ሰው የኾነው አምላክ
የክርስቶስ መለኮትነትና ቅድመ ህልውና በፊልጵስዩስ 2፥5-11
ወንድም ሚናስ
ስለ ክርስቶስ መለኮትነትና ቅድመ ህልውና ከተነሣ፣ ፊልጵስዩስ 2፥6-11 ለርእሰ ጒዳዩ ትክክለኛ መልስ የሚሰጥ የዐዲስ ኪዳን ምንባብ መኾኑ አያጠያይቅም። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትሥጉትነቱ በፊት ከአባቱ ጋር በእኵልነት ይኖር የነበረ፣ ለያህዌ ብቻ የሚገባውን አምልኮ የሚቀበል ጌታ መኾኑን በግልጽ ያመለክተናል። እኛም በዚህ ዐጭር መጣጥፍ ይህንን መለኮታዊ ምንባብ ለማብራራት እንሞክራለን፤ ክፍለ ምንባቡንም አስመልክቶ በፀረ ለሥላሴአውያን የሚነሡ ሙግቶችንም በጥቂቱ የምንዳሥሥ ይኾናል።
“ትሑት መኾን”
መጽሐፍ ቅዱስ አማኒያን ገንዘባቸው ያደርጉት ዘንድ ከሚያሳስባቸው ምግባራት አንዱና ዋናው ትሕትና ነው፤ እግዚአብሔር ለትሑታን ጸጋን እንደሚሰጥ ትምክህተኞችን እንደሚያዋርድ በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲኾን(ምሳሌ 3፥34 1ኛ ጴጥ 5፥5፤ ያዕ. 4፥6)፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ለማግኘት ትሕትና ሁነኛው ስንቅ እንደኾነ ቃለ እግዚአብሔር ደጋግሞ ያሳስበናል፤ በተጨማሪም ቅዱሳት መጻሕፍት ትሕትና ላይ ልዩ ትኵረት ሰጥተው የመግለጻቸው ምክንያት፣ ትሕትና ከአማኒያን ጋር ኅብረት የምንፈጥርበት ትልቅ መሣሪያ ስለኾነም ጭምር ነው፤ ለዚህም ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ፣ ክርስቲያኖች አንድነት ይኖራቸው ዘንድ በሚያሳስብበት ምንባብ፣ ትሕትና ኅብረት የሚፈጥሩበት ቍልፍ ምግባር መኾኑን፣ እንዲህ ሲል ይጽፍላቸዋል፦
“ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቊጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችኹ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችኹን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ ።[ፊል. 2:3 ዐ.መ.ት]”
ሐዋርያው ጳውሎስ ትሕትና ማለት የራስን ጥቅም ለሌሎች አሳልፎ መስጠት መኾኑን ይናገራል፤ ኾኖም ምዕመናን የራሳቸውን ጥቅም ስለ ሌሎች ጥቅም አሳልፎ መስጠት የማይቻል አድርገው እንዳይረዱት፣ በአማኒያኑ ዘንድ የእምነታቸውን ማዕከል የኾነውን፣ ታላቁን የሥነምግባር ጥግ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምሳሌነት ያቀርባል፤ ይኸውም እርሱ ቅድመ ዓለም ከአባቱ ጋር የነበረ ቢኾንም[1] የአባቱን ዐላማ ለመፈጸም በፈቃዱ ሰው መኾኑንና ፣ “ይህ ክርስቶስ ውስጥ የነበረው ሐሳብ በእነርሱ ውስጥም ይኖር ዘንድ” እንዲህ ሲል ይጽፍላቸዋል፦
“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይኹን፤ ርሱ በባሕርዩ አምላክ ኾኖ ሳለ፣ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ኾኖ ተገልጦም፣ራሱን ዝቅ አደረገ፤እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ድረስ ታዛዥ ኾነ” (ፊል.2፥5-8 ዐ.መ.ት)
