ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት የፈወሳት ለምጻሙን ከፈወሰ በኋላ ነው ወይንስ በፊት?

 


ጥያቄው

«ኢየሱስም ለመቶ አለቃ ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።» (ማቴ 8፡13-15) በዚህ አንቀጽ ስንመለከት ኢየሱስ ለምጻሙን ከፈወሰ በኋላ (ሙሉውን ታሪኩን ማቴወስ 8፡1 ጀምሮ ማየት ይቻላል) ወደ ጴጥሮስ አማት በመግባት እንደፈወሳት ነው። ነገር ግን በሌላ ቦታ፡- «የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው።» (ማር 1፡30-31) ሙሉ ታሪኩ እስከ 41 ድረስ መመልከት ይቻላል። በተጨማሪም ሉቃስ 4፡38-5፡13 ያገኙታል። በዚህ አንቀጽ ደግሞ የሚነግረን ደግሞ ኢየሱስ ለምጻሙን ከመፈወሱ በፊት የጴጥሮስን አማት አንደፈወሳትና ከዚያ በኋላ ለምጻሙን አንደፈወሰው ነው።

መልስ

እንደዚህ አይነቱ ጥያቄ የጥንቱን የታሪክ አዘጋገብ ስልት ካለመረዳት የሚነሳ ነው። በጥንት ጊዜ ታሪክ ዘጋቢዎች ስለ አንድ ክስተት ሲዘግቡ ከቅደም ተከተሉ ይልቅ ባለታሪኩ በሰራቸው ስራዎች ላይ ያተኩራሉ። በሶስቱም ዘገባዎች ላይ የስምኦን አማትና ለምጻሙ ሰው በተቀራራቢ ጊዜ መፈወሳቸው በግልጽ ተቀምጧል። ስለዚህም በጥንታውያኑ የታሪክ አዘጋገብ መሰረት ታሪኮቹ ትክክለኛና ህጸጽ አልባ ናቸው። አሁንም ጠያቂያችን ቆም ብለው አውደ ምንባቡን ቢመለከቱ እንላለን። በጥቅሶቹም ላይ ግልፅ ግጭት የለም።