መንፈስ ቅዱስ ነድቶ የወንጌል ጸሐፊዎች እንዲጽፉ ካደረገ ለምን አራት ጊዜ ስለ አንድ ታሪክ መጻፍ አስፈለገ?

 


18. እውን መንፈስ ቅዱስ ነድቶ የወንጌል ጸሐፊዎች እንዲጽፉ ካደረገ ለምን አራት ጊዜ ስለ አንድ ታሪክ መጻፍ አስፈለገ? አንዱ የረሳውን ሌላኛው እንዲሞላው? ወይስ ወንጌሎች ሲጋጩ እንድናነብ ፈልጎ ይሆን?

አራቱም ወንጌላት የየራሳቸው ዓላማ አላቸው፡፡ ማቴዎስ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ መሆኑን ያስረዳል፣ ማርቆስ ኢየሱስ አገልጋይና ተዓምር አድራጊ መሆኑን ያስረዳል፣ ሉቃስ ኢየሱስ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ መሆኑን ያስረዳል፤ ዮሐንስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ማቴዎስ አይሁድን፣ ማርቆስ ሮማውያንን፣ ሉቃስ አሕዛብን፣ ዮሐንስ ደግሞ የሰው ልጆችን በሙሉ ታሳቢ በማድረግ የተጻፉ ናቸው፡፡ ጠያቂው ይህንን ጥያቄ የጠየቁት በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ለማላገጥ እንጂ ለማስተማር እንዳልሆነ የመጨረሻው አባባላቸው ግልፅ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን የገዛ ቁርአናቸው አንድን ታሪክ እጅግ አሰልቺና እርስ በርሱ በሚጣረስ መልኩ መደጋገሙ ለምን እንደሆነ ብንጠይቃቸው መልሳቸው ምን ይሆን? ለምሳሌ ያህል ሱራ 2፡58-59 እና 7፡161-162፤ 27፡7፣ 20፡9-24 እና 28፡29፤ 20፡22 እና 28፡32፤ 7፡123፣ 20፡71 እና 26፡49፤ 2፡35 እና 7፡19፤ 20፡38-40 እና 28፡7-13፤ 7፡12-18፤ 15፡32-42፤ 17፡61-65፤ 38፡75-85 ያነፃፅሩ፡፡ ስለ ወንጌላት “ግጭት” ሊነግሩን የሚዳዳቸው ጠያቂው መጽሐፍ ቅዱስን ለመመዘን የሚጠቀሙትን ተመሳሳይ መስፈርት ቁርኣንን ለመመዘን የሚጠቀሙ ከሆነ እነዚህን አልተገናኝቶ ምንባቦች እንዴት ያስታርቋቸው ይሆን?