ከላይ ሰፍሮ በሚገኘው መልእክት ውስጥ ብዙ ዐሳቦች ሊዳሡሡ፣ ሊቃኙ የሚችሉ ቢኾንም፣ በዚህ መጣጥፍ የተወሰኑትን ብቻ በጥቂቱ የምንመለከት ይኾናል።
“በእግዚአብሔር መልክ”
“መልክ” (ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለው ቃል ጠቅለል ባለ አገላለጽ፣ “መታየት” “መገለጥ”የሚል ፍቺ ይኖረዋል[2]፤ በማርቆስ 16፥12 ላይ ጌታችን ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡን በሚተርክበት ምንባብ፣ “በሌላ መልክ ታያቸው” በሚለው ክፍል ላይ “ታያቸው” ለሚለው የተጠቀመው፣ ይህንን የጽርእ ቃል ነው፤ ስለዚህ “መልክ”(ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) ማለት፣ “መታየት”፣ “መገለጥ” የሚል ፍቺ ካለው፣ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር መልክ መታየቱ” ወይም “በእግዚአብሔር መልክ መገለጡ” ከምን አንጻር ልንመለከተው ልንረዳው ይገባዋል በሚለው ጒዳይ፣ የዐዲስ ኪዳን ምሁራን ቃሉን በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲሁም ለዘመኑ በቀረቡ የጽርእ መዛግብ ቃሉን በምን አግባብ ይጠቀሙት እንደነበር መመልከት ተገቢነት እንዳለው ይናገራሉ፤ ይህንንም በምንመለከትበት ጊዜ፣ “መታየት” ፣ “መገለጥ” ከ “ክብር” ጋር በተቈራኘ መልኩ እንደተገለጸ እንመለከታለን፤ ለምሳሌ ሕዝቅኤል ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅን “ተገልጦ” በተመለከተ ጊዜ፣ መታየቱን ወይም መገለጡን “የእግዚአብሔር ክብር” በሚል ሐረግ ጠቅለል አድርጐ ሲገልጸው እናነባለን (ሕዝ. 1፥26-28)፤ እንዲሁም በመጽሐፈ ሔኖክ ላይ ባለራእዩ ፣ በሰማያዊ ዙፋን የተቀመጠውን “መልክ (figure)”፣ “ታላቁ ክብር” ሲለው እናነባለን፤ ስለዚህ “መታየት” “መገለጥ” የሚለው ቃል ከክብር ጋር የተያያዘ አንድምታ ባለበት፣ በአይሁድ ማኅብረሰብ ላደገ እንደ ጳውሎስ ላለ ሰው፣ “በእግዚአብሔር መልክ” ማለት “በእግዚአብሔር ክብር” የሚል ሐሳብ እንዳለው ግልጽ ሲኾን፣ ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመኾኑ በፊት የነበረውን ቦታ የሚያስታውስ ነው።
ጥንታዊ የጽርእ ጽሑፎችንም ያየን እንደኾን፣ “መልክ”(ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለውን ቃል ከመለኮታዊ ክብር ጋር በተገናኘ ኹኔታ ሲጠቀሙት ይስተዋላል፤ ፊሎ ዘእስክንድርያ የተባለ ፈላስፋን ብንወስድ፣ እግዚአብሔር ለሊቀ ነብያት ሙሴ በነደ እሳት (burning bush) ውስጥ ያናገረበትን መንገድ በሚተርክበት ጊዜ “መልክ” (ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለውን ቃል፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጽ ተጠቅሞታል[3] በተመሳሳይ ዮስጢኖስ ሰማዕትም (Justin the Martyr) “መልክ” (ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር