ጳውሎስ “የእኔ ወንጌል ይኸው ነው” ሲል እርሱም ወንጌል አለው እንዴ? የሌሎቹ ወንጌልስ?

 


14. ጳውሎስ በ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡8 ላይ “ከሙታን የተነሳውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፣ የእኔም ወንጌል ይሄው ነው” ብሏል፡፡ ጳውሎስ “የእኔ ወንጌል ይኸው ነው፡፡” ሲል እርሱም ወንጌል አለው እንዴ? የሌሎቹ ወንጌልስ? እንዲሁ ጳውሎስ “በክርስቶስ ፀጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፡፡” (ገላትያ 1፡16) ብሏል፡፡ ጳውሎስ ይህንን ሲናገር ዛሬ የምናውቃቸው አራቱም “ወንጌላት” (የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌላት) አንዳቸውም አልተጻፉም ነበር፡፡ ይህንን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም ሆነ ስለ መጽሐፎቹ አጻጻፍ ቅድመ ተከተል ከሚገለፁ መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ ታድያ ጳውሎስ “የእኔ ወንጌል” እና “ወደ ተለየ ወንጌል” ሲል የጠራቸው ወንጌላት የትኞቹ ናቸው?

ሐዋርያው በአሕዛብ መካከል ስለሚሰብከው ወንጌል እንጂ ስለ ተጻፈ መጽሐፍ እየተናገረ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በአሕዛብ መካከል፤ ጴጥሮስ ደግሞ በአይሁድ መካከል የሚደረጉትን ስብከተ ወንጌል እንዲመሩ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ካረጋገጡ በኋላ ወደየ አገልግሎታቸው እንደተሰማሩ ተጽፏል (ገላቲያ 2፡7-9)፡፡ ሐዋርያው በአሕዛብ መካከል የሚሰብከውን የወንጌል መልዕክት ነው “የእኔ ወንጌል” በማለት የጠራው፡፡ “የተለየ ወንጌል” በማለት የጠራው ደግሞ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደሚድኑ የሚናገረውን የፀጋ ወንጌል የሚፃረረውን “መዳን በመገረዝና ሕግን በመጠበቅ ነው” የሚለውን ሰው ሰራሽ “ወንጌል” ነው፡፡ አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች ይህንን የተለየ “ወንጌል” ይሰብኩ ስለነበር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱ ጋር ክርክር ከገጠሙ በኋላ ለመጀመርያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ መጠራት ምክንያት ሆኖ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 15)፡፡