“አጭሩ” ና “ረጅሙ” የሚባሉ የማርቆስ ወንጌሎች እንዳሉ ያውቃሉን?

 


26. “አጭሩ” ና “ረጅሙ” የሚባሉ የማርቆስ ወንጌሎች እንዳሉ ያውቃሉን? አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች የማርቆስ ወንጌልን በ16፡8 ሲያቆሙ ረጅሙ ደግሞ በ16፡20 ይጠቃለላል ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? እንዴት ተለያዩ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ማርቆስ 16፡9-20 ድረስ የሚገኘውን ክፍል ተዓማኒነት በተመለከተ ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ ገሚሶቹ በአብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ስለተካተተ ተዓማኒ እንደሆነ ሲናገሩ የተቀሩት ደግሞ ይህንን ክፍል ላለመቀበል ተከታዮቹን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-

  • እነዚህ ቁጥሮች ቀዳሚና ይበልጥ ተዓማኒ በሆኑት የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡ በተጨማሪም በቀደመው ላቲን፣ ሢርያክ፣ አርመንያ እና ኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡
  • ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን እና ኢዮስቢዮስን የመሳሰሉት ብዙ የጥንት አባቶች እነዚህን ቁጥሮች አያውቋቸውም፡፡ ጀሮም ከሞላ ጎደል በእርሱ ዘመን በነበሩት በሁሉም የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
  • ይህንን ክፍል የሚያጠቃልሉት ብዙ የእጅ ጽሑፎች አጠራጣሪ መሆኑን ለማሳየት ምልክት ያደርጉበታል፡፡
  • በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ አጠር ያለ የማርቆስ ወንጌል መዝጊያ ይገኛል፡፡
  • አንዳንዶች ደግሞ አጻጻፉና የሰዋሰው ይዘቱ ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ጋር እንደማይመሳሰል ይናገራሉ፡፡

ይህ ክፍል በኦሪጅናል የማርቆስ ወንጌል ውስጥ መገኘት አለመገኘቱ አጠያያቂ እንደሆነ ቢቀጥልም ነገር ግን የያዘው እውነት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢወጣ ምንም የሚጎድል ትምህርት የለም፡፡ ያዘለው ትምህርት በሌሎች ክፍሎች እንደመገኘቱ መጠን ደግሞ ባለበት ቦታ ቢቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት በልሳን የመናገር ስጦታ፣ የጥምቀት ሥርዓት እና በእባብ መርዝ ያለመጎዳት ተዓምር በሌሎች ክፍሎች ላይ ተጠቅሰዋል (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-21፣ 10፡44-48፣ 19፡1-7፣ 28፡3-5)፡፡[40]