ክብር ጋር አያይዞ ይጠቅመዋል[4]። ስለዚህ በአጠቃላይ (1ኛ.) “መልክ”(ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) “መገለጥ”፣ “መታየት” የሚል ትርጒም አለው (2ኛ.) የእግዚአብሔር “መገለጥ” “መታየት” ከክብሩ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። (3ኛ.) ስለዚህም “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር” የሚለው ሐረግ “በእግዚአብሔር ክብር ሲኖር” ተብሎ ሊታይ ይገባዋል[5]።
ሌላው “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር” የሚለው ገለጻ ለፊልጵስዩስ አማኒያን ትልቅ አንድምታ ያለው ነገር ነው፤ በፊልጵስዩስ ማኅበረሰብ ዘንድ፣ አንድ ግለሰብ የሚታይበት መንገድ፣ ከደረጃው (status) ወይም ከማንነቱ ጋር የተቈራኘ ነው[6]፤ ለምሳሌ በዘመኑ የነበሩ የሮም ባለሥልጣናት በልብሳቸው ላይ አድርገው የሚያሳዩት “ላቱስ ክላቩስ” (latus clavus) የሚል ጽሑፍ ነበር፤ ይህም በንጉሡ የተሰጣቸውን የሥልጣን ደረጃ (ርከን) የሚገልጽ ቃል ሲኾን፣ በተመሳሳይ በአገሩ የሚኖሩ ባሮች “ፒሊዮስ” (pillius) የሚል ጽሑፍ የሰፈረበትን ልብስ በመልበስ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ደረጃ ያሳያሉ። ስለዚህ ለጳውሎስም ኾነ፣ ለቀዳማይ ተደራሲያኑ “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ” የሚለው ገለጻ፣ በእግዚአብሔር ደረጃ (status) ሰው ከመኾኑ በፊት የነበረውን ደረጃ የሚገልጽ ነው፤ በርግጥ ታሪካዊ ዳራውም ብቻ ሳይኾን፣ የክፍሉን ዐውድ ያየን እንደኾነ፣ “መልክ” የሚለው ቃል ከደረጃ ጋር የተያያዘ መኾኑን እንረዳለን፤ ይኸውም በቊጥር 7 ላይ “የባሪያ መልክ” የሚለው ሐረግ “በሰው አምሳል ተገኝቶ” በሚል ከማንነት ወይም ከደረጃ ጋር በተዛመደ መልኩ ተገልጾአል፤ በሌላ አገላለጽ ኢየሱስ በሰማያት የነበረውን ያን መለኮታዊ ክብር፣ በመተው ራሱን ዝቅ ማድረጉን የሚያሳይ ነው፣ ይህ ዐይነት አገላለጽ አንድ የሮማ ገዢ የኾነ ንጉሥ፣ ባርነትን ወዶ ሎሌ ኾነ ተብሎ ሊቈጠር የሚችል ነው፤ በቀጣይ ምዕራፍ ላይ ደግሞ ጳውሎስ ራሱን በምሳሌነት፣ እርሱ “ከዕብራዊም ዕብራዊ” ኾኖ ሳለ፣ ይህንን ማንነቱ እንደ “ጒድፍ” በመቊጠር፣ ከክርስቶስ ጋር መከራን መቀበልን መምረጡን በመናገር፣ ራሱን እንደ ተጨማሪ ምሳሌ አድርጐ ያቀርባል፤ በአጠቃላይ “ትሕትና” የመልእክቱ ዋና ነጥብ ሲኾን፣ “ሌሎች ከእነርሱ እንደሚሻሉ በትሕትና እንዲቊጠሩ፣ “በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴን ለማግኘት አንዳች እንዳያደርጉ”(ፊል 2፥3)፣ ራሳቸውን እንደ ተጠቃሚ የሮማዊ ዜጋ ሳይኾን፣ እንደ ሰማያዊ ዜጋ እንዲያስቡ አበክሮ ያሳስባቸዋል(ፊል. 3፥17-21)።
