ሁለቱም ወይንስ አንዱ?
ጥያቄው፦
ወንጌላት እንደሚነግሩን ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎች አብረው ታስረው ነበር። ታዲያ በአየሱስ ያሾፉት ሁለቱም ነበሩ? ወይንስ አንዱ? «አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር።» (ማር 15፡32) በዚህ አንቀጽ እንደተገለጸው ከርሱ ጋር ተሰቀሉ የተባሉት ሁለቱ ወንበዴዎች ይነቅፉት እንደነበር ነው። በሌላ ቦታ ግን እንዲህ ይላል፡- «ኢየሱስንም፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው።ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።» (ሉቃ 23፡42-43) በመጀመሪያው አንቀጽ ይነቅፉት ነበር በሚል ሁለቱንም ሲገልጽ በሉቃስ ወንጌል ግን ይነቅፈው የነበረ እንዱ ብቻ እንደነበር ተጠቅሷል።
መልስ፦
ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉ ወንበዴዎች ተሳለቁበት ማርቆስ 15፡32 ሁለቱም አደረጉ ይላል። ሉቃስ ግን 23፡43 አንዱ ተሳለቀበት አንዱም ኢየሱስን ተከላከለ ይላል። ይህ ግልጽ የሆነ ተቃርኖ ቢመስልም ነገር ግን ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ሉቃስ 23፡43 እዚህ ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማየት በጣም ግልጽ የሆነ መደምደሚያ ሰጥተዋል፦
ሁለቱም ወንበዴዎች መጀመሪያ ላይ ኢየሱስን ያፌዙበት ነበር፥ ነገር ግን ኢየሱስ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ካለ በኋላ ከዘራፊዎቹ አንዱ ልቡን ቀይሮ በመስቀል ላይ ንስሐ የገባ(ካደረገው እና ከተናገረው ነገር የተቆጨ) ይመስላል፣ ሌላኛው ደግሞ መሳለቁን ቀጠለ ማለት ነው።
እዚህ ላይ ሊታለፍ የማይገባው ትምህርት አለ። ምንም ዓይነት ወንጀል ወይም ኃጢአት ብንሠራ ጌታ በማንኛውም ጊዜ ንስሐ እንድንገባ እንደሚፈቅድልን፥ እነዚህ ሁለት ሌቦች የሁላችንም ምልክት ናቸው። አንዳንዶቻችን የክርስቶስን እውነታ ስንጋፈጥ እሱን መካድ እና መሳለቂያ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፣ ሌሎች ደግሞ ኃጢአታችንን ተቀብለን ይቅር በለን በማለት እንጠይቃለን። መልካሙ ዜና በመስቀል ላይ እንዳለ ሌባ በማንኛውም ጊዜ ከዚህ ኃጢአት ነፃ ልንወጣ እንችላለን በፊታችን ሞትን እያየን’ እንኳን። ከመጽሐፉ ጥልቅ ነገር የምናየው ይሄን ነው ሁለቱም የመጽሐፍ ክፍል ተመጋጋቢ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም።
