መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል ልዩነት መኖሩን አንዱ ጥቅስ በሌላኛው መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖሩ ምንን ያሳየናል?

 


8. የመጽሐፍ ቅዱስ ግርጌ ልብ ብለን ብናይ (በተለይ የ1980 ውን የቀላል ትርጉም እትም) በተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል ልዩነት መኖሩን አንዱ ጥቅስ በሌላኛው መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖሩን፣ በጥንት ቅጅ ያለው ከዚህኛው እንደሚለይ፣ ተጨማሪ ቃል፣ ሀረግ፣ ዓረፍተ ነገር እንዳለው አልያም እንደተጨማረ በብዛት ይገልጻል፡፡ ይህ ምንን ያሳየናል? በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ልዩነት፣ ቅራኔ እና ግጭት መኖሩን አያሳይምን? ታዲያ ይህ ሁሉ እያለ ክርስቲያኖች እንዴት በየዋህነት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅና ይቆማሉ?

በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት በጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ወቅት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየር እና የመሳሰሉት ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የኃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ስልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉ ጥንታዊ መዛግብ ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ከተባሉት የግልበጣ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ ካለመሆናቸው የተነሳ ሊተረጎሙ እንኳ የማይችሉ ናቸው፡፡ የከፉ የሚባሉቱ ደግሞ እንደ ስም እና ቁጥር ስህተቶች ያሉ ዋናውን መልዕክት ሊነኩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቀድሞ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1954 እትም) 2ነገሥት 8፡26 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ እድሜው 22 ዓመት እንደነበር ሲገልፅ 2ዜና 22፡2 ግን 42 ዓመቱ እንደነበር ይናገራል፡፡ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎችን ስንመለከት የእብራይስጡ 42 ሲል የሱርስት እና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች 22 እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጥንታውያን መዛግብት ምሑራን ትክክለኛው 22 እንደሆነና 42 የሚለው የግልበጣ ስህተት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (አዲሱ መደበኛ ትርጉም 2ዜና 22፡2 የግርጌ ማስታወሻ ይመልከቱ)፡፡ እንደነዚህ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ተዓማኒነት እንደሚጎለው አይታሰብም፡፡ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ምሑራን እነዚህን ችግሮች እንደ አሳሳቢ ችግሮች አይቆጥሯቸውም ነገር ግን ስለጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ወገኖች ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ እንዳልሆነ ለማሳየት የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ የሚገኙ ተቃዋሚዎች የሚነዙት የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ ሲታከልበት ደግሞ ውዥንብሩ ይብሳል፡፡ ዶ/ር ባርት አህርማንን (Bart Ehrman) የመሳሰሉ ለክርስትና ጥላቻ ያላቸው ምሑራን በጥንታዊ መዛግብት ጥናት ዘርፍ ያላቸውን እውቅናና የሚድያ ሽፋን በመጠቀም ለገንዘብ ትርፍ በማሰብ ይህንን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲያውሉት እና የዋሁን ሕዝብ ሲያወናብዱ ይታያሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖች ደግሞ ፕሮፓጋንዳውን ከነብጉሩ በመቅዳት ያስተላልፉታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ለሚሰሟቸው ሰዎች የማይነግሩት አንድ እውነታ ቢኖር የእነርሱ መጽሐፍ የከፋ ችግር እንዳለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነውን ቁርኣንን ብንወስድ የመጀመርያዎቹ ቅጂዎች ብዙ መለያየቶችና ግጭቶች ስለነበሩባቸው ዑስማን የተባሉ ኻሊፋ (የሙስሊሞች መሪ) በአራት ሊቃውንት አማካይነት እርማት ተደርጎ አንድ መደበኛ ቅጂ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ የበፊቶቹ ቅጂዎች እንዲቃጠሉ እንዳደረጉ በጥንታውያን የእስልምና የታሪክ መዛግብት ውስጥ ተጽፎ የተቀመጠ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ጥንታውያን ቅጂዎቹ በመቃጠላቸው ምክንያት ሙስሊም ወገኖች አሁን ያሉት ቁርአኖች ከቀዳሚያን ጽሑፎች ጋር አንድ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡ እነዚያን ቀዳሚያን ጽሑፎች የሚያውቁ ሙስሊሞች ጥለዋቸው ያለፏቸው ሰነዶች እንደሚያመለክቱት አሁን ባሉትና በቀደምት ቁርአኖች መካከል የሚገኙት ልዩነቶች በእጅጉ አስደንጋጭ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ የተለያዩ አሁን ያሉትን ቁርአኖች ያስገኙ የእጅ ጽሑፎች ብዙ የግልበጣ ስህተቶችና እርማቶች እንዳሏቸው ታውቋል፡፡[29] (በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ የምንለው ይኖረናል፡፡)