በአጠቃላይ ፊል 2፥6-7 ላይ ያለው ምንባብ ኢየሱስ በባሕርይው ወይም በማንነቱ መለኮት ኾኖ ሳለ፣ ስለ እኛ “የባሪያን መልክ” መላበሱን የሚገልጽ ነው፤ ይህንን ክፍል ከመጠቅለላችን በፊት ግን ጳውሎስ በ ፊልጵስዩስ 2፥6-7 ክርስቶስ “በእግዚአብሔር መልክ (ሞርፌ)” ሲኖር የነበረ ቢኾንም፣ ስለኛ “የባሪያን መልክ (ሞርፌ)” መያዙን የገለጸበት መንገድ በፊልጵስዩስ ኾነ በመላው በሮማን ቅኝ ግዛት በኾኑት ከተሞች ከሚታወቁት አማልክት መኻከል አንዱ የኾነው፣ ዲዮናስዮስ ራሱን በዩሪፒድስ ድርሳን ላይ፣ ከተገለጸበት መንገድ ፍጹም ተመሳሳይ ነው፤ ዩሪፒድስ የዲዮናስዮስን ንግግር “መለኮታዊ መልኬን (ሞርፌ) ወደ ሰው መልክ (ሞርፌ) መቀየሬን…” ብሎ አስፍሮታል[7]። ጳውሎስም ኾነ ዩሪፒድስ ማንነትን ባሕርይን በተመለከተ ኹለቱም “መልክ”(ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለውን ቃል እንደ ተጠቀሙ ልብ ይሏል። የጳውሎስ ተደራሲያን የሚኖሩባት ፊልጵስዩስ አምልኮተ ዲዮናስዮስ እጅግ የተንሰራፋባት ከተማ ከመኾኗ አንጻር፣ የዩሪፒድስ ጽሑፍ በእጅጉ ታዋቂ ሰነድ መኾኑ አያጠያይቅም፤ ስለዚህ የጳውሎስ ተደራሲያን በክርስቶስ ተሠግዎትና አስቀድመው በሚያውቁት የዲዮናስዮስ ሰው ከሚያወሣው አፈታሪክ ጋር የተነጻጸረ መኾኑ አይጠፋቸውም። በሌላ ስፍራ እንደምናነበው [8] ሐዋርያው ማኅበረሰቡ አስቀድሞ በሚያውቀውና ሊረዳው በሚችለው መንገድ የሚፈልገውን ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ ማለት ግን የዲዮናስዮስ ታሪክ ትክክል ነው ብሎ እንደወረደ አልተቀበለም፤ ይልቁንም ጌታችን ኢየሱስ እንደ ዲዮናስዮስ ሰው የሚመስል ሳይኾን፣ ፍጹም ሰው የኾነ መኾኑን በሚገልጽ መልኩ ነው፤ ይኹን እንጂ አስቀድመን እንዳልነው አማኒያኑ አስቀድመው በሚያውቁትና ሊረዱት በሚችሉት መንገድ፣ የክርስቶስን ተሠግዎት አስተምሮአል።
“ሊለቀው እንደማይገባ ነገር አልቈጠረውም”
በፊል 2፥6 ላይ ἁρπαγμὸν “አርፓግሞን” የሚለው ቃል ወደ ዐማርኛ ሲተረጐም፣ “ሊለቀው” (ዐ.መ.ት) “መቀማት” (1954 ትርጒም) “በኀይል እንደ ያዘ” (1997 ትርጒም) ወዘተ. ተብሎ ተተርጒሟል። ፀረ ሥላሴያውን የኾኑ የእምነት ቡድኖችና ግለሰቦች፣ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ለመግለጽ የፈለገው፣ ኢየሱስ አስቀድሞም ከእግዚአብሔር ጋር እኵል ስላልኾነ፣ ይህንን መለኮታዊ ማንነት “ለመቀማት” አልሞከረም የሚል ሙግት ያቀርባሉ[9]፤ ኾኖም ግን ይህ የፀረ ሥላሴውያን ሙግት ቢያንስ በሦስት መሠረታዊ ነጥቦች ውድቅ ይኾናል፦
(1). በጽርእ τό “ቶ” ዕምር የኾነ ርቱዕ ተሳቢ አርእስት፣ አስቀድሞ የተጠቀሰው ሐሳብ የሚሞላ ሲኾን፣ ይኸውም የቃል በቃል ትርጒምን የምንከተል ከኾነ፣ “ከእግዚአብሔር ጋር እኵል መኾኑን” የሚል ይኾናል።
(2). ἁρπαγμός “አርፓግሞስ” የሚለው ቃል አንድ ባለመብት የኾነ አካል፣ መብቱን፣ ዐቅሙን ወይም ኀይሉን ለመጠቀም አለመፈለጉን የሚያሳዩ ብዙ የጽርእ ድርሳናት አሉ፤ ለምሳሌ አንድ ጸሓፊ አንድ ልዑል በርሱ ደረጃ ያለችን ልዕልት፣ መብቱን በመጠቀም ልጅቱን የግሉ ባለማድረጉ፣ እንዲህ ሲል በአግራሞት ይገልጻል፦
“እጅግ ውብ የኾነው ልዑል እንደ ርሱ የተዋበችውን ልዕልት መብቱን በመጠቀም (ἁρπαγμα) የራሱ ሊያደርጋት አልከጀለም[10]”
