሉ ጸሐፊ ሉቃስ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡[5] ቀዳሚያን ሰነዶች የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ሉቃስ መሆኑን ቢያረጋግጡም ከ100 ዓመታት ወዲህ ግን አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን እየፈጠሩ የወንጌሉ ጸሐፊ በመሆኑ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚገልፁ የተወሰኑ ለዘብተኛ ምሑራን ተፈጥረዋል፡፡ በዚህች ምድር ላይ ምሑራን የማያቀነቅኑት መላምት የለም፡፡ በተለይ መንፈሳዊ መጻሕፍትን በተመለከተ የትኛውንም አማራጭ አመለካከቶች የሚደግፉ ለዘብተኛ ሊቃውንትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አመለካከቶቹ ትክክል መሆናቸውን ቀዳሚ የታሪክ ሰነዶችን በመጥቀስ ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ ማስረጃ አልባ አመለካከቶችን ማራገብ ርቱዕ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡

ሰር ዊልያም ራምሰይ የተባሉ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሑር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተዓማኒነት እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ የሉቃስ ጽሑፍ የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥራ እንደሆነ አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን እኚህ ምሑር በትንሹ ኢስያ (Asia Minor) ውስጥ የተለያዩ የሥነ ቁፋሮ ግኝቶችን ሲመረምሩ ሳሉ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የትየለሌ ማስረጃዎችን አገኙ፡፡ እኚህ ምሑር ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት (ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን) መሆኑን ብቻ ሳይሆን ሉቃስ ከታላላቅ  የታሪክ ጸሐፊዎች መካከል መመደብ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡[6]