ነገር ግን የጥንት ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን እንኳንስ ሊያቃጥሉ ይቅርና ሊያቃጥሏቸው ለሚፈልጉ ሰዎች አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ሞትን በመምረጥ ብዙዎቹ ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ክርስቲያን አባቶች ጥንታዊያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች የግልበጣ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም እንኳ ከማቃጠል ይልቅ በክብር ያስቀምጧቸው ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ትክክለኛውን አነባበብ በመመርመር ማወቅ እንድንችል ረድቶናል፡፡ ስለ ቁርኣን የግልበጣ ስህተቶች ያነሳንበት ምክንያት ሙስሊም ወገኖቻችንን ለማስከፋት ወይንም ደግሞ ኃይማኖታቸውን ለመንቀፍ ፈልገን አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ጸሐፊያኖቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚጠቅሷቸው አንዳንድ ችግሮች በከፋ ሁኔታ በቁርኣን ላይ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን እንዲያውቁና ሁለቱንም መጻሕፍት በአንድ ሚዛን መመዘን እንዲጀምሩ ለማሳሰብ ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የግልበጣ ስህተቶች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎችን ጎን ለጎን በማስተያየት ትክክለኛዎቹ ምንባቦቻቸው ሊታወቁ የሚችሉ ናቸው፡፡ በሊቃውንት እጅ የሚገኙት አብዛኞቹ ብራናዎች በስደት ዘመን የተገለበጡ በመሆናቸው ጸሐፍቱ ሌሊት መብራቶችን በመጠቀም ወይም ዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ ነበር ሲገለብጡ የነበሩት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጸሐፍት በአንድ ክፍል ውስጥ ይሰበሰቡና አንድ አንባቢ ከፊት ሆኖ እያነበበላቸው ይገለብጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ስህተቶች የመፈጠራቸው ሁኔታ ይሰፋል፡፡ ነገር ግን ነባር ሊቃውንት በዚህ ሁኔታ ችግር እንዳለበት ያረጋገጡት የአዲስ ኪዳን ክፍል ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው፡፡ 98.33 ከመቶ የሚሆነው የአዲስ ኪዳን ክፍል ከመሰል ችግሮች የፀዳ ነው፡፡ ብሩስ መዝገር የተሰኙ ዕውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ሕየሳ (Textual Criticism) ሊቅ አዲስ ኪዳን 99.5 ከመቶ የተጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ ጽፈዋል፡፡[30]  ከእነዚህ በጣት ከሚቆጠሩት ችግሮች መካከል ዋናውን የእምነት መሠረት የሚነካ አንድም እንኳ የሌለ ሲሆን የምንባቡን ትርጉም ሊለውጡ የሚችሉትን ልዩነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻዎች በማስቀመጥ አንባቢያን እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ ቁርኣንን ጨምሮ ከጥንት ሰነዶች መካከል በዚህ የጥራት ደረጃ የተጠበቀ መሆኑ የተረጋገጠ አንድም ጽሑፍ የለም! (በእርግጥ ቁርኣን ከ600 ዓ.ም. ወዲህ ስለተጻፈ በሊቃውንት ዘንድ እንደ ጥንታዊ ሰነድ አይቆጠርም፡፡) የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት በነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተጠበቀ በመሆኑ በእውነቱ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊያሳስቡን የሚገቡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር መርጧል፡፡

በሙስሊም ሊቃውንትና በክርስቲያን ሊቃውንት መካከል ያለው ልዩነት ክርስቲያን ሊቃውንት እነዚህን የተለያዩ ምንባቦች በታማኝነት ይፋ በማድረግ እያንዳንዱ ምዕመን እንዲያውቅ የሚያደርጉ ሲሆኑ ሙስሊሞቹ ግን መሰል ልዩነቶች እንዳይታወቁ መሸሸጋቸው ነው፡፡ የቁርኣንን የእጅ ጽሑፎች ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ለማጥናት የሞከሩ ሊቃውንት ተገድለዋል፡፡[31] አንዳንድ የቁርኣን ተርጓሚዎች እነዚህን ልዩነቶች ይፋ ለማድረግ የደፈሩ ሲሆን ዶ/ር ረሻድ ኸሊፋ የተሰኘው ተርጓሚ አንድ የቁርኣን ጥቅስ ጭማሬ መሆኑን በመግለፅ ከትርጉሙ ውስጥ እንዲወጣ በማድረጉ ምክንያት ተገድሏል፡፡[32] “አትላንቲክ መንዝሊ” የተሰኘ መጽሔት የቁርኣንን በትክክል ተጠብቆ መቆየት የሚገመግም ጽሑፍ ይዞ በመውጣቱ ምክንያት በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡[33] ሙስሊም ወገኖች ስለ ቁርኣን በትክክል ተጠብቆ መቆየት የሚናገሩት ንግግር ሁሉ ትክክለኛ ምሑራዊ ጥናት በማድረግ ላይ ያልተመሠረተና ከባዶ መፈክር ያላለፈ ነው፡፡