በዚህ ብቻ ሳይኾን፣ በሌሎች ምንባባትም ላይ ἁρπαγμός “አርፓግሞስ” የሚለው ቃል ሥልጣንን፣ መብትን ለግል ፍላጐት “አለመጠቀም” “አለማዋል” ተደርጐ ተወስዷል[11]
የፀረ ሥላሴአውያን ሙግት
ወደ ቍጥር 9-11 ከመቀጠላችን በፊት፣ በፀረ ሥላሴአውያን የሚቀርበውን ሙግት በጥቂቱም እንቃኛለን። ነጠላ አሐዳውያ (‘biblical’ Unitarians) እና ሙስሊሞች ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት መኖሩን አያምኑም፣ ስለዚህ ይህንን አቋማቸውን ለማጽናት በፊል 2፥6-8 የቀረበውን ግልጽ ምንባብ ለማስተባበል ሌላ ዐውድ ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፤ ሙግታቸውም የሚከተለውን ይመስላል።
ብዙ ፀረ-ሥላሴአውያን ይህንን ክፍል አዳም እና ክርስቶስን በማነጻጸር ይመለከቱታል[12]፤ ይኸውም መሲሑ “በእግዚአብሔር መልክ ” መባሉ ልክ እንደ አዳም እና ማንኛውም ሰው “በእግዚአብሔር አምሳል” (ዘፍ. 1፡26-27) ከመፈጠር ጋር ያገናኙታል፤ ነገር ግን አዳም ከዕውቀት ዛፍ በመብላት ከእግዚአብሔር ጋር “መተካከልን” ለማግኘት ወይም መለኮትነትን ለ“መቀማት” እንደሞከረ (ዘፍጥረት 3: 5, 22)፣ መሲሑ ግን ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን አልወደደም። በሌላ አነጋገር፣ እንደ ፀረ ሥላሴአውያን እምነት፣ “በእግዚአብሔር መልክ” የሚለው ገለጻ የኢየሱስን ሰብኣዊ ማንነት የሚያመለክት ሲኾን፣ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ከአምላክ ጋር እኵል ለመኾን ሳይመኝ፣ ራሱን በትሕትና ዝቅ አድርጐአል። አምላክም ይህንን ታዛዥነቱን በማየት ከፍ ከፍ አድርጐታል የሚል ሙግት ነው፤ ይህ ሙግት ግን በሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ውድቅ ይኾናል።
(1) ይህ ሙግት ቋንቋዊ ድጋፍ የለውም፤ የሰባ ሊቃናት ትርጒምም ኾነ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የሰው ልጅ “የእግዚአብሔር አምሳል” መኾኑን ለመግለጽ “መልክ” (ጽርእ፡ μορφή “ሞርፌ”) የሚለውን የጽርእ ቃል የተጠቀሙበት አንዳችም ምንባብ የለም፤ ይልቁንም ለዚህ ፅንሰ ሐሳብ የሰባ ሊቃናት ትርጒምም ኾነ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት εἰκών “ኤይኮን” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ይስተዋላል (ዘፍጥረት 1፥26፣ 27፤ 9፥6፤ 1ኛ.ቆሮ 11፥7፤ 2 ቆሮ4፡4፤ ቈላ 1፥15፤ 3፥10) ስለዚህ አንድ ሰው “በእግዚአብሔር መልክ” የሚለውን በእግዚአብሔር “አምሳል” በሚል ሊተረጒመው ቢጥርም፣ ይህንን ሐሳቡን የሚያጸና ቋንቋዊ ድጋፍ የለውም። ሌላው ጳውሎስ ኢየሱስን በእግዚአብሔር አምሳል “መፈጠሩን” ለመግለጽ ፈልጐ ከኾነ፣ ስለምን በሌሎች ምንባባት ላይ የሚጠቀመውን ቃል እዚህ ላይ አልተጠቀመም? ስለምንስ እርሱም ኾነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሓፊያን ለዚህ ፅንሰ-ሐሳብ ፈጽሞ የማይጠቀሙትንና ከዘፍጥረት ትረካ ጋር ግንኙነት የሌለውን ቃል መረጠ?
(2) ከላይ የተመለከትነው የፀረሥላሴያውያን ሙግት ከመሠረቱ አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር እኵል ለመኾን ሞክረዋል በሚል ያለ ልክ የተለጠጠ ስሑት ሙግት ላይ የተመሠረተ ነው። አዳምና ሔዋን ከጅምሩ ከእግዚአብሔር ጋር እኵል ለመኾን አልተመኙም፤ ጥንዶቹ እንደ እግዚአብሔር ለመኾን የተመኙት፣ ክፉውንና ደጉን በማወቅ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፤ የሰባ ሊቃናት ተርጓሚያንም “እንደ” ለሚለው ቃል ὡς “ኦስ” የሚለውን ሲጠቀሙ ጳውሎስ ኢየሱስ ከአብ ጋር እኵል መኾኑን ለማመልከት “ኢሶስ” ἴσος የሚለውን ይጠቀማል። “ኢሶስ” ἴσος ደግሞ ዅልጊዜ በቅዱሳት መጻሕፍት “እኵል” “ዐቻ” የሚል ፍቺን ይይዛል[13]።
በአጠቃላይ በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች በፊልጵስዩስ 2፥6 ላይ አዳምና ክርስቶስን በማነጻጸር የሚቀርበው ሙግት የዐውድም ኾነ የሥነ ቋንቋም ድጋፍ የለውም። ምንም እንኳን ብዙ ፀረ ሥላሴአውያን ይህንን ምንባብ አስመልክቶ የተለየ የሙግት ዐሳብ ቢያቀርቡም እንደ ባርት ሄርማን ያሉ እጅግ ለዘብተኛ የነገረ መለኮት ምሁራን እንኳ፣ በፊልጵስዩስ 2፥6-11 ላይ የሚገኘው ምንባብ፣ ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ዐሥር ዓመታት በኋላ የተጻፈና፣ ጳውሎስም ይህንን ትውፊታዊ ምንባብ ከጥንት ክርስቲያኖች የተቀበለው መኾኑን በመመስከር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ቅድመ ህልውና የሚያጸና ክፍል መኾኑን ይናገራል (Bart D. Ehrman, How Jesus Became God, p. 259)
ኢየሱስ ያህዌ ነው
በዚህ ክፍል ጳውሎስ ኢየሱስ በትሕትና እስከ መስቀል ሞት ድረስ በመታዘዙ ምክንያት እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ እንዳደረገው፣ ጒልበት ዅሉም በፊቱ ተንበርክኮ ጌትነቱን ያውጅ ዘንድ ሲያደርግ እናነባለን። ስለዚህ ኢየሱስ አስቀድመን እንዳየነው መለኮት በመኾኑ፣ ሰው ከመኾኑ በፊት ወደ ነበረው ቦታ መመለሱን የሚገልጽ ነው። ልዩነቱ ግን ከሙታን ከተነሣ በኋላ ይህ ጌትነቱ ለፍጥረት ዅሉ የተገለጸና የታወጀ መኾኑ ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ ከሞት የተነሣው መሲሕ “ከስም ሁሉ በላይ ያለው ስም” እንደተሰጠው ይናገራል። ይህ “ስም” ምንድን ነው ለሚለው አንዳንዶች ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይታወቅበት የነበረ ስም እንደኾነ ይናገራሉ፤ በተለይ በክፍሉ “በኢየሱስ ስም ጉልበት ዅሉ ይንበረከክ ዘንድ” የሚለውን የ1954 ትርጒም ስንመለከት ይህ ዐይነት ምልከታ ሊኖር እንደሚችል ግልጽ ነው። ነገር ግን የዚህ አመለካከት አንዱ ችግር መሲሑ ከስቅለቱና ከፍ ከፍ ከማለቱ በፊት አስቀድሞ በ “ኢየሱስ” ስም ይታወቅ የነበር ሲኾን፣ ይህ ዐዲስ ስም ግን በዐውዱ መሠረት ከዕለተ ሞቱ በኋላ የኾነ መኾኑ ነው። ምሁራን “ተሰጠው”(ጽርእ: ἐχαρίσατο “ኤኻሪሳቶ”) የሚለው ቃል ዐላፊና አንድ ቅፅበት ላይ የተከወነ መኾኑን በማስረዳት፣ ይህ ዐዲስ ስም ከሞቱ በኋላ የተከተለ መኾኑን ይናገራሉ[14]። ስለዚህ ትክክለኛው የክፍሉ ትርጒም “የኢየሱስ ስም ለኾነው”፣ ወይም “ለኢየሱስ ስም” የሚል ይኾናል[15]። የኢየሱስ ስም የኾነው ምንድነው ካልን፣ በቍጥር 11 መሠረት የተሰጠው ስም ጌታ እንደኾነ ተጽፏል። “ጌታ” የሚለው ልዩ ስም የኾነበት ምክንያት ደግሞ፣ የሰባ ሊቃናት በመባል የሚታወቀውና ከዕብራይስጥ ወደ ጽርእ የተመለሰው የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም “ያህዌ” የሚለውን የእግዚአብሔር መጠሪያ የኾነውን ስም አብዛኛውን ጊዜ “ ጌታ” በሚለው ተክቶ መተርጐሙ ነው። በብሉይ ኪዳን ቅጂ ውስጥ በዕብራይስጡ ከ6 ሺሕ ጊዜ በላይ የተጠቀሰው “ያህዌ” (יְהוָ֑ה) የሚለው የእግዚአብሔር ስም ወደ ጽርእ ሲተረጐም አብዛኛውን ጊዜ “ጌታ” (κύριος) በሚለው ስያሜ ተተክቶ እናገኘዋለን። በዐጭሩ “ጌታ” የሚለው ስያሜ “ያህዌ” ለሚለው ስም ምትክነት ጥቅም ላይ የዋለ ነው፤ ስለዚህ የጽርኡ “ጌታ” (κύριος “ኩሪዮስ”) ለመለኮታዊ ስም የሚያገለግል ከኾነና፣ በአይሁድውያን ዐውድ “ከስም ሁሉ በላይ ያለው ስም” የፈጣሪ ስም ብቻ ከኾነ፣ ይህ “ጌታ” የሚለው ማዕረግ ለክርስቶስ መሰጠቱ መለኮትነቱን የሚያመለክት ነው። ሌላው ኢየሱስን ጌታ ማለቱ ያህዌ ነው ለማለት እንደፈለገ ከተረዳንበት ምክንያት አንዱ፣ በትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ጌትነቱ ከተገለጸበት ጥቅስ በቀጥታ ለክርስቶስ በመጠቀሙ ነው፦
ኢሳ. 45፥23፦ “ጒልበት ዅሉ በእኔ ፊት ይንበረከካል (ἐμοὶ κάμψει πᾶν γόνυ) አንደበትም ዅሉ በእኔ ይምላል (καὶ ἐξομολογήσεται πᾶσα γλῶσσα)”
ፊል 2፥10-11፦ “ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ(ἵνα ἐν τῷ ὀνόματι Ἰησοῦ πᾶν γόνυ κάμψῃ)፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው (καὶ πᾶσα γλῶσσα ἐξομολογήσηται ὅτι κύριος Ἰησοῦς Χριστὸς) ።”
ጌታችን ኢየሱስ በታላቁ መለኮታዊ ስም መጠራቱ ብቻ ሳይኾን፣ ኢሳይያስ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርበውን አምልኮ ይቀበላል። ጳውሎስ “በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከካል” በማለት አምልኮ የሚቀበል መኾኑን ይነግረናል፤ ሐዋርያት ጳውሎስ ብቻ ሳይኾን፣ ዮሐንስም “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ” በዙፋኑ ለተቀመጠው እና ለበጉ አምልኮ እንደሚያቀርቡ ይናገራል። (ራእይ 5፥13)
መደምደሚያ
ቅዱስ ጳውሎስ አማኞች ትሑታን እንዲኾኑና አንዳቸው ከአንዳቸው የተሻሉ እንደኾኑ እንዲቈጥሩ ያሳስባል፤ ለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአርኣያነት ያቀርባል። እርሱ በሰማያዊ ስፍራ ከእግዚአብሔር ጋር እኵል ዕሪና ያለው ኾኖ ሳለ፣ ይህንን ክብሩን ሊለቀው እንደማይገባ ሳይቈጥር፣ ከሰማያዊ ክብሩ በመውረድ የእኛን የባሪያን መልክ በመያዝ፣ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ያለ እንከን አባቱን በመታዘዝ የትሕትናን የመጨረሻ ጥግ አሳይቷል። በዚህም እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ዅሉ በላይ የኾነውን ያህዌ የሚለውን የማዕረግ ስምም አጐናጸፈው። ፍጥረት ዅሉም ጌትነቱን እየመሰከሩ እንዲያመልኩትም አድርጐአል፤ ስለዚህ ፊልጵስዩስ 2፥5-11 የክርስቶስን ቅድመ ህልውናና መለኮትነት የሚያሳይ ምንባብ ነው።
ማጣቀሻዎች
[1] ዮሐ. 1፥1፤ ዮሐ 17፥5
[2] BDAG 4th ed. 584
[3] Philo, Life of Moses 1.66
[4] Justin Martyr, 1 Apology 9
[5]Joseph H. Hellerman, “ΜΟΡΦΗ ΘΕΟΥ as a Signifier of Social Status in Philippians 2:6,” JETS 52/4 (December 2009): 779-797.
[6] Hellerman, 794
[7]Euripides, Bacchae 4-5
[8] ሐዋ 17፥28
[9]Anthony F. Buzzard, Who Is Jesus? A Plea for a Return to Belief in Jesus, the Messiah , 20 ፤ በሥላሴ ማመን ይገባኻልን(ያማርኛ ዕትም), 25
[10] Heliodorus, Aethiopica VII.20
[11] Eusebius, Commentary on Luke 6; Heliodorus, Aethiopica VIII.7; VII.11; VII.20; Isidore of Pelusium, Epistola 4.22
[12] ይህን ሙግት በእንግሊዝኛው Adamic view የሚባል ሲኾን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን መከራከሪያ በስፋት ያቀረበው እንግሊዛዊ ለዘብተኛ የዐዲስ ኪዳን ምሁር የኾነው ጀምስ ዱን(James Dunn) ይመስለኛል(Christology in the Making, pg. 119)
[13] Gordon Fee, Pauline Christology: An Exegetical-Theological Study, 379
[14] Bert-Jan Lietaert Peerbolte, “The Name above all Names (Philippians 2:9),” The Revelation of the Name YHWH to Moses: Perspectives from Judaism, the Pagan Graeco-Roman World, and Early Christianity, 201.
[15] በዚህ ክፍል ኢየሱስ የሚለው ስም ዘርፍ ሙያ (genitive case) ከመኾኑ አንጻር፣ “ለኢየሱስ ስም” ወይም “የኢየሱስ ስም ለኾነው” የሚለው ሰዋስዋዊ ሐሳቡን የጠበቀ ነው፤ (Ralph P. Martin, Carmen Christi: Philippians 2.5-11 in Recent Interpretation and in the Setting of Early Christian Worship [Cambridge University Press 1967], pg. 250)